የማይመቱት ልጅ…ሲመክሩት ይሰማል Featured

03 Sep 2015

ማንም ወላጅ ቢሆን ልጁ ምግባረ ብልሹ ሆኖ ማየትን አይፈልግም፡፡ ልጆች በመልካም ምግባር አድገው ለቁም ነገር ሲበቁ ማየት ለወላጆች ስኬት ነው፡፡ ሰው የሚማረው ከቤት ጀምሮ፣ በሠፈር ውስጥ፣ በትምህርት ቤትና ማሕበረሰቡ ውስጥ ከሚያያቸውና ከሚሰማቸው ነገሮች ቢሆንም ልጅን ግብረ ገብ አድርጎ የማሳደግ ድርሻ በዋነኛነት የወላጆች ነው፡፡

የጨዋ ልጅ አባት/እናት ተብሎ መጠራት ማንም የሚፈልገውና ሁሉም ሰው የሚስማማበት ቢሆንም ልጆቻችንን እንዴት በመልካመ ምግባር ኮትኩተን እናሳድግ የሚለው ጥያቄ ልዩነቶችን ሲፈጥር ይታያል፡፡ አንዳንዱ ቤተሰብ ቁንጥጫና ኩርኩምን ሲያስቀድም ሌላው “ልጆች በጭራሽ ዝንባቸው እንኳ እሽ መባል የለበትም” በማለት መመካከርና ንግግርን ይጠቀማል፡፡

ምንም እንኳ ልጆችን ከመቅጣት ይልቅ መምከርን የሚመርጡ በርካቶች ቢኖሩም ባህላችን ግን ልጆቻችንን መቅጣትን የሚያበረታታ ነው፡፡ «የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል» ተብሎ የሚተረተውም ያለ ነገር አይደለም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ልጅን በበርበሬ ማጠንና በሳማ መግረፍ ሥርዓት ማስያዝ እንጂ በሕጻናት ላይ የሚደርስ አካላዊ ቅጣት ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ በእርግጥ እዚህ ድረስ አይደርስ ይሆናል እንጂ አሁንም ቢሆን ማሕበረሰባችን ልጆች መልካም ስነ ምግባር ይዘው እንዲያድጉ መቀጣት እንደሚኖርባቸው በሰፊው ያምናል፡፡

ልጆችን መግረፍ ሕጻናቱን የመልካም ባሕርይ ባለቤቶች ያደርጋል ብለው የሚያምኑ ወላጆች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያት ሲሰጡ መስማትም የተለመደ ነው፡፡ ይሄም በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን አሜሪካን ጨምሮ ሰልጥነዋል በሚባሉ በርካታ አገራት መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን መቅጣት እንደሚኖርብን እንደሚፈቅድ እንደ ምክንያት ሲቀርብና ሕጻናቱም ለቅጣት ሲዳረጉ ይታያል፡፡

በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ልጅን መቅጣት ለልጁ መልካም ምግባርም ሆነ ለወላጆች እረፍት መልካም መሆኑን የሚመክሩ አንቀፆች አይጠፋውም፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በተለይም በመጽሐፈ ምሳሌ ልጅን መቅጣት አስፈላጊ እንደሆነ ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ሕፃንን ከመቅጣት ቸል አትበል፣ በበትር ብትመታው አይሞትምና›› ብሎ የሚጀምረው አንዱ ጥቅስ ‹‹በበትር ትመታዋለህ፣ ነፍሱንም ትታደጋለህ›› ሲል ይጨርሳል፡፡ ሌሎችንም በርካታ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ምዕራፍና ቁጥሮች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‹‹በትርና ተግሳጽ›› ለልጆች ጥበብን እንደሚሰጡ፤ በሕጻናት ልብ ውስጥ የታሰረውን ስንፍና በትር እንደሚያርቃት፤ ልጅ መቅጣት ለወላጁ እረፍትን እንደሚሰጥ ለነፍስም እርካታ እንደሆነ ወዘተ የሚያስተምሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ብዙ ናቸው፡፡

