ከሞት መንጋጋ ያመለጡ ስንኞች Featured

27 Aug 2015

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት አቶ ህላዌ ዮሴፍ በቅርቡ ‹‹ታሪካና ጥበብ›› የተሰኘ ዳጎስ ያለ የግጥም መድብል አሳትመዋል፡፡ ይሄንን ጉዳይ አስመልክቶ ቃለ መጠይቅ ልናደርግላቸው ብናስብም እሳቸው በአሁኑ ሰዓት የሚገኙት እስራኤል አገር በመሆኑ በአካል ተገናኝተን ልንጨዋወት አልቻልንም፡፡ ሆኖም ጥያቄዎቻችንን በኢሜይል ልከንላቸው በጽሑፍ የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ዘመን፡ ግንቦት 20/1983 ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ እርስዎ ጐንደር አካባቢ የተሰጠዎትን ሃላፊነት እየተወጡ ነበር፡፡ ያቺን ቀን እንዴት ያስታውሷታል?

አምባሳደር ህላዌ፡ እርግጥ ነው፣ ኢህአዴግ አዲስ አበባ የገባ እለት እኔ ጐንደር ነበርኩኝ፡፡ ይህንኑ በ"ታሪክና ጥበብ" ውስጥ "የምስራች ይበሉሽ" በሚለው ግጥሜ ማብራሪያ ላይ ገልጨዋለሁኝ፡፡ በእለቱ የተሰማኝ ስሜት እጅግ የተደበላለቀ ስሜት ነው የነበረው፡፡ በአንድ በኩል ከፍተኛ ደስታ ይሰማኝ ነበር፡፡ ድሉ ታላቅ ድል ነው የነበረው፡፡ አይገፋም፣ አይደፋም የተባለው ግዙፉ፣ ጨካኙና ሃገራችንን 50 ዓመታት ወደ ኋላ የመለሳት ደርግ ሲወድቅ ከማየት የበለጠ ደስታ የሚሰጥ ነገር አልነበረም፡፡ ደርግ በመጨረሻ የጭካኔ እርምጃዎቹ የሃዘን ጨርቅ ያለበሳት ጐንደር በደርግ ውድቀት መፈንደቅ ስትጀምር ስመለከት እጅግ ተደሰትኩ፡፡ ተወልጄ ያደግሁባት ከተማ አዲስ አበባ ከፋሺስታዊ አገዛዝ ነፃ መውጣቷም ለኔ የተለየ ትርጉም ነበረው፡፡ የደርግ ውድቀት ብዙዎቻችን ካለፍን በኋላ ሊሆን ይችላል ብለን እናስብ ነበር እንጂ በህይወት እያለን ይገጥመናል ብለን የማንገምተው ፍፃሜ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሴቶች ምሁራን፣ ሠራተኞችና አርሶ አደር ታጋዩች ይህንን ቀን ለማምጣት ምትክ የማይገኝላትን ህይወታቸውን ገብረዋል፣ ከአፈር በታች ውለዋል፣ እናም ለድሉ የተከፈለውን ውድ ዋጋ ሳስበው ደግሞ ጥልቅ የሀዘን ስሜት ይሰማኝ ነበር፡፡ ለዚህ ነው ስሜቴ ድብልቅ ነበር ያልኩት፡፡

ዘመን፡ በትግሉ ውስጥና ከዚያም በኋላ ግጥም ለመፃፍ ምን ያነሳሳዎታል ? በወቅቱ ከምድብ ስራዎስ ጋር እንዴት ያጣጥሙት ነበር? ጊዜስ አይወስድብዎትም ነበር?

