ገፅታዋን የቀየረች አገር «ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎች መጠለያ ትሆናለች» - አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ Featured

03 Sep 2015

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ ሀገሪቱም በፍጥነት እንድታድግ በብርቱ ከሚመኙ ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን አንዱ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ናቸው፡፡ አቶ ዘመዴነህ ለኢትዮጵያ መልካምን በመመኝት ብቻ ሳይሆን ከዛሬ ዐሥራ ስድስት ዓመት በፊት ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ መጥተው በተግባር ኢንቨስት በማድረግና ከመላው ዓለም ያሉ ባለሀብቶችንና የኢትዮጵያን ዲያስፖራ በማግባባት በኢትዮጵያ ሀብታቸውን ለልማት በማዋል እነርሱም እንዲጠቀሙ በማድረግ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ ዘመዴነህ ለታዋቂ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት፣ የ2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕድገት ሮድ ማፕ ዝግጅት ላይ አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ በፋይናነስ፣ በማኒፋክቸሪንግ፣ በቴሌኮም፣ በዓየር መንገድ አገልግሎት ላይ ደንበኞችን በማማከር ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው፣ የኤርነስት ኤንድ ያንግ የኢኮኖሚና ግብይት ጉዳዮች አማካሪ ድርጅት ማኔጂንግ ፓርትነር ናቸው፡፡ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ከፍተኛ ባለሙያና እውቀትን ለጥቅምና ለሀገር ግንባታ በማዋል ላይ ከፍተኛ እምነት ያላቸው ሲሆኑ በአሜሪካን ሀገር አድገው በአሜሪካን ሀገር ተምረው አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ሀገሮች ተዘዋውረው በሙያቸው ሲሠሩ የኖሩ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ በትውልድ ሀገራቸው አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከልማት ኃይሎች ጋር ሁሉ ተሰልፈው እየሠሩ ነው፡፡ እኛም ይህንኑ ታሳቢ አድርገን በወሳኝ የሀገራችን የልማትና የመልካም ገጽታ ዕድገት ላይ ያላቸውን አስተያየት፣ የእርሳቸውንም አስተዋጽኦ በተመለከተ በዚህ ዕትማችን ሠፊ ቃለምልልስ አድርገናል፡፡

ዘመን፦ የኢትዮጵያ የመልካም ገጽታ ሁኔታ በአዎንታ እየተለወጠ መምጣቱን ብዙዎች ያነሳሉ፤ በእርግጥ አሁን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምትታይበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ የሆነበት ዕድል አለ? ይህ ከሆነ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች ምን ነበሩ?

አቶ ዘመዴነህ፦ ገጽታ የሚገለጸው በሁለት መንገድ ነው፤ አንዱ በድርጊት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እያደገ መምጣቱ ከምንም በላይ የገጽታ ለውጥን የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄንን ስል ምሳሌ ላነሳ እችላለሁ፡፡ የዓለም ባንክና አይ.ኤም.ኤፍ. በየጊዜው የሚያወጧቸው ጥናቶች አሉ፡፡ በተለይ ዓለም ባንክ በቅርቡ ያወጣው ጥናት እንኳን ምን ይላል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ በዐሥር ነጥብ ሦስት ወይም ነጥብ አራት በአማካኝ አድጓል ይላል፡፡ ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? አፍሪካ ውስጥ ነዳጅ ከሚያመርቱ ሀገሮች ውጪ በፍጥነት በማደግ በአንደኛ ደረጃ ላይ ያለ ነው ተብሏል፡፡ ይሄ ምንም ትርፍ መግለጫ አያስፈልገውም፡፡

እኛም ብዙ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ላይ እየተገኘን ነው፤ እንደተናጋሪ ሆነን በመድረኮች ተሳታፊዎች እየሆንን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ስለኢትዮጵያ ዕድገት ይህቺን ከጠቀስንላቸው በኋላ ሁለተኛ አንቀጽ አያስፈልገውም፡፡ ከዚያ በኋላ ውይይት ነው እንጂ የእኛ ማብራሪያ አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህ በድርጊት ማሳየቱ አንደኛ ኢትዮጵያ እየተቀየረች ነው የሚለውን ማሳየት ያስችላል፡፡

ይህ ሲባል ግን ማየት ያለብን ርዕሱን ብቻ አይደለም፤ ዝርዝር አለው፤ የዐሥር ነጥብ ሦስትና አራት ዕድገት ምን አምጥቷል? የሚለው ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዕድገት ሁሉን ያካተተ የመሆኑ ነገር ነው፡፡ የመጀመሪያው የገቢ መመጣጠን ጊኒ ኮፊሺየንት የሚባለው ማመላከቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ውስጥ እጅግ ተመራጭ የሆነ ጊኒ ኮፊሺየንት የገቢ አለመራራቅ ሪከርድ አላት፡፡ በሀብታምና በደሃው መካከል ያለው ርቀት ሚዛናዊ የሆነበት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ለኢንቨስተሮችም የበለጠ በራስ መተማመን ይሰጣቸዋል፡፡ ምክንያቱም ቀጣይነት ያለው ዕድገት በመሆኑ ነው፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ቀጣይነት ያለው ልማት ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ ለኢንቨስተሩም ይሄ የዕድገት ተከታታይነት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ኢንቨስተር ሀብቱን በአንድ ሀገር የሚያፈሰው ለረጅም ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ቀጣይነት ያለው ልማት መተማመን ይሰጣል፡፡ ስለዚህ የሕዝቡ ተሳታፊነት የሚታይበት መሆኑንም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡

ሌላው ጠቋሚ ደግሞ አማካኝ የዕድሜ ጣሪያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዜጎች አማካይ የዕድሜ ጣሪያ ከሌሎች ተወዳዳሪ የአፍሪካ ሀገሮች አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ የ2012 ቢወሰድ የኢትዮጵያ 62 ዓመት ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ 55 ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ደቡብ አፍሪካ በአህጉሩ የተሻለች ሀገር ነች፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ የዕድሜ ጣሪያ የተሻለ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ በዝርዝር ሲታይ አንዱ ማመላከቻ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያ የትምህርት ተደራሽነት እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ የትምህርት ለሁሉም ተደራሽነት ከዘጠና በመቶ በላይ ነው፡፡ ኮሌጆችንና ዩኒቨርሲቲዎችንም ያየን እንደሆነ የዛሬ 16 እና 17 ዓመት አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ 32 አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ያየሁት ዕቅድ ደግሞ ከ40 በላይ ይኖረናል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ትምህርት ትልቅ ዕድል ሰጪ ነገር ነው፡፡ ይሄንን ስናየው ነው የሀገሪቱን መለወጥ የሚያሳየው፡፡ በዚህ ውስጥ ግን ብዙ ተግዳሮት ይኖራል፡፡ ይሁንና ባለፉት ዐሥር ዓመታት የተመዘገበው ዓይነት ዕድገት ከቀጠለ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገሮች ተርታ እገባለሁ ብላ ለያዘችው ዕቅድ ማመላከቻ ማረጋገጫ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ዘመን፦ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተዘጋጀውን ‹‹ፋይናንስ ለልማት›› ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዴት አገኙት? የተገኘው ስኬትስ እንዴት ይገመገማል?