ሆኖም ግን ልጅን መልካም ስነ ምግባር ለማስተማር ቅጣት አስፈላጊ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰው የሚከራከሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀታቸው የተመረጠ ወይም እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ የተተረጎመ ሊሆን እንደሚችል ሕጻናትን መቅጣት ተገቢ አይደለም ብለው የሚከራከሩ አካላት የሚያነሱት ሃሳብ ነው፡፡ በሀዲስ ኪዳን ውስጥ “በትር” ሌላ ትርጉም ስላለው “ልጅን መቅጣት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብሎ ማመን ሞኝነት ነው” የሚሉት እነኚህ ወገኖች፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት በጊዜና በቦታ ልዩ ልዩ ትርጓሜ እየተሰጣቸው እንደመጡና በየጊዜውም ከልዩ ልዩ ባሕሎች ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ መተርጎሙን እያነሱ ልጅን መቅጣት ምንም አይነት ሃይማኖታዊ መሠረት እንደሌለው ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡

ቅጣት ያስተምራል?

 

ልጆችን መግረፍ ምግባረ ብልሹ ሆነው እንዳያድጉ የሚያደርግ ሁነኛ መንገድ ነው ብላ ታምን የነበረች አንዲት እናት ታሪክ እናንሳ፡፡ ይህቺ የሁለት ልጆች እናት አንድ ቀን ሦስት ዓመት የሆነው ልጇ አንድ ዓመት ከሁለት ወራት ዕድሜ ያላትን ታናሽ እህቱን ሲመታ ታየውና ለምን እደዚያ እንዳደረገ ትጠይቀዋለች፡፡ ልጁ የሰጠው ምላሽ አስገራሚ ነበር፡ ‹‹እየተጫወትን እኮ ነው እማዬ››፡፡ ይህቺ እናት ከዚህ በኋላ ልጆቿ ላይ አርጩሜ መምዘዝ አቆመች፡፡

ሕጻናት ሌላ ሰው የሚያደርገውን ነገር ሁሉ መቅዳት ይወዳሉ፤ በተለይም የሚወዱትና የሚያከብሩት ሰው የሚያደርገውን፡፡ እናንተ ወላጆች የምታደርጉት ነገር በጠቅላላ ለማድረግ ምንም ችግር እንደሌለው አድርገው ያስባሉ፡፡ ስለዚህም ቅጣት ለልጆች የሚያስተምረው ነገር ቢኖር ሌላውን ሰው መምታት ምንም ችግር እንደሌለበትና ተገቢ የሆነ የግንኙነት መንገድ እንደሆነ ነው፡፡

ወላጆች የሚያሳድጓቸው ልጆች ነገ የልጆች አባትና እናት እንደሚሆኑ ማስታወስ ይኖርባቸዋል፡፡ እነሱ ላይ የምትጠቀሟቸው የአስተዳደግ መንገዶች ማለት እነሱም ልጆቻቸው ላይ የሚጠቀሟቸው መንገዶች የመሆን ዕድላቸው የሠፋ ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተሰብ ማለት ልጆች ግጭትን የሚፈቱበትን መንገድ የሚያዩበት የሙከራ ቦታ ነው፡፡ በልጅነታቸው እየተገረፉ ያደጉ ሰዎች ግጭት በሚያጋጥም ጊዜ በጉልበት ለመፍታት እንደሚቀናቸው ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡

በእርግጥ ልጆችን መቅጣት ወደ መጀመሪያ አካባቢ ልጁ ከመጥፎ ምግባር እንዲርቅ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ይህ አይነቱ ዘዴ በረጅም ጊዜ የሚያመጣው የራሱ ጣጣ አለው፡፡ ይሄውም በዚያ መንገድ ያደጉ ልጆች ቁጡና ተደባዳቢ ይሆናሉ፡፡ ከቤት የመውጫ እድሜያቸው ደርሶ ከሕብረተሰቡ ጋር ሲቀላቀሉም ይሄ ባሕሪያቸው ጎልቶ እንደሚታይ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡

እየተቀጡ ያደጉ ሰዎች የራሳቸውንም ልጆች በዚያው መንገድ የማሳደግ ዕድላቸው በሦስት እጅ ይጨምራል፡፡ ግርፋት ለልጆች የሚያስተምረው ነገር ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረስ ምንም ችግር እንደሌለውና ችግሮችንም በመማታት መቅረፍ እንደሚቻል ነው፡፡

ስነ ልቦናዊ ጫና

 

አካላዊ ቅጣት የተደረገባቸው ልጆች ስነ ልቦናዊ ቅጣትም ሲደርስባቸው ይስተዋላል፡፡ በንግግርም ሆነ በድርጊት ጥቃት የደረሰባቸው ሕጻናት የስነ ልቦና መረበሽ ይደርስባቸዋል፡፡ አካላዊ ቅጣት ልጆች ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ዝቅ ያለ እንዲሆን የሚያደርግ ሲሆን ለአዕምሮ ጉዳት፣ ለአደንዛዥ ዕፆች ተጠቃሚነት እና ለመሳሰሉ ተያያዥ ችግሮች የተጋለጡ እንደሚሆኑ የአሜሪካ የጤና ሚኒስቴር የሠራው ጥናት አሳይቷል፡፡ በተጨማሪም በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ያደጉ ልጆች ትልቅ ሰው ሲሆኑ፣ ከሰው የመግባባት ችሎታቸው ደካማ እንደሚሆን፣ ጭንቀትና ድብርትም እንደማያጣቸው ጥናቱ አሳይቷል፡፡

ልጆች ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት መገንባት የሚጀምረው ሌሎች ሰዎች ለእነሱ ያላቸውን አመለካከት ከማየት ጀምረው ነው፡፡ በፍቅር የተሞሉ በሚባሉ ቤተሰቦች ውስጥ እንኳ፤ አልፎ አልፎ የሚደረግ ግርፋት ለምን እንደተቀጣ ለማያውቀው ሕጻን የተዘበራረቁ መልዕክቶች እንዲተላለፉ ያደርጋል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያሳዩት ፍቅር ልጁ ዋጋ እንደሚሰጠው የሚያሳዩት ሲሆን ልጁ በድንገት ብርጭቆ ወይ የሆነ ሌላ የቤት ዕቃ በአጋጣሚ ይሰብርና ይገረፋል፡፡ በዚህ ጊዜ ልጁ መጥፎ ልጅ እንደሆነ አድርጎ ያስባል፡፡ የሚገርመው ነገር ወላጆች ተፀፅተው ልጁን ቢያቅፉትና ቢስሙት እንኳ ልጁ ላይ የሚቀረፀው የመጎዳት ስሜት አይፋቅም፡፡ አቅፋችሁና አባብላችሁት እንኳ እስከ ረጅም ጊዜ ድረስ መመታቱን ያስታውሳል፡፡ ግርፋት በተደጋጋመ ቁጥር ደግሞ ለልጁ የሚደርሰው መልዕክት አንድ ነው። «ደካማ እና ምንም የመከላከል አቅም የሌለህ ነህ»፡፡

ለአስራ ዘጠኝ ዓመታት የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው አካላዊ ቅጣት እየተደረገባቸው ያደጉ ልጆች ከሰዎች ለመቀላቀል አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸውና በባሕሪይም ግለኛና ራስ-ተኮር እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ለአቅመ አዳም ሲደርሱና ከዚያም በኋላ ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑ ደግሞ አካላዊ ጥቃትን በሌላ ሰው ላይ ማድረስ ያለው ችግር የማይታያቸው እንደሚሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ትምህርት በሚከታተሉበት ጊዜ ደግሞ የስነ ልቦና መረበሽ ይታይባቸዋል፡፡

 

ሲገርፉ ክብርዎን ያጣሉ

 