አምባሳደር ህላዌ፡ ከትግሉ ውጭ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የተፃፉት ግጥሞች በቁጥራቸው አነስተኛ (ጥቂት) በመሆናቸው ብዙ መናገር የሚቻለው ከትግሉ ጋር ስለተያያዙት ግጥሞች ነው፡፡ ግጥሞቹ በምን ሁኔታ እንዴትና መቼ እፅፋቸው እንደነበር ያው"ታሪክና ጥበብን" ያነበበ ሊረዳው ይችላል፡፡ እዚያ ላይ በአግባቡ የገለፅኩት ይመስለኛል፡፡ በህዝቡ ላይ ይደርስ የነበረው በደል፣ የግፍና የጭቆና ስርዓትን ከትግል ውጪ ማቸነፍ የማይቻል መሆኑ፣ ለዚህም የሚከፈል መስዋእትነት፣ ድል ሁሉ ግጥም ለመፃፍ የማያነሳሱኝ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ እርግጥ ነው ግጥም መፃፍም ሆነ ከሱ ጋር በተያያዙ የስራ መስኮች ላይ በመደበኛነት የተመደብኩ አልነበርኩም፡፡ ምድቤ ተዋጊ ሰራዊት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በፖለቲካ ክፍል፣ በህዝብ አደራጅነትና በአመራር ስራዎች አካባቢ ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የዝንባሌና የፍላጐት ጉዳይ ነው የነበረው፡፡ በተሰማህና በተመቸህ ጊዜ ታደርገዋለህ፡፡ ደግሞ እኮ በ36 ዓመታት ውስጥ 50 ምናምን ግጥም ብዙ አይባልም፡፡ ስለዚህ ይበልጥ ያበረታንም ስራችንንም ይደግፍ ነበር እንጂ ብዙ አይጫነውም ነበር፡፡

ዘመን፡ ‹‹ታሪክና ጥበብ›› ደስ የሚል ርዕስ ነው፡፡ ለእርስዎ ታሪክና ጥበብ ያላቸው ግንኙነት ምን ይመስላል? አንዱ በሌላቸው ላይ የሚያሳርፉትን ተፅዕኖስ እንዴት ያዩታል?

አምባሳደር ህላዌ፡ ታሪክ የሰው ልጆች ያለፉበት የትግልና የድል፣ የእድገትና የውድቀት፣ የፈተናና የደስታ ድርጊቶችና ፍፃሜዎች ውጤት ነው፡፡ ስነ-ጥበብም የዚህ ነፀብራቅ ነው፡፡ አንዳንዶች ስነ-ጥበብን ከሁነቶችና ከድርጊቶች ነጥለው ፍፁም በህሊናችን ውስጥ ብቻ ያለና ከነባራዊው አለም የተለየ ንጥል ነገር አድርገው የሚገነዘቡበት እይታ ለኔ ብዙ አይጥመኝም፡፡ ስለዚህ በኔ ግምት ስነ-ጥበብ በነባራዊው አለም እውነታዎች ላይ ተመርኩዛ የምትዳብርና የምታብብ ተመልሳም ነባራዊው ሁኔታ እንዲለወጥ እንዲዳብር የራሷን ተፅእኖ የምታሳደር ነች፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መሃከል መደጋገፍና አንዱ በሌላው ላይ ተፅእኖ ማሳረፋቸው የማይቀርና አብሮ የሚኖር አድርጌ እረዳዋለሁ፡፡

ዘመን፡ ‹‹ታሪክና ጥበብ›› በብሔራዊ ቴአትር ሲመረቅ አቶ በረከት ስመዖን አንድ የፍቅር ግጥም አንብበው ነበር፡፡ እርስዎ ተርጉመው ያቀረቡት ‹‹ጠብቂኝ›› የተሰኘ ግጥም ተወዳጅ እንደነበረም በመጽሐፍዎ ነግረውናል፡፡ እስቲ በጠቅላላ በትግል ወቅት ፍቅርን አስመልክቶ የነበረው የስነ ግጥም እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር? የእርስዎስ አጋጣሚ?

