ከሞት መንጋጋ ያመለጡ ስንኞች Featured

27 Aug 2015

ህላዌ ግጥም እንዲጽፍ ያነሳሳው የዘጠኝ ዓመቱ ታዳጊ ፍቅሩ ዮሴፍ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በትምርት ቤታቸው በሚደረግ የክርክር መድረግ ለመሳተፍ ዕድሉ ይደርሰውና ዝግጅቱን ይጀምራል፡፡ ይህ ክርክር ለየት የሚያደርገው ነገር የሚከናወነው በግጥም መሆኑ ነው፡፡ የክርክሩ ርዕስም ‹‹ከገጠርና ከከተማ ሴት የትኛዋ ትሻላለች?›› የሚል ነበር

 

ሰደፍና ግጥም

ወቅቱ የደርግ መንግሥት በኢህአፓ አባልነት የተጠረጠሩ ሰዎችን በብዛት እያፈሰ ወደ እስር ቤት የሚወረውርበት፣ ለግርፋት እና ለስቃይ የሚዳርግበት በመጨረሻም በሞት የሚቀጣበት አስጨናቂ ጊዜ ነበር፡፡ ቀይ ሽብር ተፋፍሟል፡፡ በነጻ እርምጃ ሰበብም በየሠፈሩ ያሉ አብዮት ጠባቂዎች ‹‹ዐይነ ውሀው ያላማራቸውን›› ሰው በፈለጉበት ሰዓትና ቦታ ያለምንም የፍርድ ሂደት ደመ ከልብ አድርገው የሚያስቀሩበት ዘመን ነበር፡፡ እስር ቤቶች በግርፋት የስቃይ ድምፆች፤ መንገዶችም በወጣቶችና ጎልማሶች ደም ታጠቡ፡፡ የጅምላ መቃብሮች የመንግስት ተቃዋሚዎችን ሊውጡ አፎቻቸውን በሰፊው ከፈቱ፡፡

በዚሁ አስከፊ ዘመን በ1969 .. በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ከመንግስት ጎን ያልሆነ ፖለቲካዊ እቅስቃሴ በማድረጋቸው የታሰሩ፤ ታስረውም ለግርፋትና እንግልት የተዳረጉ አምሳ የሚደርሱ ሰዎችን የጫኑ የወታደሮች ጂፖች በመቃብር ቆፋሪ መኪና ታጅበው ከማዕላዊ እስር ቤት በስድሰት ኪሎ አድርገው፤ ቀበናን ተሻግረው ወደ ኮተቤ ይከንፋሉ፡፡ በመኪኖቹ ላይ እጆቻቸው የፊጥኝ ታስረው የተጫኑት ሰዎች ዕጣ ፋንታቸው ምን እንደሆነ እያወቁም እንኳ የትግል መዝሙሮቻቸውን ከመዘመር አልተቆጠቡም ነበር፡፡ ከመካላቸው አንደኛው ደርግ እርምጃ ሊወስድባቸው እንደሆነና አገራቸው ከመውደዳቸው ውጪ ምንም ጥፋት እደሌለባቸው ጮክ ብሎ ይለፍፋል፡፡ በየመንገዱ ዳር የሚያልፉ ሰዎች ድምፅ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተገላመጡ ያያሉ፡፡ የሚናረው ነገር ከመኪኖች ድምፅ ጎልቶ ተሰሚነት ይኑረው አይኑረው ግድ አላለውም፡፡ ቀሪዎቹ ሕብረ ዝማሬያቸውን ሳያቋርጡ ያዜማሉ፡፡

ቀበናን አልፈው ጥቂት እንደተጓዙ ከታሳሪዎቹ መካከል የስብስቴ ነጋሲ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምርት ቤት መምህር የነበረ አንደኛው ሰው የታሰረበትን ገመድ መፍታት ቻለ፡፡ ፈጠን ብሎም የሌሎቹንም እስር ይፈታላቸው ጀመር፡፡ እስሩ የተፈታላቸው ወጣቶችም መኪናዋ ምቹ ቦታ እስክትደርስ ጠብቀው እየዘለሉ መውረድ ጀመሩ፡፡ እግሮቻቸው መሬት እንደነኩም በየአቅጣጫው እግሬ አውጭኝ ሆነ፡፡ ሆኖም አጅበዋቸው ከሚከተሏቸው ሌሎች መኪኖች ተኩስ ሲከፈትባቸው አፍታም አልቆየ፡፡ ብዙዎቹ እዚያው ሰለባ ሆነው ቀሩ፡፡ ስምንት ያህሉ ሮጠው ለማምለጥና ነፍሳቸውን ለማትረፍ ቻሉ፡፡