ጆዋን የተሰኘች ልጆችን በመቅጣት የምታምን አሜሪካዊት እናት ግርፋት «ለልጁ በጣም ይጠቅመዋል» ብላ ታስብ ነበር፡፡ ልጇ ከመስመር ሲወጣ በግርፋት ሥርዓት እያስያዘችው የተወሰኑ ወራት ከተቆጠሩ በኋላ ልጁ ላይ ለውጦች መታየት ጀመሩ፡፡ ከጓደኞቹ ጋር መጫወት እያስጠላው፣ አንድ ጥግ ላይ ብቻውን በድብርት እየቆዘመ፣ ከእናቱም ጋር ዓይን ለዓይን ከመተያየት እየሸሸ መጣ፡፡ ቀድሞ የነበረውን ንቃትም አጣ፡፡ ከውጭ ሲታይ «ጨዋ ልጅ» የሚባል ቢሆንም ሕጻኑ ግን በውስጡ በጣም ብልሹ ልጅ እንደሆነ ያስብ ነበር፡፡ ግርፋት ከመጠኑ ያነሰ እና ደካማ ሆኖ እንዲሰማው ያደረገው ሲሆን ከእሱ በሚተልቁ ሰዎች መጨቆን የሚችል እንደሆነም አስተምሮታል፡፡

ይሄ እንግዲህ ልጅ ላይ ዱላ መምዘዝ ምን ያክል ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ማሳያ ሲሆን ግርፋት ከዚህም በተጨማሪ የወላጅን ዋጋ ያሳጣል፡፡ ፈላጭ ቆራጭ ሆናችሁ መታየታችሁ እንድትከበሩ ያደርግ ይሆናል ልጃችሁ ግን ፈጽሞ አይፈራችሁም፡፡ ምክንያቱም ዘላቂ የሆነ የበላይነት በፍርሐት ላይ ሊመሠረት አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት ልጁ ለወላጆቹ ያለውን አክብሮት ያጣል፡፡ ወላጆች ደግሞ ጭንቅላታቸው ከግርፋት ሌላ አማራጭ መፍትሔ እንደሌለ አድርጎ እንዲያስቡ ይሆናሉ፡፡ ስሜቶቹን የመቆጣጠር ችሎታውን እንዲያዳብር ስላላስተማሩት የበለጠ ጥፋቶች እየፈጸመ ለተጨማሪ ግርፋት ይዳረጋል፡፡ ይሄ ደግሞ የማያቋርጥ ዑደት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻም ልጁ የትዳር አጋሩን የሚደበድብ፤ በቅጣት ስም ልጆቹ ላይ አካላዊ ጥቃት የሚያደርስ አባት ባስ ሲልም ከባድ ወንጀል ሠርቶ ራሱን እስር ቤት የሚያገኘው ይሆናል፡፡ በጣም ከባድ የሚባሉ ወንጀሎችን ፈጽመው እስር ቤት የሚገኙ ሰዎች ታሪክ እንደሚያሳየው እነኚህ ወንጀለኞች ከመጠን ያለፈ አካላዊ ቅጣት በነበረበት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ናቸው፡፡

 

ከቅጣት ወደ ጥቃት

... 2006 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መብቶች ኮሚቴ ልጆችን አካላዊ ቅጣት መቅጣት «በሕጻናት ላይ የሚደርስ ሕጋዊ የሆነ ጥቃት ነው» በማለት ገልፆት ሊወገድ እንደሚገባው አስምሮበታል፡፡ ይህ ስምምነት በ192 አገሮች ስምምነት ላይ የተደረሰበት ሲሆን የሚገርመው ነገር ይህንን ስምምነት ካልፈረሙት ሁለት አገሮች አንዷ አሜሪካ መሆኗ ነው፡፡