አቶ ዘመዴነህ፦ ስኬታማ ነው ሲባል የሚታይበት ገጽታ የተለያየ ነው፡፡ አንደኛው ከተሳታፊው ቁጥር አንጻር ስናየው ነው እስከ ዐሥራ አንድ ሺ ያህል ተሳታፊ ተገኝቷል ይባላል፡፡ የተገመተው ከአምስት እስከ ሰባት ሺ ነበር፡፡ ሰባት ሺም ቢሆን በጣም ብዙ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ይሄን ያህል ሰው የማስተናገድ አቅም ያላቸው ሀገሮችም ይሁን ከተሞች ከሁለት ከሦስት አያልፉም፡፡ ስለዚህ ይሄን ያህል ሰው መስተናገድ መቻሉ እጅግ በጣም ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ይሄን ያህል ሰው ለአራት ለአምስት ቀናት በሰላም ተስተናግዶ በሁሉም ሆቴሎች ተስተናግዶ መሄዱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይህ ከሰላምና ከደኅንነት አንጻር ሲታይ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ተጋባዥ ሆነው ከተገኙት እንግዶች ማንነት አንጻር ነው፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአይ.ኤም.ኤፍና በዓለም ባንክ በመሳሰሉት ውስጥ ያሉ እጅግ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች መምጣታቸው ሀገሪቱን የት ደረጃ ላይ ነች የሚለውን ለማሳየት ይረዳል፡፡ ስለዚህ ይህ ስኬት ነው፡፡ ለኢኮኖሚው ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ እንግዲህ አዲስ አበባ አምስት ሺ ሁለት መቶ ያህል ማስተናገድ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አሉ ነው የሚባለው ሌላው ደግሞ እንዴት እንደተስተናገደ አላውቅም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ሲደረግ ሆቴል ጠፍቶ የሚመጡት ልዑካን በየሰው ቤት የሚያድሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን ሰባት ሺ ስምንት ሺ ሰው ደረጃቸውን በጠበቁ በሆቴል ደረጃ መስተናገድ መቻሉ ቀላል ለውጥ አይደለም፡፡ እንግዲህ ከሆቴሎቹ፣ ከስጦታና ማስታወሻ መሸጫዎችን የመሳሰሉት የሚያገኙትን ገቢ ስናስብ ኢትዮጵያ በዚህ የስብሰባ ጊዜያት በብዙ ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዓየር መንገድም ብዙ ሺ ሰው አስተናግዷል፡፡ ስለዚህ መካሄዱ ለኢኮኖሚውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ማለት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የኢትዮጵያን ገጽታ ከመለወጥ አንጻርም ከፍተኛ ጥቅምም አለው፡፡ በፊት ከምትታወቅበት ገጽታ አሁን ተቀይራ በዚህ ደረጃ ላይ ነች ብሎ ማሳየቱ ራሷን በነፃ እንዳስተዋወቀች የሚታሰብ ነው፡፡ እዚህ የመጡ በርካታ ሚዲያዎች አሉ፤ እኔን እንኳን ያነጋገሩኝ ብዙ ሚዲያዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ከሌላጋ መጥተው ስለኢትዮጵያ መዘገባቸው ነፃ የማስተዋወቅ ሥራ ነው የሠሩልን ማለት ይቻላል፡፡

ዘመን፦ ይህ በአዎንታ እየተለወጠ የመጣው መልካም ገጽታ ሀገራችን ከሌሎች ጋር በየመስኩ ባላት የሁለትዮሽና ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች ላይ ያሳደረው በጎ ተጽዕኖስ እንዴት ይታያል?

አቶ ዘመዴነህ፦ አንድ የወጣ ጥናት አለ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ አምስት ወሳኝ እጅግ ትኩረት የሚሰጣቸው ሀገራት ተብለው ከተጠቀሱት ከግብፅ ደቡብ አፍሪካና ናጄሪያ ጋር የተጠቀሰችው አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ እነርሱ ያዩት መቼም አንድ ሀገር በሁሉም ነገር ታድጋለች ብለው አይደለም፤ ነገር ግን የተለዩ አስተዋጽኦዎችም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሀገር ለአካባቢው ያላት አስተዋጽኦ ሊታይም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ በሰላምና በጸጥታ ለምሥራቅ አፍሪካ አካባቢና ለመላው አፍሪካ የምታበረክተውን አስተዋጽኦ ያያሉ፡፡ ብዙ ወታደሮችን ለአፍሪካ ሕብረትም ለተባበሩት መንግሥታትም ትሰጣለች፡፡ ይሄ ታዲያ ትልቅ ትኩረት ያሰጣል፡፡ ሁለተኛው ነገር በዚህችው በአካባቢያችን እንኳን ስናይ ጎረቤቶቻችን የተወሰኑት ያልተረጋጉ ናቸው፡፡ በምዕራብ ደቡብ ሱዳን አለ፤ በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ በምሥራቅ የታወቀ ነው፤ ሶማሊያ አለ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓይነት አካባቢ ውስጥ የኢትዮጵያ ሰላም መሆንና ማደግ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው፡፡ መታየት ያለበት ኢትዮጵያ ከዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ሀገር ነች። ትልቅ ሀገር ነች፡፡ በየዓመቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕዝብ አዲስ ይጨመራል፡፡ ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? ጠቅላላ ህዝባቸው እኮ 2 ሚሊዮን የማይደርስ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት አሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ደረጃ ሕዝቧ የሚያድግ ሀገር ሰላም መሆኗ ቀላል ትኩረት አይስብም፡፡

ሌላው ጠቃሚ የሆነው ነገር የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ እዚህ ነው ያለው፡፡ በሳምንት ውስጥ ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት የአፍሪካ መሪ አዲስ አበባ ውስጥ አለ፡፡ ይህ ለግንኙነቶች መዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በዚህም ላይ ኢትዮጵያ የኔፓድን መሪነት ወስዳለች፡፡ ይሄም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይህ ሁሉ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እዚህ መሆኑ ያስገኘው ነው፡፡ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ የታወከች ሀገር ብትሆን ዕድገት ባታሳይ ኖሮ በፖለቲካም በምንም ይሁን የሚኖራት ተጽዕኖ ደካማ ይሆን ነበር፡፡ ይንቁን ነበር፡፡ የኢኮኖሚውን ማደግ ከሌላው ነጥሎ ማየት አይቻለም፡፡ ከአሜሪካኖች የምንማረው ነገር ምንድነው? እንዴት አድርገው ነው ሶቪየትን ያፈረሱት? ሶቪየቶች የተሳሳቱት በወታደራዊ ኃይል ብቻ ልዕለ ኃያል ሆነው ለዘላለም እንደሚኖሩ ማሰባቸው ነው፡፡ በዚያን ጊዜ አሜሪካኖች ፍሪጅ እንኳን መሥራት የማይችል ኢኮኖሚ እያሉ ይቀልዱባቸው ነበር፡፡ ሕዝቡ በተቸገረበት ሀገር ውስጥ ሚሳኤል ቢሠሩ ምንድነው ጥቅሙ ይሉ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ መሠረት ያለው ነገር የያዘችው እያደገች በምትሄድበት ጊዜ የሕዝቡን ኑሮ መቀየር አለባት፡፡

በኢኮኖሚ ዕድገቱ የተገኘው ጥቅም ለሌላም ለሌላም ነገሮች ተጽዕኖ ለማድረግ ሊረዳት ይችላል፡፡ ለዚህም ኢኮኖሚ ስልቱ አካባቢውንም በመለወጥ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለምሳሌ በምሥራቅ አፍሪካ ለሁሉም ሀገሮች በሚባል ደረጃ ኃይል ለመስጠት እየጣረች ነው፡፡ ኬኒያና ሩዋንዳ ፈርመዋል፡፡ ወደ ሱዳንና ጂቡቲ ቀድሞም ኤክስፖርት እየተደረገ ነው፡፡ ሄዶ ሄዶ ለግብፅም ይረዳል፡፡ ይህ ታዲያ አንደኛ በኢኮኖሚ አስተዋጽኦ አለው ግን ደግሞ በፖለቲካ ትስስርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ዘመን፦ ምናልባትም በቅርቡ ኢትዮጵያ የፕሬዚዳንት ኦባማ ተመራጭ ተጎብኚ ሀገር ለመሆን እንድትችልም ይህ አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻላል?