ከሞት መንጋጋ አምልጠው በቀሪ ሕይወታቸው ታሪክ ለመሥራት ከቻሉት መካከል አንዱ የሀያ ዓመት ወጣት ፍቅሩ ዮሴፍ ነበር፡፡ ፍቅሩ ከዚያ ዘመን ጀምሮ ሲጽፋቸው የነበሩ የግጥም ስብስቦቹን አሳትሞ በያዝንው ዓመት እንካችሁ ያለን ገጣሚ ነው፡፡ ይህ ወጣት በዚያች ዕድለኛ ቀን የሞትን ጽዋ ካሳለፋት በኋላ ሕቡዕ ገብቶ መንቀሳቀሱን ቀጠለ፡፡ ጥቂት ቆይቶም የኢህአፓ የጦር ክንፍ የሆነውን ሠራዊት (ኢህአሰ) ተቀላቀለ፡፡ ከኢህአፓ መፈራስ በኋላም የያኔውን ኢህዴን የአሁኑን ብአዴን ከትግል አጋሮቹ ጋር በመሆን ለመመሥረት ቻለ፡፡

በትግል ወቅትና ከዚያም በኋላ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅና ታዋቂ የሆኑ ግጥሞች ባለቤት ነው፡፡ ጠንካራ ግጥሞቹ ታጋዮች ተስፋ ሊቆርጡ በታቀረቡባቸው ጊዜያት ሁሉ የተስፋ ጭላንጭንል በመስጠት ያበረቱ እደነበር አብረውት የታገሉ ሁሉ ምስክር ሆነው ይቆማሉ፡፡ ይህ የበርካታ ግጥሞችና መዝሙሮች ፀሐፊ ብዙዎቻችን በምናውቀው የትግል ስሙ ህላዌ ዮሴፍ ይባላል፡፡ ህላዌ በልዩ ልዩ የመንግሥት አመራር ቦታዎች ላይ ሲሠራ ቆይቶ በአሁኑ ሰዓት በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ዛሬ የምንጨዋወተው ስለ አምባሳደሩ ሳይሆን ስለ ገጣሚው ህላዌ ነውና አንተ እያልኩ መጥራቴ አክብሮት ከማጓደል አለመሆኑ እንዲታወቅ አሳስቤ እንዲህ እቀጥላለሁ፡፡

ህላዌ ግጥም እንዲጽፍ ያነሳሳው የዘጠኝ ዓመቱ ታዳጊ ፍቅሩ ዮሴፍ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በትምርት ቤታቸው በሚደረግ የክርክር መድረግ ለመሳተፍ ዕድሉ ይደርሰውና ዝግጅቱን ይጀምራል፡፡ ይህ ክርክር ለየት የሚያደርገው ነገር የሚከናወነው በግጥም መሆኑ ነው፡፡ የክርክሩ ርዕስም ‹‹ከገጠርና ከከተማ ሴት የትኛዋ ትሻላለች?›› የሚል ነበር፡፡ የገጠር ሴትን ደግፎ የተከራከረው ቡድን ግጥሙን አቅርቦ ከመድረክ ሲወርድ፤ የሦስተኛ ከፍል ተማሪ የነበረው ፍቅሩ የገጠር ሴት ‹‹እበት የምትጠፈጥፍና ንጽሕናዋን የማትጠብቅ›› እንደሆነች አድርጎ ያዘጋጀውን ግጥም ማቅረብ አልቻለም፡፡ ግጥሙን እንደማያነብ ሲከራር ጥቂት ቢቆይም የቡድን አባላቱን ግፊት መቋቋም አልቻለም፡፡ እጆቹ እየተንቀጠቀጡ፤ እብዛም ተሰሚ ባልሆነ ድምጽ አንብቦ ከመድረኩ ወረደ፡፡ ፍቅሩ በዚህ ግጥም ሀፍረት ቢሰማውም ህላዌ ግን አንድ ነገር አረጋገጠ፡ ግጥም መጻፍ እደሚችል፡፡

ከኢህአፓ ጎን ሆኖ ትግሉን ተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይገጥማል፡፡ በዘመን የተፈተኑ ጊዜ ተሻጋሪ ግጥሞቹ ‹‹ታሪክና ጥበብ›› በሚል ርዕስ ታትመው በያዝነው ዓመት ለገበያ በቅተዋል፡፡ በመልካም የሕመት ጥራት የተሰናዳው ‹‹ታሪክና ጥበብ›› ከ1969 – 2005 (36 ዓመታት) የተጻፉ 60 ግጥሞችና አንድ መነባንብ ይዟል፡፡ ከእነኚህ ግጥሞች መካከል ሀያ ሦስቱ ዜማ ተሠርቶላቸው ተወዳጅ መዝሙሮች ለመሆን በቅተዋል፡፡