ልጅን መቅጣት እየተባባሰ የሚሄድ ነገር ነው፡፡ ልጅን በትንሹ መቅጣት ከጀመሩ መቼ እንደሚያቆሙ አይታወቅም፡፡ ዳዴ የሚል ልጃችሁ እንዳይነካ የተነገረውን ስኒ ሰበረ እንበል፡፡ ሁለተኛ እንዳይለምደው አይበሉባውን መታ መታ ታደርጉታላችሁ፡፡ እሱም ለአፍታ ያክል እጁን ሰብሰብ ካደረገ በኋላ ቤቱ ውስጥ ዋጋ የሚሰጡትን ሌላ ዕቃ ይሰብራል፡፡ ከበፊቱ ጠንከር ባለ ሁኔታ ትመቱታላችሁ፡፡ ማንም ሊያሸንፈው የማይችለውን ጦርነት ጀመራችሁ ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ጉዳዩ ከልጃችሁ ወይም ከእጃችሁ ማን ይበረታል? የሚለው ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ልጁ ሕግ አለማክበሩን እስኪያቆም ድረስ ዱላ መሰንዘራችሁን ትቀጥላላችሁ?

ከመጀመሪያውም ቢሆን አካላዊ ቅጣት የመጀመር ችግር የዱላውን መጠን እየጨመሩ መሄድ ማስፈለጉ ነው፡፡ አይበሉባ ላይ የምታርፍ ተራ ምት ወደ ቁንጥጫ፣ ከቁንጥጫ ወደ ቀበቶ፣ ከቀበቶ ወደ አለንጋ… እያለ እያለ ሲጀምር ልጁን ለማረም ይደረግ የነበረው ቀላል ቅጣት ሕጻናት ላይ የሚደርስ አካላዊ ጥቃት ሆኖ ይጠናቀቃል፡፡ አካላዊ ቅጣትን የሚጠቀሙ ወላጆች የቅጣቱን መጠን እየጨመሩ ከመምጣት አያመልጡም፡፡ ይሄም የሚሆነው ባሕሪን የማስተካከያ አማራጭ ዘዴዎችን ስለማይጠቀሙ ነው፡፡ ስለዚህም ልጆቻቸው «ወጥ በረገጡ» ቁጥር አካላዊ ቅጣትን ከመጠቀም አይቦዝኑም፡፡

 

እናስ ምን ይበጃል?

 

ልጆችን መቅጣት ፈፅሞ አስፈላጊ አይደለም ሲባል ግን ልጆች ሥርዓት አልባ ሆነው እንዲያድጉ ፍቀዱላቸው ማለት አለመሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ልጆች መልካም ምግባርን ሊማሩ የሚችሉት ከወላጆቻቸው መሆኑ ግልፅ ነውና ይሄንን እንዲያገኙ ማድረግ ከማንም በላይ የወላጆች ኃላፊነት ነው፡፡ ታዲያ ጥያቄው የሚሆነው «ልጆቻችን ሥርዓት እንዲይዙ ካልቀጣናቸው በምን ዓይነት መንገድ ማስተማር እንችላለንየሚለው ይሆናል፡፡ ልጆችን በስነ ምግባር አንፆ ለማሳደግ የሚረዱ ከ«በትር» ውጪ የሆኑ ዘዴዎች በርካታ ቢሆኑም ለዛሬ ጥቂት ስልቶች መርጠን እናያለን፡፡

በዘርፉ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ወላጆች ግጭትን ስለሚፈቱበት ተገቢ የሆነ መንገድ ከልጆቻቸው ጋር መወያየት አለባቸው፡፡ በልጆች ላይ እምነትን በመፍጠር ስርዓት መያዝ ያለፍላጎት የሚደረግ ነገር እንዳልሆነ ወይም በብስጭት የሚደረግ እንዳልሆነ ያሳያቸዋል፡፡ ስለዚህ ልጆችን ሳንቀጣ እንዴት ማስተማር እንችላለን?