አቶ ዘመዴነህ፦ ይሄን በትዊተር ገጼም ላይ አስቀምጨዋለሁ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያደረጉት ጉብኝት ተገቢነት ያለው ነው፡፡ የሚገርመው ከአፍሪካ ሀገሮች መካከል አሜሪካ እጅግ ረጅም የግንኙነት ዘመን ያላት ከኢትዮጵያ ጋር ነው፡፡ ከመቶ ዓመት በላይ ከንጉሡ (ከኃይለሥላሴ) ጀምሮ ደግሞ ጠንካራ ግንኙነት ነበራት፡፡ እኔ አስታውሳለሁ በታሪክም ያለ ነው የፕሬዚዳንት ኬኔዲን የቀብር ሥነሥርዓት ላይ ተጋብዘው የተገኙ ብቸኛው አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቢያንስ ለሦስት ጊዜያት ዋይትሀውስ ተገኝተው በመሪ ደረጃ ጉብኝት ያደረጉ አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ በታላላቅ ሚዲያዎችም ሽፋን ያገኙ ነበር፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያና አሜሪካ የረጅም ጊዜ ግንኙነት አላቸው፡፡ ነገር ግን አንድም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በሥልጣን ላይ እያለ ሌላው ቀርቶ ጃንሆይም እያሉ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አያውቅም፡፡ በእርግጥ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ብዙዎች መጥተዋል፡፡ ይህ ግን አንድ አይደለም፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው ሲመጣ በሙሉ የአሜሪካን ወሳኝ የሥልጣን አካል አብሮት ነው የሚመጣው፡፡ ስለዚህ ይሄንን እንደ ትልቅ ስኬት ማየት አለብን፡፡

እኔ አሜሪካንም ስላደግሁ ኢትዮጵያ አሜሪካዊም ስለሆንኩ አውቀዋለሁ፡፡ አሜሪካኖች አንድን ነገር ሲያደርጉ እጅግ ብዙ አመዛዝነው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ፕሬዚዳንታቸውን አንድ ሀገር ለመላክ ብዙ ነገር አመዛዝነው ነው፡፡ ለብዙ ወራት አንዳንዴም ለብዙ ዓመታት መዝነው ነው፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንቱ ወደዚህ ለመምጣት ለምን ወሰኑ የሚለው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው የኢኮኖሚ ዕድገቱ ነው፡፡ እነርሱም በየጊዜው የሚከታተሉት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም መሪ ወደፊት እያደጉ የሚመጡ ሀገሮች እነማን ናቸው ብለው ገምግመው፣ ከአሜሪካን ጥቅም ጋር አያይዘው፤ ተንትነውት ነው፡፡ በእርግጥ የቻይና በሠፊው ኢትዮጵያ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ስምሪት ውስጥ መግባት የእነርሱንም ትኩረት ስቧል፡፡

በእኔ ግምት አሜሪካኖች ኢትዮጵያን ለቻይና ብቻ የመተው ምንም ዓላማ የላቸውም፡፡ በምንም ዓይነት፡፡ ሁለቱም ሀገሮች ቻይናም አሜሪካም ስልታዊ ጥቅም ይሰጣሉ ብለው ከያዟቸው ሀገሮች ኢትዮጵያ አንዷ በመሆኗ እዚያ ላይ እንሟሟታለን የሚል ነው፡፡ ይሄ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ኢኮኖሚ ስንል ምን ማለታችን ነው፡፡ ለምሳሌ የቦይንግ ኤርክራፍት በአፍሪካ አንደኛ ደንበኛ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ብዙ ቢሊዮን ዶላር አውጥታ በራሷ አውሮፕላን የምትገዛ አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ በዚህ ረገድ በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ደቡብ አፍሪካ ኬኒያ ወይም ናይጄሪያ አይደለም ኢትዮጵያ ነች፡፡ በእንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለው እንኳን ልዩነት ተቀራራቢ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚ አንድ ግምት አለ፡፡ ኢትዮጵያ ለምትገዛው ለእያንዳንዱ ቢሊዮን ዶላር 11 ሺ የአሜሪካን ሰዎች ሥራ ያገኛሉ፡፡ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሊዮን ዶላሮች እያወጣ ከእነርሱ አውሮፕላን ይገዛል፡፡ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አሜሪካኖች ሥራ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ ለአሜሪካኖች ስለኢትዮጵያ ማንነት አንድ ማመላከቻቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምንያህል የመግዛት አቅም አላት የሚለውን ያዩበታል፡፡ ባለፈው የእኛም ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ አሜሪካን ተጉዘው ከፕሬዚዳንቱ ጋር በተወያዩ ጊዜ ፕሬዚዳንት ኦባማ በአደባባይ የቦይንግን አውሮፕላን ስለገዛችሁ እናመሰግናለን ብለው ሲገልጹ ሰምተናል፡፡ ስለዚህ የፕሬዚዳንቱ መምጣት እጅግ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ መታየት አለበት፡፡

ኢኮኖሚ ትስስሩም እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ እነርሱም ይሄንን ተገንዝበዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ ለአካባቢው ዋነኛ አንቀሳቃሽ ነች፡፡ ለአካባቢው መረጋጋትና ደኅንነት ወሳኝ ሚና ስለምትጫወት ከአሜሪካ ፍላጎት አንጻር ይታያል፡፡ ይሄ አካባቢ ሰላም ካልሆነ ሌላውም የአፍሪካ አካባቢ ሰላም አይሆንም፡፡ ይህ ከእነርሱም ኢኮኖሚና የደኅንነት ጉዳይ አንጻር ያዩታል፡፡ ሲታይም በአንድ በኩል የመን አለ፤ እርስ በእርስ ጦርነት ላይ ያለ ሀገር ነው፡፡ መካከለኛው ምሥራቅም በአብዛኛው ከእኛ የማይርቅ አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ በዚያኛው ጎን ሳውዲ አረቢያ፣ በዚህኛው ጎን ደግሞ ኢትዮጵያ አካባቢውን ከማረጋጋት አንጻር ሚና ይኖራቸዋል ብለው ያስባሉ፡፡ እነዚህ ሀገራት ትልልቅ ሀገራት ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ደግሞ ሰላም ስለሌለ በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሰላም አሜሪካኖች ያበረታታሉ፡፡ አሜሪካን ተከትሎም የአውሮፓ ሕብረት ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንቱም ሆኑ የሚመሯት ሀገር ይሄንን ይገነዘባሉ፡፡ የእርሳቸውም መምጣት ትርጉም ያለው ከዚህም አንጻር ነው፡፡ በእርግጥ አሜሪካኖች የሚያነሷቸው ጉዳዮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንቱም ከአሁን ቀደም እንዳነሱት በፓርተነሮች መካከል የአመለካከት ልዩነት ይኖራል፡፡ ይሄ በጊዜያት የሚፈታ ነው፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንት ኦባማ መጡ ሲባል የአሜሪካን ሚዲያ ሠፊ ሽፋን ነው የሚሰጠው፡፡ ኢትዮጵያ ነፃ የሚዲያ ሽፋን ታገኛለች፡፡ የአሜሪካ የቢዝነስ ማህበረሰብም ትኩረት ይሰጣል፤ እኛም ዕድሉን መጠቀም አለብን፡፡

ዘመን፦ በትዊተር ገጽዎት ላይ በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ‹‹ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎች መጠለያ ትሆናለች›› ብለው ነበር፤ ከዚሁ ጋር አያይዘው ይሄ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችው መልካም ገጽታ ኢንቨስትመንቱም ላይ እያሳደረ ያለውን በጎ ተጽዕኖ ቢዳስሱት?

አቶ ዘመዴነህ፦ ልክ ነው ሁለቱም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲወጣ እየተከታተልን አስተያየት ስንሰጥ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መዳረሻ እሆናለሁ ብላ ማቀዷ አስፈላጊ ነው ምክንቱም በ10 ወይም በ11 ጂዲፒ ለማደግ ለሰውም ሕይወት ለመቀየር ድሮ የነበረው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አካሄድ አያዋጣም፡፡ ለዚህም ነው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአቶ መለስ ይፋ የተደረገው፤ አሁንም ያለው አመራር በዚሁ መንገድ ሲቀጥል ትርጉም ያለው ነገር ስለሆነ ነው፡፡ ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ኤክስፖርት ስታደርግ የነበረው ያው ቡናን የመሰሉ ሸቀጦችን ነው፡፡ በዚህ መንገድ የምንቀጥል ከሆነ ደግሞ ሁሌም በ11 በመቶ ኢኮኖሚውን ማሳደግ ያስቸግራል፡፡ ቡና ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የግብርና ምርቶች እሴት የሚጨምር ኢንዱስትሪ መምጣት አለበት፡፡ ይህ የእኔ አቋም ብቻ ሳይሆን ዕቅዱም ይሄንን ነው የሚለው፡፡ ከዚህ ጋር ደግሞ አብረው የሚሄዱ ኢንዱስትሪን የሚያመጡ ሴክተሮች አሉ፡፡ ጨርቃጨርቅና ቆዳ ከዚያም ደግሞ እጅግ የተራቀቁ ኢንዱስትሪዎች አብረውት ይመጣሉ፡፡ አሁን ያየን እንደሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ አራት የመኪና ፋብሪካዎች አሉ፤ ብዙው ሰው ይሄንን አይገነዘብም፤ ለጊዜው መገጣጠም ነው የሚሠሩት፤ ወደፊት ግን ማምረት ደግሞ ይመጣል፡፡ ይሄ የመጀመሪው የኢንዱስትሪ ልማት ደረጃ ነው፡፡ ይህ በዚህ መልክ እያደገ ከሆነ በ2025 የኢትዮጵያን ከ20 በመቶ ያላነሰ ኢኮኖሚ ይይዛል ማለት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ግን 4 በመቶ ነው፡፡