‹‹ታጋይ 3 ነገሮችን ይወዳል፡ መጽሐፍትን፣ ሬዲዮንና ስነ-ጥበብን›› ይላል ህላዌ በመጽሐፉ ውስጥ፡፡ ትግል በጠመንጃ ብቻ አለመሆኑን የሚያውቁ ሁሉ ምን እንደሚል ይገባቸዋል፡፡ ጠላት ሁሉ በጥይት አይሞትም፡፡ ሁሉም ትግል በጠመንጃ ብቻ አይካሄድም፡፡ አጠቃቀቀሙን ላወቀ ስነ ጥበብም መሳሪያ ነው፡፡ ግጥምም ከባሩድ እኩል ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው የህላዌ እጆች የጨበጡት ሁለት የተለያዩ መሣሪዎች የሆነው፡ አንደኛው ሰደፍ፤ ሌላኛው ግጥም፡፡

ግጥሞቹ በሦስት ምዕራፍ ተከፍለው ሊታዩ እደሚችሉ የሚናገረው ገጣሚ ህላዌ የመጀመሪው ምዕራፍ ‹‹ለጋ ደረጃ ላይ ያሉ ግጥሞች›› የጻፈበት ከነሐሴ 1969 – 1972 ያለው ጊዜ ነው ይላል፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከ1972 – 1983 ያለው ዘመን ነው፡፡ ይህ ጊዜ ድርጅት (ኢህዴን) ለመመሥረት ጥረት ከተጀመረበት እስከ ደርግ ውድቀት ያለውን የሚያካት ሲሆን በታጋዩ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡም ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ‹‹ያልተንበረከክነው›› እና ‹‹ደማቅ ታሪክ ጻፈ›› የመሳሰሉ ታዋቂ ግጥሞች የተጻፉበት ወቅት ነው፡፡ ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከደርቅ ውድቀት ወዲህ የተጻፉ ግጥሞች የተገጠሙበት ጊዜ ነው፡፡

ግጥምና ታሪክ

‹‹የንቅናቄው ፍልሚያ አዋጅ›› በሚል ርዕስ ሥር በሰፈረው ጽሑፍ ላይ ‹‹ሚያዚያ 11 ቀን 1973 ሚሲግ ሚካኤል በተባለ መንደር ተሰባሰብን፡፡ … ከዚህ ቀን ጀምሮ ትጥቅ ትግሉን በይፋ እንደጀመርን አበሰሩ፡፡ ለበዓሉ ፍየልም አርደን ደስ የሚል ካምፕፋየር አደረግን፡፡ ግጥሞች ተነበቡ፤ መዝሙሮች ተዘመሩ፡፡ ጨፈርን፤ ለትጥቃዊ ፍልሚያው ተነሳን፡፡ አብሪ ጥይቶች የብስራት ርችት ሆነው ተተኮሱ፡፡ እኔም ለዚህ ቀን ያዘጋጀሁትን ይህንን መነባንብ አሰማሁ›› ይለናል ገጣሚው፡፡ (ሆኖም ይህ ግጥም መጽሐፉ ውስጥ አልተካተተም)፡፡

ታሪክ በመሥራት ሂደት ውስጥ የግጥም ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ በማንኛውም ዓይነት ንቅናቄ ውጤት ማጣት የሚሻ ማንኛውም አካል ስነ ጥበብ በተለይም ግጥምን ወደ ጎን ቢያደርግ ጥረቱ ከጥቂት እርምጃዎች የዘለለ አይሆንም፡፡ ለዚህም ነው በየጊዜው የሚነሱ ኃይሎች ሁሉ ግጥምና መዝሙርን እንደተጨማሪ መሣሪያ የሚጠቀሙት፡፡

ከህላዌ ጋር ከ1970 .. ጀምሮ ትውውቅ ያላቸው አቶ በረከት ስመዖንም የሚሉት ይሄኑ ነው፡፡ ‹‹በኢህአፓ ጊዜም መዝሙሮች ነበሩ፡፡ ስንሸነፍና ስናሸንፍ እንዘምራለን፡፡ ኢህዴንን ስንጀምርም አልተውንውም››፡፡ (በነገራችን ላይ አቶ በረከት ራሳቸውም ግጥሞችን ይጽፋሉ) መዝሙሮች ለትግል መሳካት አስተዋፅዖ የሚደርጉትም ታጋዩን በማበርታት ነው፡፡ ለዚህ ነው አንድ ድርጅት ፈርሶ ሌላ ሲመሠረት መዝሙሮች ግን ጥቅም ላይ መዋላቸው አይቀሬ የሚሆነው፡፡ ኢህአፓ ፈርሶ ኢህዴን ከተመሠረተ በኋላ የመዝሙሮች ቀጣይነት ካረጋገጡ ታጋዮች አንዱ ህላዌ መሆኑንም አቶ በረከት መስክረዋል፡፡