 

አንድ፦ የራሳችሁን ስሜት ተቆጣጠሩ

 

የራሳችሁን ስሜቶች ስትቆጣጠሩ፤ ልጆችም እንደዚያው ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ በተበሳጫችሁበት ሰዓት ምንም ዓይነት እርምጃ አትውሰዱ፡፡ አየር በጥልቀት ወደ ውስጥ ሳቡና እስክትረጋጉ ጠብቁ፡፡ ከዚህ በኋላ መፍትሔ ወደ መስጠት መሄድ ትችላላችሁ፡፡ ቅጣት የመቅጣት ፍላጎታችሁ ሁል ጊዜም ቢሆን መጥፎ የሆነ ውጤት ያመጣልና ለመገደብ ሞክሩ፡፡

 

ሁለት፦ ከማረም በፊት መግባባት

 

ለማረም ከመነሳታችሁ በፊት ጠንካራ የሆነ ግንኙነት በእናንተና በልጁ መካከል መኖሩን ያረጋግጡ፡፡ ልጆች መጥፎ ባሕሪ የሚኖራቸው ስለራሳቸው የሚኖራቸው መጥፎ የሆነ ስሜት ሲሰማቸውና ከወላጆች ጋር ጠንካራ የሆነ ግንኙነት እንደሌላቸው ሲሰማቸው መሆኑን አስተውሉ፡፡

 

ሦስት፦ ጥፋቱን ራሱ ያስተካክል

 

ማናችንም ብንሆን የራሳችንን ጥፋቶች የማስተካከል ኃላፊነት እንዳለብን በማስተማር ጀምሩ፡፡ ለምሳሌ ልጁ እየጠጣ የነበረውን ወተት ደፋው እንበል፡፡ ፎጣ ያዙና ያለ ሀፍረትና ያለ መወቃቀስ የደፋውን እንዲያፀዳ እርዱት፡፡ እያደገ ሲሄድ ደግሞ በመረጋጋት ሁሉንም ችግሮቹን መፍታት እንደሚቻልም አስተምሩት፡፡

 

አራት፡- «አዎ» በሉ

 

ልጆች በፍቅር እስከተጠየቁ ድረስ አድርጉ የተባሉትን ነገር ሁሉ ያለ ማቅማማት ያደርጋሉ፡፡ ገደብ ስታስቀምጡላቸው እንኳ ለልጆቻችሁ ጥያቄዎች «አዎ» የሚል ምላሽ የምትሰጡበትን መንገድ አመቻቹ፡፡ በዚህ ጊዜ እርስዎ ባሳዩት የአዎንታዊነት አስተሳሰብ መጠን ልጁም ምላሽ እየሰጠ ይሄዳል፡፡

 

አምስት፦ ያላችሁን ኃይል ዕወቁት

 

ሕጻንን በመግራት ሁኔታ ላይ ከምታስቡት በላይ ኃይል አላችሁ፡፡ ልጃችሁም ምንም እንኳ የሚቃወም ቢመስልም በእናንተ አመራር ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ለልጆቻችሁ በቂ ድጋፍና እገዛ ካደረጋችሁ እንዲሆኑላችሁ ወደምታስቡት ዓይነት ሰው ይቀየራሉ፡፡ ምናልባት አንዳንዶቹ ልጆች የበለጠ ድጋፍና አትኩሮት ይፈልጉ ይሆናል እጂ ሊለወጡ የማይችሉ ልጆች ፈጽሞ የሉም፡፡

እነኚህ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ዘዴዎችን የተጠቀመ ወላጅ «ጨዋ»፣ ባለ መልካም ምግባርና ለሀገር የሚጠቅም ዜጋ ማፍራት ይቻለዋል፡፡ ልጅን መስመር ለማስያዝም ከአለንጋ ይልቅ ምክር የበለጠ ውጤታማ ነው፡፡ ሥርዓትን በግርፋት የሚይዝ ልጅ በልቡ ግን ቁጡና «ሥርዓት አልባ» ሆኖ ያድጋል፡፡ ስለዚህም ልጆች «ፈር ሲስቱ» ቀምበር ውስጥ እንደገባ በሬ አለንጋ አንስቶ ሾጥ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች ስልቶችን ተጠቅሞ ማረቅ ይበጃል፡፡ የማይመቱት ልጅ ሲመክሩት እንደሚሰማም በቀላሉ ለማየት ይቻላል፡፡

 

ፀሃፊው ሙሉጌታ አለባቸው

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000141468
TodayToday58
YesterdayYesterday90
This_WeekThis_Week167
This_MonthThis_Month2821
All_DaysAll_Days141468

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።