መታወቅ ያለበት አንድ ባለሀብት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ መልካም ገጽታዋን አይቶ ነው፡፡ ሀገሪቱ እንዴት እየተንቀሳቀሰች ነው የሚለውን ይመረምራል፡፡ ለምሳሌ ቦብ ጊልዶፍ በኢትዮጵያ ረሃብ ጊዜ የዕርዳታ ገቢ ለመሰብሰብ ያቀነቀነ እንግሊዛዊ ኮከብ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ያኔ ሲመጣ ለቸርነት፣ ለዕርዳታ ነበር፡፡ ከሁለት ከሦስት ዓመት በፊት ግን ኢትዮጵያ ሲመጣ ኢንቨስተር ሆኖ ነው፡፡ አዋሽ ወይንን የገዛው እርሱ ነው፡፡ ሌላም እያየ ነው፡፡ ስለዚህ በድህነት ያውቃት የነበረው ሰው እንኳን እርሱን ረስቶ ኢንቨስት ለማድረግ መጥቷል፡፡

የእኛም ድርጅት የሠራው ጥናት አለ በ2025 በፈረንጆች አቆጣጠር አፍሪካ ውስጥ ከሚኖሩት አራት የማኑፋክቸሪንግ ማዕከላት አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከደቡባዊ አፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ከምዕራብ ናይጄሪያ ሲሆኑ ሌላው ከፍተኛ ውድድር የሚኖረው ደግሞ ምሥራቅ አፍሪካ ነው፡፡ ከአራቱ ሁለቱ ያሉት እዚህ ስለሚሆን ኬኒያና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሀገራት ተመሳሳይነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት ይዞታዎች ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ በ2004 አካባቢ ነው የአበባ ልማት የተጀመረው፡፡ በዚህ ጊዜ መንግሥት ጥሬ ዕቃ የሚቀርበውም ለኢትዮጵያ ትኩረት እንዲሰጥ በርከት ያሉ የአበባ ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ ብናደርግ ትኩረት እናገኛለን ብሎ ነበር፡፡ አሁን ከመቶ ያላነሱ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ለጥሬ ዕቃ ወይም ግብዓት አቅራቢውም ለመንግሥትም በአንድ አካባቢ በዓይነት የሚመሳሳሉ ፕሮጀክቶች ሲኖሩ አገልግሎት ለመስጠት ይቀለዋል የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ለውጥ የተገኘበት ዘርፍ አበባ መሆን ችሏል፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያና ኬኒያም ክልላዊ የኢንዱስትሪ ቀጣናዎች መሆን ስለሚችሉ ትልቅ ዕድል ነው፡፡

የኢንዱስትሪ መንደር ቀጣና ወይም አካባቢ በከተማ ብቻ የሚወሰን አይደለም ለምሳሌ ደቡባዊ ኤሺያን ስናይ ታይላንድ፣ ማሌዢያ፣ ሲንጋፖር በአንድ አካባቢ መኖራቸው የሚያመጣው ተጽዕኖ አለ፡፡ ስለዚህ በአንድ አካባቢ መሆናቸው ለትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ለመሳሰሉት ይቀላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያና ኬኒያ እንደ ተወዳዳሪ መታየት የለባቸውም፡፡ አንዱ ለአንዱ ደጋፊና ጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል አለ፡፡

ዘመን፦ ግን እኮ ብዙ ኢንቨስተሮች ሊሄዱ የሚችሉት ነዳጅ ወዳላቸው የአፍሪካ ሀገሮች ነው የሚሉ አሉ፤ ታዲያ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መሠረተ ልማትና ማበረታቻ እርምጃዎች ይዛ ነው በዚህ ደረጃ ባለሀብቶችን ልትስብ እንደምትችል የሚታመነው?

አቶ ዘመዴነህ፦ ኢትዮጵያ እኮ እርሱን ማዘጋጀት መስጠትም ጀምራለች፡፡ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡ በአፍሪካ ትልቁም ተግዳሮት ይሄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 2400 ሜጋ ዋት ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል አላት፡፡ አሁን ደግሞ ግልገል ጊቤ ሦስት ከጥቂት ወራት በኋላ ሥራ ላይ ሲውል በአመዛኙ በእጥፍ ያድጋል፡፡ ከአራት ሺሕ በላይ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ የአባይ ግድብ ሲያልቅ ወደ ዐሥር ሺ እንገባለን፡፡ ይሄ አቅርቦቱ እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዋጋው አበረታች መሆኑ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በኪሎዋት አዎር አራት የአሜሪካን ሳንቲም ነው፡፡ በዓለም እጅግ ርካሹ ነው፡፡ በኬኒያ ስናይ ዐሥራ ስምንት ሳንቲም ነው፡፡ ከአራት ጊዜ እጥፍ በላይ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ኢንቨስተር ስታስበው ይሄንን ታስባለህ ስለዚህ ኃይል መኖሩ ወሳኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ያንን ማቅረብ ጀምራለች፡፡

ሌላው ደግሞ ሠፊ የሰው ገበያ ወዳለበት ኢንዱስትሪ መግባት ከፈለግህ ኢትዮጵያ ተመራጭ ነች፡፡ ቻይናም ያደገችው በዚህ ነው፡፡ ሠፊ የሰው ኃይል አላት፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ከፍተኛ ዕድል አላት፡፡ ዘጠና አምስት ሚሊዮን ሕዝብ አለ፡፡ መካከለኛ ዕድሜ የሚባለው ሃያ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣት ሕዝብ ነው፡፡ ይሄንን ሁሉ ሥራ ላይ ማዋል ትችላለህ፡፡ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች በዚህ ረገድ ዕድል የላቸውም፡፡ ያያችሁ እንደሆነ የማኒፋክቸሪንግ የሰዓት ደሞዝ ኢትዮጵያ ውስጥ የዶላር ሳንቲም ተጠቅመን ስናስበው በሰዓት አርባ አንድ ሳንቲም ነው፡፡ ይሄ የቻይናን ሃያ በመቶ ነው ማለት ነው፡፡ ለምንድነው ቻይናዎች ኢትዮጵያ መጥተው ፋብሪካ የሚከፍቱት ተብሎ ሲጠየቅ አንዱ ጠቋሚ ይሄ ነው፡፡ ዛሬ ቻይና በዓለም ላይ ሁለተኛውን ኢኮኖሚ ይዛለች፡፡ ከአሜሪካ ጋር የሚወዳደር ኢኮኖሚ አላት፡፡ የህዝቡ ኑሮ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል ማለት ይቻላል፡፡ በዚያው መጠን የሠራተኛው ደሞዝ በጣም በከፍተኛው ጨምሯል፡፡ ስለዚህ ሠፊ የሰው ኃይል ጉልበት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ጨርቃ ጨርቅ ቆዳን የመሳሰሉ ሠራተኛን በተወዳዳሪ ዋጋ የሚፈልግ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ለምሳሌ እዚህ በምሥራቅ ኢንዱስትሪ ዞን ያለው የቻይናዎቹን ጫማ ፋብሪካ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለሃያ ዓመታት ከቻይና ጫማ እያመረቱ ኤክስፖርት ያደርጉ ነበር፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ኢትዮጵያ መጥተው ፋብሪካ ተከሉ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ሺ የማያንስ ሠራተኛ አላቸው፡፡ ስለዚህ አንዱ ሳቢ ነገር ይሄ ነው፡፡