ታሪክና ታጋይ

‹‹ታሪክና ጥበብ››ን የግጥም መጽሐፍ ብቻ ብሎ መጥራት የመጽሐፉን ክብደት ይቀንሰዋል፡፡ ይሄም የሚሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ስንኞቹ በራሳቸው የሚነግሩን ታሪክ በመኖሩ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እያዳንዱ ግጥም ስለተጻፈበት ሁኔታ ማብራሪያ በሚሰጥባቸው የግርጌ ማስታወሻዎች አማካኝነት ታሪክ በመነገሩ ነው፡፡

ገጣሚውም በመጽሀፉ መግቢያ ላይ ይላል፡ ‹‹በትጥቅ ትግሉ ዘመን ስነ ጽሑፍ ላይ ጥናት ለማድረግ ለሚሹ ሰዎችም ይህ መድብል ጥሬ ግብዓት ሆኖ ቢያገለግላቸው በእጅግ እደሰታለሁ››፡፡ መድብሉ ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡ በትግሉ ዘመን ስነጽሑፍ ላይ ብቻ ጥናት ለሚያደርጉ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ ስለ ትግሉ ዘመን ታሪክ ጥናት ለሚያደርጉ ሰዎች ግብዓት ሆኖ ማገልገል የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም የበርካታ ‹‹ያልተዘመረላቸው›› ታጋዮች የጀብዱ ታሪኮች በመጽሐፉ ውስጥ ተካተዋል፡፡

የትግል ዘመን ታሪክ ለመንገር ሲነሱ የታጋዩን ታሪክ መንገር ግድ ይላል፡፡ ታሪካቸው በመድብሉ ውስጥ ከተዘከረላቸው ታጋዮች አንዷ ‹‹ባሰብኩሽ ቁጥር፤ ሁሌ እንደ ታናሽ ወንድምሽ፤ በቅጽል ስሜ ስታቆላምጪኝ ይታወሰኛል›› የሚል የግርጌ ማስታወሻ በሰፈረለት ‹‹እኔም እንዳንቺ ድል ላይ ልቁም›› የሚል ግጥም ውስጥ የተወሳችው ድላይ አንዷ ነች፡፡

እንግዲያውስ እንድለምደው፣

ለዘለአለም እንዳፈቅረው፣

የድልሽን መንገድ ልያዘው…

እጄም እግሬም ይዘርጋ፣

ልሳን አንደበቴም ይዘጋ፣

ሁለመናዬም ይጥፉ…

የልብ ትርታዬም…

እኔም አንዳንቺ ድል ላይ ልቁም፣

እኔም አንዳንቺ ድል ላይ ልቁም፡፡

እንዲህ የተገጠመላት ድላይ ለረጅም ጊዜ ያህል ታሪካቸው ካልተነገረላቸው ታጋዮች ተርታ የተሰለፈች ነበረች፡፡ በእርጥ የጀብዱ ታሪኳ በወሬ የደረሳቸው የቀድሞ ታጋዮች እስካሁን ድረስ ለልጆቻቸው ድላይ የሚል ስም ያወጣሉ፡፡ ሆኖም ግን ከ‹‹ታሪክና ጥበብ›› በፊት የድላይ ታሪክ በተቀናጀ መልኩ በጽሑፍ የቀረበው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ለሕመት በበቃው ‹‹የአሲምባ ፍቅር›› በተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ድላይ (ስመኝ ምናለ) 1969 .. ትግሉን የተቀላቀለች ወጣት ታጋይ ነበረች፡፡ ከመሠረታዊ ታጋይነት ጀምራ ምክትል አዛዥነት ደረጃ ለመድረስ ችላ የነበረ ሲሆን በ1972 .. ስትሰዋ የ19 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡

‹‹ታሪክና ጥበብ›› ከዘከራቸው ታጋዮች ሌላኛው ‹‹መዘክረ ታጋይ›› በሚል ግጥም ውስጥ የሚገኘው አለበል በግዱ (ብርሃኑ) የተባለ ታጋይ ነው፡፡ ህላዌ ለዚህ ታጋይ ከቋጠራቸው ስንኞች መሀል ስንመዝ፡

ሕይወት ያለው ነገር ዝር በማይልበት፣

የውሀ ጠብታ ከማይታይበት፣

ከሐሩር በረሐ የተጣለች እህል፣

በደምህ እርጥባን ትለመልማለች፣

በአንዲቷ ጠብታ ፍሬ ትሰጣለች፡፡

ብርሃኑ ኢህአሠን ከመቀላቀሉ በፊት የደርግ ሠራዊት አባል ነበር፡፡ ኋላም ኢህዴን ሲመሠረት ከመሥራች አባላት አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡ ብርሃኑ በ1975 .. ድርጅቱን ለመቀላቀል ከሄዱ ወጣት አርሶ አደሮች ጋር ተመሳስሎ በገባ የደርግ ሰርጎ ገብ ሰላይ ቢገደልም መዘክረ ታጋይ በሚለው ግጥም ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡

ታጋይና ፍቅር

እንደተፋቀርን ላንተያይ፣ ሳንተያይም ልንፋቀር

እንደ መናን ከዓለም ነገር፣ ከሰው ተራ ስንባረር

በታጋይ ሕግ ተገድበን በአጉል ስርዓት ስንጠፈር

መቸስ ምን እንላለን በተስፋ ከመሞት በቀር፡፡

የዚህ ግጥም ፀሐፊ አቶ በረከት ስመዖን ናቸው፡፡ ግጥሙን የሰማሁትም ‹‹ታሪክና ጥበብ›› በብሔራዊ ቴአትር ሲመረቅ መጽሐፉን እዲመርቁና ይሄንን ግጥማቸውን እዲያቀርቡ በአቶ ህላዌ ተጋብዘው ሲያነቡ ነው፡፡ በትግል ሜዳ የፍቅር ግንኙነት መመሥረት በሕግ የተከለከለ ነበርና ፍቅር የሚሞከር ነገር አልነበረም፤ ከተሞከረም በምስጢር ነበር፡፡ ለዚህም ነው አቶ በረከት ኋላ ላይ ባለቤታቸው ለሆነችው የትግል አጋራቸውና የፍቅር ጓደኛቸው የቋጠሩላቸው ስንኝ ውስጥ ‹‹በታጋይ ሕግ ተገድበን በአጉል ስርዓት ስንጠፈር›› ያሉት፡፡

‹‹ታሪክና ጥበብ›› ከትግል ግጥሞች ባሻገር የፍቅር ግጥሞችም ይዟል፡፡ ‹‹አንድ ላይ›› የሚለውን ግጥም ብንወስድ ገጣሚው ወደ ትግል ከመግባቱ በፊት ይወዳት ለነበረች፤ ስሟ በአፅሕሮተ ቃል ለተቀመጠ አንዲት ኮረዳ የተጻፈ ነው፡፡ ‹‹ትግል ሜዳ ከመውጣቴ በፊት ከደርግ ተደብቄ ከነበርኩባቸው ቦታዎች በአንዱ በአካባቢው ትኖር የነበረችውን ሶ.በን በልቤ ወድጃት ነበርና ትግል ሜዳ ከወጣሁ በኋላ ትዝ ብትለኝ ፍቅሬ ተቀስቅሶ ይህንን ግጥም ጻፍኩኝ፡፡ በወቅቱ 20ኛ ዓመቴን ይዤ ነበር›› ይላል በግርጌ ማስታወሻው፡፡ ግጥሙ በከፊል እንዲህ ይነበባል፡፡

እኔ ጋደም ስል አንቺ ትነቂያለሽ፣

ለኔ ፀሐይ ስትወጣ፣ በጨረቃ ብርሃን…

በከዋክብት ደምቀሽ፣ አንቺ ታልሚያለሽ፣

ግጥሙ ቀጥሎ ለጨረቃ፣ ለፀሐይና ለከዋክብት ባንቺና በእኔ አማላጅነት እንለምንላቸው በዚህም ክረምትና በጋ መዓትና ሌሊት፣ ደቂቃና ሰዓት እንዳይለያዩአቸው/ ተቃቅፈው ተዛዝለው አንድ ላይ ይምጡልን እያለ ከተረከ በኋላ እንዲህ ይቀጥላል፡

እኛም አንድ ላይ፣ አቃቅፈው አዛዝለው…

በፍቅር ሰረገላ፣ ወደ ሀሴት ህዋ…

ወደ ደስታ ጠፈር፣ አጅበው ያብርሩን፣

እያስፈነደቁ በእልልታ ያምጥቁን፣

አሜን! አሜን! አሜን!

ገጣሚው በትጥቅ ትግል ወቅት እንደ አብዛኛው ታጋይ የድብቅ ፍቅር ከመመሥረት አላመለጠም፡፡ ‹‹የትኛው ይሻላል›› በሚለው ግጥም ማብራሪያ ውስጥ እደሠፈረው በትግል ሜዳ የፍቅር ግንኙነት የሚከለክለውን ደንብ ‹‹ሳንሽረው በፊትም በመጠኑም ቢሆን እየሸረሸርነው ነበርና፣ ይህን ግጥም አሁን የትዳር ጓደኛዬና የአንድ ልጄ እና የሆነችው ውዲቱ ኑሩ ስትናፍቀኝ ፃፍኩት›› ይለናል ገጣሚው፡፡

እኔ ምን አገባኝ፣ ቢመሽም ቢነጋ፣

ባይመሽም ባይነጋ፣

አንቺ ካለሽልኝ ልቤና አንጀቴ ጋ፡፡

እንባ አይወጣኝ እኔ ብከፋም ብደሰት፣

ብቀርብም ብርቅም፣ እርሷ ካለችበት፡፡

ፍቅር ሲባል ደስታ፣ ፍቅር ሲባል ሀዘን፣

የትኛው ይሻላል? የትኛው ይቅረበን?