አምባሳደር ህላዌ፡ በእኔ አስተያየት ለህዝቡ ትግል ድል አድራጊነት በቁርጠኝነት ይታገል የነበረው ታጋይ ህይወቱን መስዋዕት ለማድረግ ፍፁም ስስት አልባ የነበረው ለህዝቡና ለአላማው ጥልቅ ፍቅር ስለነበረው ነው፡፡ ለትግል ጓዱም ሆነ ለፍቅር ጓደኛ የነበረው ፍቅርም ልባዊ ነበር፡፡ በእርግጥ በትግሉ ወቅት ለፍቅር ጓደኛ በግጥም መልክ በብዙ መጠን አይፃፍም ነበር፡፡ ምናልባት ከምናውቃቸው ውጪ አንዳንዶች የያዟቸው ስንኞች ሊኖሩ ይችሉሉ፡፡ ሆኖም ግን ስለ ፍቅር ጓደኛ ከተፃፈም አሁን (የግለሰቧን) የግለሰቡን ውበት ከእግር ጥፍርዋ እስከ ራስ ጠጉርዋ በማሞካሸት ወይም ያላአንቺ ያላንተ አይሆንልኝም፣ እሞታለሁ በማለት ሳይሆን በተወሰነ ደረጃ ትግሉንና አላማን ቅመምና አማካይ በማድረግ ነበር፡፡ በአህዴን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኢህአፓ ውስጥም ከሚታወሱኝ ግጥሞች መካከል ለምሳሌ ከበደ ደስታ "አልተለየሽኝም" በሚል ርዕስ የፃፈው ግጥም ሚስቱ እርሱ ገጠር ለትግሉ ከወጣ በኋላ በደርግ ካድሬዎች ምን ያህል ትሰቃይ እንደነበር፣ ህፃን ልጁ የአርናርኪስት ልጅ እየተባለ ምን ያህል ይሳቀቅ እንደነበር ጭምር ለእነርሱ ካለው ፍቅር ጋር እጅግ ከሽኖ የፃፈው ግጥም ነበር፡፡ መዝገብነሽ ተብላ የምትታወቀው ታጋይ በከተማ መስዋዕት ስለሆነ ፍቅረኛዋ "በእንባዬ ውስጥ ተቀመጥ" በሚል ርዕስ የፃፈችው ግጥምም የዚሁ ዓይነት ባህርይ ነበረው፡፡ እኔን በሚመለከት እንደተገፀው እኛ ጋር (በኢህዴን) ትዳር የተፈቀደው በ1980 ነው፡፡ ትንሽ ቀደም ብለን በስሱ ጀመርነውና ሲፈቀድ ቀጠልንበት፣ ሌላ የለውም፡፡ ስለዚህ የሚፃፈው ከትግሉ ጋር በተያያዘና በተመጠነ መጠን እንጂ እንዳው በሰፊው የሚፃፍበት ጉዳይ አልነበረም፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት እንግዲህ አንድም ሁለትም ስንኝ እየቋጠረ በየሚስጥር ኪሱ የደበቀ ሊኖር ይችላል፡፡

ዘመን፡ ለድላይ (ስመኝ ምናለ) ‹‹እኔም እንዳንቺ ድል ላይ ልቁም›› የሚል ግጥም ጽፈውላታል፡፡ የድላይ ታሪክ ‹‹የአሲምባ ፍቅር›› በተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ በሰፊው ታትቷል፡፡ እርስዎ የሚያስታውሷቸው ሌሎች ታሪካቸው በሰፊው ያልተነገረ ግን በርካታ ጀብዱ የሠሩ ጀግኖች ይኖሩ ይሆን?