ጸጥታውና ሰላሙም እንደዚያው የሚታሰብ ነገር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ጉዳይ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር ይከፈታል፡፡ ዛሬ ከዚህ ጂቡቲ ኮንቴይነር ለመላክ አምስት ቀን የሚፈጀውን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ በዐሥር ሰዓታት ውስጥ ይነሳል፡፡ ይህም የመሠረተ ልማት መስፋፋት ኢትዮጵያን ኢንቨስተር እንድትስብ እያደረጋት ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኖችም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሃዋሳ፣ በኮምቦልቻ እዚህ አዲስ አበባም ቦሌ ለሚ ሁለተኛው ክፍል እየተሠራ ነው፤ ሌሎችም መንደሮች ይኖራሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ኢንቨስተሮችን በመሳብ ተወዳዳሪ ያደርጋል፡፡ ውድድር ያለ ነው፡፡ ወደ ቻይና በየጊዜው ሠፊ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት እየገባ ነው፡፡ ከእነርሱ ደግሞ ወደኛ እየመጡ ያሉ አሉ፡፡ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራትም እርስ በእርስ በመፎካከር ቻይናዎቹን ጭምር እኛጋ ኢንቨስት አድርጉ ይላሉ፡፡ በጎረቤቶቻችን ያሉ ሀገራትንም ስናይ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እጅግ ማራኪ የገለጻ መድረኮችን ያዘጋጃሉ፡፡ ውድድር ነዋ፡፡ በአሜሪካም ያሉ ሃምሳዎቹም ግዛቶች ራሱን እንደቻለ ሀገር ሆነው ነው እርስ በእርሳቸው የሚወዳደሩት፡፡ የእያንዳንዱ ግዛት ገዢዎች ለኢንቨስተሮች ምን ያህል የታክስ ማበረታቻ ልስጥህ እያሉ እርስ በራሳቸው ይወዳዳራሉ፡፡ ለምሳሌ የእኛ ድርጅት የሚያወጣው አፍሪካን አትራክቲንግ ሰርቬይ የሚባል ሪፖርት አለ፡፡ ባለፈው ዓመት ታዲያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ከፍተኛ ከተባሉት አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዐሥሩ ከፍተኛ ሀገሮች አንዷ ሆናለች፡፡ እርሱ ብቻ አይደለም ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት በመፍጠር ለውጥ ካመጡ ሀገሮች ከአምስቱ አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡

ሌላው መረሳት የሌለበት ደግሞ በአፍሪካውያን በራሳቸው እጅ ያለ የመርከብ ድርጅት ቢኖር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመርከብ ድርጅት ነው፡፡ አንድም የአፍሪካ ሀገር በራሱ እጅ ያለ የመርከብ ድርጅት የለውም፡፡ በአፍሪካ ግዙፉ የመርከብ ድርጅት የኢትዮጵያ ነው፡፡ ብዙ ሰው ይሄ ነገር ይገርመዋል፡፡ የትነው መርከቦቻችሁን የምታቆሙት ይለናል፡፡ ጅቡቲ ነዋ እንላቸዋለን፡፡ ደቡብ አፍሪካ እንኳን የራሷ የላትም የውጭ ድርጅቶች ሀብት ነው፡፡ ከብሔራዊ ደኅንነት አንጻርም ካየኸው የራስ መሆኑ፣ ትልቅ መሆኑም ትርጉም አለው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ምክንያቶች ባለፈው ዓመት ብቻ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ 1 ነጥበ 5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት መቶ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ይህ እያደገ ነው ማለት ነው፡፡ አሁንም ግን እጅግ ብዙ እንፈልጋለን፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት 2 ቢሊዮን ዶላር ለመሳብ ታቅዷል፡፡ አስገራሚ ነው፡፡ አንዳንደ ሀገራት ከፍተኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ አምስት ቢሊዮን ዶላር ሳቡ ተብሎ ሊወራ ይችላል፡፡ ዝርዝሩን ስታየው ግን የፕሮጀክቱ ዓይነት ምናልባትም መቶ ሰው ብቻ ሊቀጥር የሚችል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ዶላር ፋብሪካ ቢመጣ አንድ ሚሊዮን ወይም አምስት መቶ ሺ ሰው ለቀጥር ይችላል፡፡ የአንዳንድ ሀገራት ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ስማርት(ሥልጡን) አይደለም፡፡ ያንን ገንዘብ በመጠቀም ዘርፈብዙ አላደረጉትም ማለት ነው፡፡

ዘመን፦ የእርስዎ ድርጅት ኢትዮጵያን ኢንቨስተሮችን በመሳብ አቅሟ ከአፍሪካ አሥር ሀገሮች አንዷ አድረጎ ዘርዝሯል፤ ነገር ግን አንዳንዶች መንግሥት ባንክና ቴሌኮምን የመሳሰሉ ሴክተሮችን ለግሉ ሴክተር ክፍት አለማድረጉ ከዚህም በላይ መሳብ እየተቻለ ሳይስብ እንዲቀር አድርጓል ይላሉ፤ ምን ዓይነት አስተያየት አለዎት?

አቶ ዘመዴነህ፦ እስቲ ባንክንና ቴሌኮምን ለያይተን እንየው፤ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ መምጣት ስጀምር የዛሬ 17 ዓመት ፍጹም የአሜሪካዊ የአዕምሮ ግንዛቤ ይዤ ነበር የመጣሁት፡፡ ስመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ንግድ ባንክ፣ አንድ ልማት ባንክ፣ ሁለት ሦስት ትንንሽ ገና የጀመሩ የግል ባንኮች ነበሩ፡፡ ሳየው ታዲያ ይሄ ሀገር እንዴት ሆኖ ነው የሚያድገው? ለምን የውጭ ባንኮች የሉም? እል ነበር፡፡ ቴሌቪዥን ላይ ሁሉ ወጥቼ እናገር ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የነበረው የኢኮኖሚ ፍልስፍና የዓለም ባንክም ሆነ የገንዘብ ድርጅቱ ገበያው ራሱን ማስተካከል ይችላል፤ መንግሥት እዚህ መግባት የለበትም የሚለው ስለነበር ሁላችንም እናምን ነበር፡፡ ኬኒያ እንኳን ሃምሳ ባንክ አለ እል ነበር፡፡ እኔ አሁን የምለው ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ የውጭ ባንኮች መግባታቸው እኔ አይታየኝም፤ ወደፊት የሚሆነው ደግሞ ሌላ ታሪክ ነው፡፡ አሁን መንግሥትም ያያዘው ስትራቴጂ አሁን ያሉትን ማጠናከር፣ የመንግሥትም ይሁን የግል ባንኮቹን ማጠናከር ብቁና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማድረግ፣ እንዲያላምዱ ማድረግ፣ ሌሎች ዓለም አቀፍ ባንኮች ከመምጣታቸው በፊት እነዚህ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ እኔም የምስማማው በዚህ ነው፡፡ ካፒታላቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡ እንደማንኛውም ብሔራዊ ባንክ መሥራት መቻል አለባቸው፡፡ ይዞታውን ማጠናከር ነው፡፡

እንደተባለው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደኋላ ጎትቶታል የሚል ክርክር በእርግጥም አለ፡፡ ብዙ ቦታ ሲባል እሰማለሁ፡፡ እኔ የምለው ግን ዓለም ባንክ ራሱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ10 ነጥብ አንድ አድጓል ካለ ምኑ ላይ ነው ጥያቄው? 15 በመቶ እናድግ ነበር ወይ? አይመስለኝም፡፡ በዚህ ደረጃ ቻይናም አላደገችም፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚውን ጎትቷል የሚለው ብዙም አዋጪ ክርክር አይደለም፡፡ ምናልባት የአገልግሎት ብቃት ጥራት ላይ ሁላችንም ጥያቄ እናነሳለን፡፡ ባንኮቻችን ሙሉ በሙሉ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን መለወጥ ማሳደግ አለባቸው የሚለው ያስማማል፡፡ በእርግጥ ያንንም በማድረግ ላይ ናቸው፤ ቴክኖሎጂ መጠቀም ላይ እየሄዱበት ነው፡፡