የትኛው ይከፋል? የትኛው ይራቀን?

የታጋይ ፍቅር በህግ፣ በጊዜና በቦታ ታጥሮም ቢሆን ብርቱ ነው፡፡ ይህ በእኛ አገር ብቻም ሳይሆን ወታደሮች ሁሉ የሚወዷቸውን ከኋላ አስቀርተው ወደጦር ሜዳ በሚሄዱበት ጊዜ ናፍቆት ያይላል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የዘመተው ኮንስታንቲን ሲሞኖቭ የተባለ ጋዜጠኛና ገጣሚ በ1941 የጻፋት Wait for ME የተሰኘች ግጥም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆና ልትቀርብ ትችላች፡፡ ‹‹ወታደሮች ይህን ግጥም ከጋዜጣው ቀድዶ በማውጣት ለፍቅረኞቻቸውና ለሚስቶቻቸው ይልኩት የነበረ ሲሆን፣ በቆሰሉና በተሰዉ ወታደሮች የደረት ኪስ ሳይቀር ይገኝ የነበረ ግጥም ነው›› ይላል ግጥሙን ወደ አማርኛ መልሶ በመድብሉ ውስጥ ያካተተው ህላዌ፡፡

Wait for ME ‹‹ጠብቂኝ›› በሚል ርዕስ የተተረጎመ ሲሆን ከማራኪ ስኞቹን ጥቂቱ እነኚህ ናቸው፡

ጠብቂኝ፣ ካለሁበትም ሩቅ ሀገር፣

ደብዳቤም ሳይመጣልሽ ቢቀር፡፡

ጠብቂኝ! ካንቺ ጋር የጠበቁ ሁሉ፣

እርሺው በሕይወት የለም ቢሉ፡፡

አገርና መዝሙር

የገጣሚውን ሥራዎች በሚገባ የሚያውቁት አቶ በረከት በመጽሐፉ ምርቃት ስነ ስርዓት ወቅት ስለ መዝሙሮቹ ሲናገሩ ‹‹እኛ ትግሉ ውስጥ የነበርን ሰዎች ከንድፈ ሀሳባዊ ስራዎቻችን በማይተናነስ ደረጃ ክብር የምንሰጣቸው›› ናቸው በማለት ያሞካሿቸው ሲሆን ገጣሚውንም ‹‹ያላንተ ግጥሞችና ያላንተ መዝሙሮች እዚህ ደረጃ አንደርስም ነበር›› ሲሉ አመስግነዋል፡፡

እንዳያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ፣

ታጋይ የሕዝብ ልጅ በደሙ በላቡ፣

ደማቅ ታሪክ ፃፈ፡፡

ይህቺን ዜማ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚያ ወቅት የነበረ ሰው ብቻ ሳይሆን የትኛው ታጋይ፤ የትኛው የሕዝብ ልጅ ምን ዓይነት ደማቅ ታሪክ እንደጻፈ የማያውቁ ልጆችና ታዳጊዎች ጭምር ለዚህ ዜማ ባይተዋር አይደሉም፡፡ ይንን ግጥም ከማያውቁ ሰዎች ብዛት የዚህ ግጥም ጸሐፊ ህላዌ መሆኑን የማያውቁ ይበዛሉ፡፡ ገጣሚው ግን ግጥም መጻፍ ብቻም ሳይሆን ዜማ መድረስና የሙዚቃ ቅንብር ላይ ጭምር የሚሳተፍ ነው፡፡

ሌላኛው ተወዳጅ መዝሙሩ ‹‹ያልተንበ ረከክነው›› ለመላው ታጋይ ይደርስ ዘንድ በቴፕ ሲቀረጽ የነበረውን ሁኔታ ህላዌ እንዲህ ይገልጸዋል፡ ‹‹በቀረጻ ሥራ ላይ የዋሉ ሁለት ቴፕ ሪከርደሮች ነበሩ፡፡ ሦስቱ ታጋዮች መጀመሪያ በድምጻችን እየዘመርን በቴፕ ተቀረጽን፡፡ ቀጥለንም የቀረጽነውን ድምጻችንን በቴፕ እየተከተልን (እያዳመጥን)፣ ሀርሞኒካዎቹን ኦስማንና ታምራት እየተጫወቱና እኔ ጠረጴዛውን እንደ ከበሮ እዬደቃሁ ሁለቱንም በሌላ ሁለተኛ ቴፕ ቀረጽነው፡፡ አቀናበርነው ይባል ይሆን?››