አምባሳደር ህላዌ፡ አሉ እንጂ፡፡ ታሪካቸው ከተፃፈላቸው ጀግኖች ያልተፃፈላቸው የሚበዙ ናቸው፡፡ በከተሞች ደርግን በመቃወም በተደረገው ትግል ውስጥ አስደናቂ ታሪክ የፈፀሙ በርካቶች አሉ፡፡ በገጠሩ ትጥቅ ትግል በኢህአፓ/ሠ ውስጥ ይሁን በኢህዴን/ኢህአዴግ ውስጥም ሆነ በሌሎች እህት ድርጅቶች ውስጥ ታሪካቸው ገና ያልተፃፈ በርካታ ጀግኖች ወንዶች ሴቶች አርሶ አደሮች አሉ፡፡

እኔ በአካል የማላውቃቸው ትጥቅ ትግሉን ከኔ ቀድመው የተቀላቀሉ ታጋዮች የሚያውቋቸው ጀግኖች አሉ፡፡ እነዚህ ታጋዮች ስለነዚህ ምርጥ ጀግኖች ሲያወሩ ተመስጬ ያዳመጥኩባቸውንም ሁኔታዎች አስታውሳለሁ፡፡ ለማንኛውም ይህ ጉዳይ ብዙ ትጋትና ሃላፊነት የሚጠይቅ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ማንኛችንም እየደከምንና ወደ አፈሩ እየቀረብን እንጂ እየጠነከርን አንሄድምና ሁኔታዎቹ ሳይረሱ የሰውም ትውስታ (Memory) ሳይደበዝዝ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በተፃፉትም ላይ አንዳንድ አነጋጋሪ (Controversial) ጉዳዮች ካሉም እነርሱን ማጥራት እኒያ ንፁሃን ታጋዮች በተገቢው ሁኔታ እንዲዘከሩ ለማድረግ ያግዛል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡

ዘመን፡ ከግጥም ስብስቦች ውጪ ለወደፊት የሚያስቡት ጽሑፍ የለም?

አምባሳደር ህላዌ፡ ይኖራል፣ በመሃል የሚያደናቅፍ ነገር ካላጋጠመ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ የሚያስቡ ሌሎች እንዳሉም አውቃለሁ፡፡ ለማንኛውም መበርታት የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡

ዘመን፡ የእርስዎ ግጥሞች፤ ከብአዴንም ውጭ ተወዳጅ የሆኑ ዜማዎች ሆነው በሕዝብ ይዘመራሉ፡፡ በተለይም ‹‹እንዳያልፉት የለም›› እና ‹‹ያልተንበረከክነው›› ዘወትር ይጠቀሳሉ፡፡ ክጥሞችዎ ውስጥም 23 የሚሆኑት ዜማ ተሰርቶላቸዋል፡፡ ግጥምና ዜማ በሕብረተሰብ ውስጥ ስለሚኖራቸው ፋይዳ ምን ይላሉ?

አምባሳደር ህላዌ፡ ስለ እዚህ ጉዳይ በንድፈ ሃሳብ ወይም በረቂቁ ከመናገር አሁን በሃገራችን ይበልጥ እየሰፋና እያደገ የሚገኘውን የሙዚቃና የስነ-ፅሁፍ ሁኔታ በማየት መመስከር ይቻል ይመስለኛል፡፡ ስነ-ጥበቡ ለማህበረሰባችንና ለሀገራችን ልማትና እድገት ለህዝቦቻችን አንድነት እየተጫወተ የሚገኘው ሚና በደንብ ደምቆ መታየት የጀመረ ይመስለኛል፡፡ ዜማንና ግጥምን በአጠቃላይም ስነ-ጥበብን ስእልንና ቅርፃቅርፅንና ሌሎቹንም የስነ-ጥበብ ዘርፎች ከልማቱ ጋር አቆራኝቶ የማይራመድ ማህበረሰብ እድገቱ ምሉዕ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ያሉትን እየጠበቀ እያዳበረ አዳዲስ ፈጠራዎች እያከለ የማይሄድ ማህበረሰብም እድገቱ አዝጋሚና የሚደበትም (Depressed የሚሆን) ማህበረሰብም ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ አሁን ከምናደርገው በላይ ለመንፈሳዊ ሃብቶቻችን ልማት መትጋት ያለብን ይመስለኛል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137309
TodayToday120
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week20
This_MonthThis_Month3391
All_DaysAll_Days137309

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።