ቴሌኮምን በተመለከተ ግን መንግሥት ቢያየው ጥሩ የሚመስለኝ ምንድነው የኢትዮጵያ ፕራይቬት ሴክተር ባንኮቹ ላይ እንዳደረገው ቴሌኮም ሴክተርም ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርግ ቢፈቀድ ጥሩ ነው፡፡ ስለውጭ ኢንቨስተሮች እያወራሁ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን 17 ውጤታማ የሆኑ የግል ባንኮች አሉ፡፡ ስለዚህ ንግድ ባንክም ቀልጣፋ እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ተወዳዳሪ ባንኮች ናቸው፡፡ ኃላፊነትም እንዲሰማው አድርገዋል፡፡

በአሜሪካ ስላለው ልንገራችሁ። አሌክሳንደር ግርሃም ቤል ነው ቴሌፎንን የፈጠረው፤ ኢቲየንቲ የሚባል ኩባንያ አቋቁሟል፡፡ ስድሳ ሰባ ዓመት አሜሪካኖች የነበራቸው ይሄ አንድ ቴሌኮም ኩባንያ ነበር፡፡ ሁሉን የምትገዛው ቀፎውንም ከዚሁ ኩባንያ ነበር፡፡ ጥገናና አገልግሎት ሳይቀር የሚሰጠው እርሱ ነበር፡፡ የግል ኩባንያ ቢሆንም ሞኖፖሊ ነበር፡፡ የዛሬ ሠላሳ አንድ ዓመት አሜሪካኖች ይሄ ሞኖፖሊ አዋጪ አይደለም ብለው ተወዳዳሪ ብዙ እንዲኖር አደረጉ፡፡ ስለዚህ እንኳን እንደኛ ዓይነት ታዳጊ ሀገር ይቅርና ሌሎች ከፍተኛ ካፒታሊስት ሀገሮች እንኳን ሞኖፖሊ አልሠራም፡፡ ስለዚህ በባንኩ እንደተደረገው ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ በቴሌኮም ኩባንያ በማቋቋም ሚና ቢኖራቸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ለኢትዮ ቴሌኮም የሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ ቢኖረው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን አሁንም ለውጭ ይከፈት የሚል አቋም የለኝም፡፡

ባለፈው ፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ከመጡት ትልልቅ ሰዎች አንዱ ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ አንዱ ነበር፡፡ እርሱ ሲመጣ ከአሜሪካን ሀገር ሞባይሉን ይዞ ነው የመጣው እጅግ አዎንታዊ አመለካከት ያለው ሰው ነው፡፡ እዚህም እየመጣ ያማክራል፡፡ አቶ መለስም እያለ ይመጣ ነበር፡፡ አየ አየና ‹‹እኔ ለኢትዮጵያ ለሁሉም ነገር በጎ አመለካከት አለኝ፤ ከዚህ ከሞባይል አገልግሎት በስተቀር፤ ለምንድነው ስልኬ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሠራው? የእኔ ስልክ የማይሠራባት የዓለማችን ብቸኛ ሀገር ነች›› ሲል ነበር (ሳቅ…)፡፡

በእርግጥ እዚህ ቤቴ አሁን አራተኛ ትውልድ ሞባይል ቴክኖሎጂ አለ። ኢንተርኔቱም እጅግ ፈጣን ነው፡፡ ድምፁም የጠራ ነው፡፡ እዚህ እቤቴ ድረስ ፋይበር ኬብል አስገብቻለሁ፡፡ ስለዚህ የ13 ዓመት ልጄ ማይክ የቤት ሥራ የማይሠራበት ምንም ምክንያት የለውም ማለት ነው፡፡ ይሄን ይሄንን ማመስገን አለብን፡፡ በገጠርም ኢትዮ ቴሌኮም ብዙ ሠርቷል፡፡ መመስገን አለበት፡፡ ነገር ግን ከዚህ በላይ ይጠበቃል፡፡ ደግሞ ሠፊም ዕድል አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ወጣቱ ቴክኖሎጂ አድናቂ ወዳጅ ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን የአይ..ቲ ማዕከል መስፋፊያ ማድረግ የሚያስችል ዕድል አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቴሌኮም ባንኪንግም እየመጣ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ መንግሥትን ብሆን አንድ እንኳን እፈቅዳለሁ፡፡

ዘመን፦ የውጭ ኢንቨስትመንት እንሳብ ሲባል በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖስ የለም? እርሱ መታየት ያለበት እንዴት ነው?

አቶ ዘመዴነህ፦ መቼም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የግድ የሚፈለግ ነገር ነው፡፡ ከዓለም ልዩ ልንሆን አንችልም፡፡ የሚያከራክርም አይደለም፡፡ ዋናው ነገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሲመጣ በተቻለ መጠን ከሀገር ውስጥ የግሉ ሴክተር ጋር በጥምረት እንዲሠራ የማድረጉ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሸሚዝ የሚያመርት የቻይና ኩባንያ ቢመጣ ዋናውን ገጣጥሞ ማቅረቡን የሚሠራው ዋናው የቻይና ኩባንያ ቢሆንም የተወሰነውን የሥራውን ሂደት ግን ኢትዮጵያዊ ፋብሪካ ያለው ባለሀብት ቢሠራና የቻይናው የአቅርቦት ምህዋር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ በመንግሥትም የተያዘው ፖሊሲ ምንድነው በእርግጥም ጥምረቱን መፍጠር አለብን የሚል ነው፡፡ ይህ ሲፈጠር በዓለም አቀፉ ገበያ ውስጥ ኢትዮጵያዊውም የግሉ ሴክተር ድርሻ እንዲኖረው ያደርጋል ማለት ነው፡፡ አንዳንዶች በእርግጥም የውጭ ኢንቨስትመንት መምጣቱ ያሳስባቸዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም የገቡ የውጭ ኢንቨስተሮች ከኢትዮጵያ የግል ሴክተሮች ጋር በጆይንት ቬንቸር እየሠሩ ያሉ አሉ፡፡ በእርግጥ በግድ አብረህ ሥራ የሚል ሕግ የለም፡፡ አንዳንዶች ሀገራት የግድ ያደርጉትና ሳይሳካላቸው ሲቀር ይታያል፡፡ በተቻለ መጠን ግን ኢትዮጵያ ተመራጭ ፖሊሲ ይዛ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱም በሰንሰለቱ ውስጥ የሚገባበትን ብዙ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል፡፡

ዘመን፦ አሁን የዲያስፖራ ቀን በኢትዮጵያ እየተከበረ ነው፤ እርስዎ በዚህ ላይ ያለዎት ሐሳብ ምንድንው?

አቶ ዘመዴነህ፦ ኢትዮጵያ ካላት ትልቅ ሀብት አንዱ ውጭ ያለው ዲያስፖራ ነው፡፡ ለሀገሪቱም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለውጥ እያመጣ ያለው አንዱ ዲያስፖራውም ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከሚገኝባቸው ምንጮች አንዱ ዲያስፖራው ነው፡፡ በቢሊዮን ዶላር ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገባው፡፡ በተለይ መካከለኛው ምሥራቅና አሜሪካ ያሉ ዲያስፖራዎች በብዙ ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ ይልካሉ፡፡ በአንድ በኩል የእነርሱ አስተዋጽኦ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሞላው ክፍተት አለ፡፡ ብዙ ሕዝብ የሚተዳደረው፣ ቤት የሚገዛው ዲያስፖራ በሚልከውም ዶላር ነው፡፡ ስለዚህ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ለእኔ ግን ትልቁ ነገር ምንድነው? እነዚህ ወገኖች ወደ ሀገራቸው መጥተው እውቀታቸውንና ሀብታቸውን እዚህ በሠፊው ማዋል የሚችሉበት ቀን ቢመጣ ነው፡፡ አንድ ቀን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡ ስለዚህ ይሄ መዘጋጀቱ ጠቃሚ ነው፡፡ የአንድ ሳምንት ስብሰባ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ውይይት ይደረጋል፡፡ ይሄ ዕድል ነው፡፡