የዚህ መዝሙር ግጥም ጠንካራ ነው፡፡ እንኳንስ ዜማ ወጥቶለትና በሕበረ ዝማሬ ተቀንቅኖ እንዲሁ እንደግጥም ሲነበብ ራሱ ልብ ውስጥ የሚቀር ነገር አለው፡፡ ትግል ሜዳ ያልገባነውን ሁሉ የሚያጀግን ኃይል አለው፡፡ ለቆምንለት ዓላማ በፅናት እንድንታገል የሚያበረታ ወኔም ይሰጣል፡፡

ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው

ነገ እልፍ እንሆናለን ታሪክ ምስክር ነው

ይህንን መዝሙር ሲሰሙ ልዩ ስሜት ከሚሰማቸው ሰዎች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንዱ ነበሩ፡፡ አቶ መለስ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ‹‹…ከግጥሞቹና መዝሙሮቹ ሁሉ እስከ አሁንም ስሰማ ትንሽ እንደ ኤሌክትሪክ ሾክ ዓይነት ነገር የሚሰማኝ ያልተንበረከክነው በሚለው መዝሙር ነው፤ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር በማያያዝ ሲታይ ያልተንበረከክነው የሚለው ግጥም የያኔውን ኢህዴን ከምንም በላይ የሚገልጽ ነው›› ብለው ነበር፡፡

የህላዌ ግጥሞችና መዝሙሮች እንደ ኤሌክትሪ ንዝረት የመሰለ ስሜት የሚረጩት ለታጋዩ ብቻ አይደለም፡፡ ግጥሞቹ ከዜማዎቻቸው ጋር ያላቸው ውህደት ውብ መሆን ገና ‹‹ክፉና ደጉን በማይለዩ›› ሕጻናት ጭምር እንዲዘመሩ አስችሏቸዋል፡፡ በተለይ ከዚህ ጋር ተያይዞ ህላዌ ልዩ ትውስታ አለው፡፡ ‹‹በርቺ ባይሽ በረከተ›› የተባለው መዝሙሩን ከእናቷ ጋር የእርዳታ እህል ለመቀበል የሄደች ሕጻን ስታንጎራጉር የነበረበትን አጋጣሚ እንዲህ ያስታውሳል፡፡

‹‹1977 ድርቅ ወቅት የእርዳታ እህል ፍለጋ ወደ ኮረም የሄዱ የዋግ ኸምራ አርሶ አደሮች የእርዳታውን እህል ከመውሰዳቸው በፊት የኢህዴን ደጋፊዎችና አባላት መሆን ያለመሆናቸውን ጭምር የደርግ ካድሬዎች አስቀድመው ያጣሩ ነበር፡፡ አንዲት እናት በእርዳታ አከፋፋዮች ስለዚሁ ጉዳይ ስትጠየቅ ኮረም የሄደችው እርዳታ ለመጠየቅ እንጂ ሌላ የድርጅት ተልዕኮ ይዛ ያለመሆኑን ለማስረዳት እየሞከረች እያለ ይዛት የሄደቻት እግረ-ተከል ሕጻን በኮልታፋ አንደበቷ ይሄንን ዘፈን ስታንጎራጉር ታጣቂዎቹና ካድሬዎቹ ሰምተው ኖሮ፤ አንቺ የወንበዴ ተባባሪ መሆንሽን ብትደብቂም ልጅሽ አጋለጥሽ በማለት እናትየዋን እስር ቤት አስገቧት››፡፡ በእርግጥ በሕጻኗ እናት ላይ የደረሰው ነገር አሳዛኝ ቢሆንም ልጅቷ ትርጉሙን እንኳ ሳታውቀው መዝሙሩን እድታዜም ያደረጋት የዜማው ጥንካሬ መሆኑን እናያለን፡፡

ህላዌ ገጣሚ ብቻ አይደለም፡፡ ዜማ ደራሲም ጭምር እንጂ፡፡ ህላዌ ዜማ ደራሲ ብቻም አልነበረም፡፡ ድምጻዊም ጭምር እጂ፡፡ የሕላዌ ሌላኛው ተወዳጅ መዝሙር ‹‹እንዳያልፉት የለም›› ዜማው በእያሱ በርኸ ከተሠራ በኋላ በ1ኛው ድርጅታዊ ጉባዔም ላይ በክራር ታጅበው ህላዌና መዝሙር በጋራ አንጎራጉረውታል፡፡ ‹‹ደማቅ ታሪክ ጻፈ ዛሬ ከኢህዴን/ብአዴን ታጋዮችም አልፎ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ተወዳጅነትን ያተረፈ ጆሮ ገብ ዘፈን ለመሆን በቅቷል›› ይላል ገጣሚው፡፡