አሜሪካ ያለውን እንኳን ሳይ አሁን የተወሰነ ዕድሜ ላይ የደረሱ አሉ፡፡ ከዛሬ አርባ ዓመት ምናመን ላይ የሄዱ ከዚያም ትልቅ ደረጃ የደረሱ ዶክተሮች፣ ሳንቲስቶች፣ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ወዘተ፡፡ እነዚህ ብዙ ያስባሉ፤ እዚህ ደርሻለሁ እንግዲህ ምን ላድርግ ብለው ያስባሉ፡፡ እዚህ ቁጭ ከምል ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ አልሠራም? ኢንቨስት አላደርግም የሚሉ አሉ፡፡ ከዚያ ትውልድ ደግሞ በዕድሜ ያነሰ አለ፡፡ 40 ዓመት ወይም ሃምሳ ዓመት አካባቢ ያለ፡፡ ይሄም ለውጡን እያየ ለምን ኢንቨስት አላደርግም የሚል አለ፡፡ ስለዚህ ተስፋ አለ፡፡

በቅርቡ ዋሽንግተን ሄጄ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የሀኪሞች ቡድን የሚባል አለ፡፡ 250 የሚደርሱ ድንቅ ዶክተሮች ናቸው፡፡ የአዕምሮ የጀርባ አጥንት ወዘተ ቀዶ ሕክምና ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ዶክተሮች በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የልህቀት ማዕከል የሆነ ሆስፒታል ለመሥራት አቅደዋል፡፡ እንግዲህ ይህ ሆስፒታል ሲከፈት ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጣ ማሰብ ይቻላል፡፡ ሰዎች ወደ ባንኮክ፣ ወደ ህንድ፣ ወደ አሜሪካም ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ አንድ ሰው ሲወጣ በዐሥር ሺዎች የሚሆን ዶላር ሊያወጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ሆስፒታል ሲሠራ የሚመጣ ለውጥ ይኖራል፡፡ ይሄንን በአይቲ፣ በሌሎች ቴክኖሎጂዎች እናባዛው የተለያዩ ባለሙያዎች እንዲህ ቢከፍቱ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ምናልባት አንድ ቀን ዕውቀት ኤክስፖርት ልታደርግ ትችላለች ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ እኮ ትልቁ ኤክስፖርት የግብርና ምርት አይደለም፤ ዋናው አገልግሎት ነው፡፡ ይህም አገልግሎት አቪየሽን ነው፡፡ ባለፈው እንኳን 3.2 ቢሊዮን ዶላር ከአቪየሽን አግኝታለች፡፡ ይህ የቡናን ብዙ እጥፍ ነው፡፡ ስለዚህ ሐኪሞችም ሲመጡ ሜዲካል ቱሪዝም የሚባለው ዓይነት ይስፋፋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዲያስፖራው ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ የሚችልባቸው ሴክተሮች አሉ ማለት ነው፡፡

እኔ እዚህ ስመጣ የዛሬ 17 ዓመት የዲያስፖራ ፖሊሲ አልነበረም፡፡ ስለዚህ እዚህ ሀገር ቪዛ ይታደስልኝ የነበረው የካምፓኒየን ፈቃድ ሳድስ ብቻ ነበር፡፡ በፈረንጆች 2002 ላይ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የምትባለው ሕግ ወጥታለች፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ ቢዝነስ ኖረኝም አልኖረኝም ይሄ ራሱ በራስ መተማመን ይሰጥሃል፡፡ እንደዚህ ቤት መሥራት ትችላለህ፡፡ ካልሆነ ግን ቢያስወጡንስ ትላለህ፡፡ አንድ ቀን የኢትዮጵያ ዜግነትም ይሰጠናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጥምር ዜግነት የሚባል አለ አይደል፡፡

ዘመን፦ የዛሬ 17 ዓመት አገርዎ ለመግባት ግድ ያለዎ ምክንያት ምን ነበር?

አቶ ዘመዴነህ፦ መቼም ሁላችንም አሜሪካ ስንኖር ኢትዮጵያ እንመጣለን የሚል ሃሳብ ይኖራል፡፡ ያፋጠነው ግን ምንድነው ብትሉኝ ግን ሚስቴን ጁሊን ማግኘቴ ነው፡፡ የእኛ ሴቶች እንደሚታውቀው ቆንጆዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት እኔ አግብቼ አላውቅም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጓደኞቼ አሜሪካን ሀገር ጥሩ ጋብቻ አላቸው፡፡ በአጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ግን አንድ ሁለት ሳምንት ሲቆዩ ምን ቀን ነው ሚስት ያገባሁት እያሉ የሚያማርሩ አጋጥመውኛል፡፡ የእኛ ሴቶች የሚያምሩ ናቸው፡፡ ከቦሌ አየር ማረፊያ ጀምሮ ወደ ከተማ ስትመጣ የሚያዩአቸውን ሴቶች ሁሉ ለራሳቸው ማጨት ሊፈልጉ ሁሉ ይችላሉ፡፡ እኔም መጥቼ መስቀል አደባባይ አካባቢ ስደርስ ያጋጠመኝ ይኸው ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሚስቴ ጁሊ በዚያ አካባቢ ሱቅ ነበራት፡፡ አሁንም አላት፡፡

የዚያን ጊዜ እኔ የመጣሁት ለአንድ ሳምንት ጉብኝት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አባቴ ነበር፡፡ የምሠራው አርጀንቲና ነበር፡፡ ከአርጀንቲና ወደ ብራዚል ዕቃዬ በኮንቴይነር ተጭኖ ነበር የመጣሁት፡፡ አንድ ፓይለት ጓደኛ ደግሞ ነበረኝ፡፡ ለአንተማ አንድ በኢትዮጵያ እጅግ ውብ የሆነች ቆንጆ አስተዋውቅሃለሁ አለኝ፤ ሱቋ ወሰደኝ፡፡ ከዚያም ማታ ቤቷ ጋበዘችኝ፡፡ ቅዳሜና ዕሁድ ላንጋኖ ሄድን፤ ከላንጋኖ ስንመለስ መኪና ውስጥ እንግዲህ ከተዋደድን ለምን አንጋባም ተባባልን፡፡ በቀላሉ ተስማማን፡፡ ሰኞ ጠዋት መዘጋጃ ቤት ሄድን፤ ምስክር አምጡ አሉን ተሯሩጠን አንድ ሁለት ሰዎች ይዘን ሄድን፡፡ ከዚያ ደግሞ ምን ይሉናል ብዙ ቀጠሮ ስላለ ከወር በኋላ ኑ ይሉናል፡፡ ኧረ እኔ አልችልም ብል አይሆንም ተባለ፡፡ ያን ዕለት ማታ ትኬት ቆርጠን ወደ እኔ ቤት ወደ አሜሪካን ልንሄድ ወሰንን ወደ ዋሽንግተን፡፡ ከዚያ በፍጥነት ሄድን እርሷም የአውሮፓ ቪዛ ነበራትና ወዲያው ተሳካ፡፡ ለመጋባት በአሜሪካ አስፈጻሚዎች ዐሥራ አምስት ደቂቃ አልፈጀባቸውም፡፡ ተጋባን፡፡ ቤተሰቦቻችን ልንጋባ ነው ስንል እንዴ አብዳችኋል እንዴ አሉን፤ መቼ ትተዋወቃላችሁ አሉን፤ እኛ ግን ጨርሰን እኔ ወደምሠራበት ከዚያ በኋላ ከዋሽንግተን ወደ ብራዚል ሄድን፤ እኔ እምኖረው ብራዚል ነው እርሷ ግን ብራዚል አልኖርም አለችኝ፡፡ ታዲያ የት እንኑር ስል ኢትዮጵያ አለች የዚያን ሀገር ኑሮ አትወደውም ነበር፡፡

እኛ ወደኢትዮጵያ ስንመጣ በዚያን ጊዜ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነበር፡፡ በኋላም የህወሓት ክፍፍል ነበር፡፡ የዘጠና ሰባት ምርጫም እዚህ ነበርኩ ይሄንን ሁሉ እኮ አሳልፈናል፡፡ ስለዚህ 1998 ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚታሰብ አልነበረም፡፡