ታጋይ ሦት ነገሮችን ይወዳል፡፡ ከእነኚህ አንዱ ስነ-ጥበብ ነው፡፡ ከስነ-ጥበብ ዘርፎች አንዱ የሆነው ሙዚቃ ሲሆን ያለ ሙዚቃ መሣሪያ ሙዚቃ ማራኪ አይሆንም፡፡ ታጋይ ስነ ጥበብን መውደዱ ያለ ነገር አይደለም፡፡ ይዞት የተነሳውን ዓላማ ለታጋዩ ለማስታወስና ለሚታገልለት ሕዝብ ጭምር ለማስረዳት ከጥበብ የተሻለ መንገድ እንደሌለ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም በሙዚቃ መልዕክት ይተላለፋል፡፡ በሙዚቃ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በሙዚቃ ድል ይበሰራል፡፡ ገጣሚውም ይሄንን የሙዚቃ ውለታ የረሳ አይደለም፡፡ ‹‹ለአዲሱ ቀን ይበቃሉ›› የሚል ግጥሙ በትግል ወቅት በግምት የማይቀመጥ ግልጋሎት የሰጡ የሙዚቃ መሣሪያዎች ከድል አድራጊዎች እኩል ነገን እንደሚያዩ በስንኝ ያስቀመጠበት ማስታወሻ ነው፡፡ እያንዳንዱን መሣሪያ ሲጠራም ዓላማቸውን ሳይዘነጋ ነው፡፡

የበርኸኞች ክራራችን፣

የሕዝብ እረኞች ዋሽንታችን፣

መምህራኑ ማሲንቆአችን፣

ድል አብሳሪው ከበሮአችን…

መዝሙርና ስዕል

በዋነናት የትግል ዘመን ግጥች ከመያዙም በላይ ታሪክና ጥበብን ከሌሎች የግጥም መድብሎች ለየት የሚያደርጉት በየመሀሉ የገቡት ውብ ስዕሎች ናቸው፡፡ በጥቂት የአማርኛ የግጥም መጽሐፍት ውስጥ የጥቁርና ነጭ ቀለም ስዕሎች የሚገኙ ሲሆን በታሪክና ጥበብ ውስጥ ግን በባለቀለም ሕትመት የተዘጋጁ ስዕሎች ይገኛሉ፡፡ ስዕሎች ከግጥሞቹ ጋር ተመሳሳይ ርዕስ አላቸው፡፡ ይህ የሆነው በአጋጣሚ አይደለም፡፡ ገጣሚው የተወሰኑ ሰዓሊዎችን መርጦ ግጥሞቹን ያነብላቸዋል፡፡ ግጥሙ የፈጠረባቸውን ስሜት ሰዓሊያኑ በቀለም ያስቀምጡታል፡፡ ግጥምና ስዕል ውህደት ፈጥረው መሳ ለመሳ መቀመጣቸው ልዩ ስሜት የሚፈጥር ሲሆን ግጥሞቹም ሆነ ስዕሎቹ ራሳቸውን ችለው ሲቆሙም ትርጉም የሚሰጡ የጥበብ ሥራዎች ናቸው፡፡ ገጣሚው ለአገራች ስነጥበብ ያበረከተው አስተዋፅዖ ስንኞችን ብቻ ሳይሆን ግጥሞቹም ሰዓሊያንን በማነሳሳት ተጨማሪ የጥበብ ሥራዎች እንዲፈጠሩ ምከንያት በመሆኑም ሊመሰገን ይገባዋል፡፡

ለማጠቃለል ያህል የህላዌ ግጥሞች ታጋዮችን ለማበርታት ከተቋጠሩ የትግል ዘመን ስንኞች በላይ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ይዘታቸውን ወደ ጎን ትተን እንደ ግጥም እንያቸው ብንል እንኳ ህላዌ ውብ የቃላት አጠቃቀም ያሉት የቤት አመታቱም ግሩም የሆነ ገጣሚ ነው፡፡ ግጥሞቹም ታሪክን ከመንገር በላይ፤ ታጋዩን ለማበረታታት ጥቅም ላይ ከመዋላቸውም በላይ ለአሁኑ ትውልድ ጭምር መነሳሳትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጠንካራ ስንኞች ናቸው፡፡ ‹‹ታሪክና ጥበብ››ም እንደ ርዕሱ ሁሉ ታሪክና ጥበብን በአንድ ላይ ሰፍቶ ‹‹እነሆ›› የሚል ማለፊያ የግጥም መድብል ነው፡፡ ገጣሚው ከሞት አፍ ያመለጠባት ያቺ ዕለት ለእኛም ጭምር የመልካም ዕድል ቀን ነበረች፡፡ ምክንያቱም ዕድለኛ ሳይሆን ቢቀር ኖሮ እነኚህን ሁሉ ውብ ስንኞችና ጆሮ ገብ ዜማዎች አናገኝም ነበርና፡፡

ፀሃፊ ሙሉጌታ አለባቸው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137305
TodayToday116
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week16
This_MonthThis_Month3387
All_DaysAll_Days137305

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።