ከዚያ በፊት ግን እንዳልኳችሁ ውጭ ነበርን፡፡ ለተወሰነ ጊዜ እርሷ እሪ አለች ብራዚል ኖርን፡፡ እርግጥ እየተመላለሰች ነበር፡፡ እንደዛሬው እንኳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጥታ ሳኦፖሎ በረራ አልነበረውም፡፡ ስልክም መከራ ነው፡፡ እርሷ እጅግ ማራኪ ሚስት ስለሆነች በሁለት ሳምንት በምናምን አንዴ እመጣ ነበር፡፡ እኔ ሳውቃትም ወደ ሃያ አምስት ዓመት ነበረች፡፡ አባቷ ጣሊያን ስለነበሩ የአውሮፓ ቪዛ ነበራት፡፡ ወደ አሜሪካም ስንሄድ የአውሮፓ ፓስፖርት ስለነበራት ነው፡፡ አሁንም ድረስ ግን የአሜሪካ ፓስፖርት የላትም ግሪን ካርድ አላት፤ ግን ብዙም ግዴላትም፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ከመጣን በኋላ ከኢትዮጵያ አልወጣም አለች፤ ስለዚህ መጨረሻ ላይ ወሰንን፡፡

እንደምንም ብለን እዚህ ቃሊቲ አቃቂ አራት ሺ ስኩየር ያህል ቦታ ወስደን የሴቶች ሞዴስ ማምረቻ ፋብሪካ ልንገነባ መሣሪያ አዘን ግንባታ ጀምረን መንቀሳቀስ ስንጀምር ቴሌቪዥን ላይ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ተጀመረ የሚል ሰማን፡፡ የሚገርም ነበር፤ ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው ይገርማል፤ እኛ እንደውም ዕድለኞች ነን፡፡ ከአንድ ዓመት ቀደም ብለን መጥተን ቢሆን አስቸጋሪ ነበር፤ ብዙ ሰው ዕቃው ተወስዶበታል፡፡ ብዙዎች ማሽነሪ አዘው አሰብ ላይ ተወርሶባቸው በኋላ መቋቋም ያቃታቸው ብዙ ሰዎች አውቃለሁ፡፡ እኛ ግን ገና መሬት ስንቆፍር መሣሪያ ስናዝ ያ ሆነ፡፡ መጀመሪያ አዝነን ነበር፤ ነገር ግን ያ ሁሉ አለፈ፡፡ እንግዲህ ይህ ነበር ወደዚህ እንድመጣ ያፋጠነኝ፡፡

ለእኔ እዚህ መቆየት የእርሷ መኖር ወሳኝ ነበር፡፡ ብዙ ነገር ስለዚህ ሀገርም ታስረዳኛለች አሁን እንኳን ንግግር ሳዘጋጅ ሚዲያ ላይ ስወጣ ከኢትዮጵያ አንጻር እንዲሆን አስተያየት ትሰጠኛለች፡፡ እዚህም ስመጣ እርሷ እጅግ ሠፊ ኔትዎርክ ስለነበራት ያ ጠቅሞኛል፡፡ በጣም ተግባቢ ነች፡፡ እርሷ ካለች እዚህ ቤታችን እንኳን በሳምንት አንዴ እንኳን ግብዣ ይደረጋል፡፡ እርሷ ካለች የውጭ ኢንቨስተሮች ሲመጡ ብዙ ጊዜ ሆቴል አንወስዳቸውም፡፡ እርሷ ካለች ወደቤት እናመጣቸዋለን፡፡ ስለዚህ ዲያስፖራዎችንም ምን እናድርግ ሲሉን መጀመሪያ ሚስት ከሌላችሁ ሚስት አግቡ እላለሁ፡፡ ያ ሚዛንን ይጠብቃል ጠንካራ ሚስት ስትኖር ብዙ ነገር ይለወጣል፡፡

ለምሳሌ ይሄንንም ቤት ልንሠራ ስናስብ ሲገዛ ቦታው የዚያን ጊዜ ምንም የሌለበት ነበር። እርሷ ወደዚህ አካባቢ ትንሽ ቤት ስለነበራት ይሄንን ቦታ እናየው ነበር፡፡ ከሰፈር ሰፍር መሬት እንድንገዛ እርሷም ትዞር ነበር፡፡ ከዚያም አንድ ቀን መሬት አግኝቻለሁ በሊዝ መግዛት አለብን አለችኝ፡፡ ምን ያደርግልናል ስላት ይሄ ወደፊት በጣም ጠቃሚ አካባቢ የሚሆን ነው አለችኝ፡፡ ተደራድራ መጣች ይሄ ያለንበት አሁን አንድ ሺ ካሬ ነው ያኔ በሁለት ሚሊዮን ገዛነው፡፡ አይሆንም ብዬ ስል እርሷ ኡኡ አለች። የዚያን ጊዜ ታዲያ ለአንድ ወር ያህል ተናድጄ አላናገርኳትም፡፡ አሁን ዋጋው እየጨመረ ሳየው፣ አሁን ያለውን የቦታውን ግምት ስሰማ ሁሌ በደስታ እስማታለሁ፡፡ አሁን መሬቱ ስድሳ አምስት ሚሊዮን የሚገመት ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ ተያያዥ በሆነ ቦታ አንድ ሺ አምስት መቶ ካሬ በሊዝ ወጥቷል…አሁን ይሄም ሲገመት ሰባ አምስት ሚሊዮን ነው፡፡ በአጠቃላይ አሁን የያዝነው ቦታ የመሬቱ ግምት መቶ አርባ ሚሊዮን ነው፡፡ እኔ ብሆን እዚህ ሠፈር አሁን መኖር አልችልም፡፡ ሚስት ባላገባ ማለቴ ነው፡፡ በአንድ በኩል ይሄ የሚያሳየው የኢትዮጵያንም ዕድገት ነው፡፡ ስለዚህ እርሷ ባትኖር እኔ ወደዚህ አልመጣም ነበር፡፡

አሁን ግን ዘመዶቼም እናቴም ጭምር ወደዚህ መጥተዋል፡፡ እዚያ በእርግጥ የላውንደሪ ቢዝነስ ነበራት፡፡ የፔንታጎንን የወታደራዊ ሹማምንት ልብሶች ማጠብ ትሠራ ነበር፡፡ አሁን ዕድሜዋም ሲገፋ ወደዚህ መጥተዋል፡፡ ልጄም 13 ዓመቱ ነው፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ከእውነታው ወጥቶ እንዳያስብ፣ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲያድግ እጥራለሁ፡፡ ለምሳሌ ምግብ ላይ ሲሆን ይሄንን ያንን አልበላም ሲል አሜሪካን ሀገር ቢሆን መጽሐፍ አውጥቼ አስነብቤ፣ ቪዲዮ አሳይቼ እውነታውን አውቆ እንዲመገብ ማድረግ ሊኖርብኝ ይችል ይሆናል፡፡ እዚህ ሳለ ግን በመኪና ይዤው ወጥቼ በአቅራቢችን ያሉ ችግረኛ ልጆችን አሳይቼው እነዚህ እኮ ለመብላት እንኳን ሲፈልጉ ምንም የሚያጡበት ጊዜ አለ ብዬ ሳሳየውና ስነግረው ሁኔታውን ይረዳል፡፡ ስለዚህ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲያድግ የዚህንም ሀገር እውነታ እንዲረዳ አደርጋለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ብዙ መልካም እሴቶች አሉ፡፡ እዚህ ቀብር እኩል ትሄዳለህ፤ ሠርግ ትጠራራለህ፡፡ ውጭ እኮ እንደዚህ አይደለም፡፡ ተመራርጦ የሚደረግ ነው፡፡ ብጤህን ነው የምትፈልገው፡፡ እዚህ እንደዚያ አይደለም፤ አብረህ ነው የምትኖረው፤ እኔ ቤት አሁን ሰባት ሠራተኞች አሉ ነገር ግን የሚበላው የሚጠጣው አብሮነው፡፡ ሚስቴም ይቺን የቡና ክሽክሽ ትወዳለች ስለዚህ ተሰብስቦ ቡና ይጠጣል፡፡ ልጄም ጓደኞቹን ይዞ ይመጣል፡፡

የሰላምና የጸጥታችን ጉዳይም ጥሩ እንዲሆን ያደረገው ይኸው ማህበራዊ ትስስር መኖሩ ነው፡፡ እዚህ ሀገር ያለ ሀብታምም ደሃም ሠርግ ቢደግስ ሀብታም ደሃ ሳይል የአካባቢውን ሰው ሁሉ ይጠራል፡፡ ሸራተን ስሄድ ተገርሜ ነው የምመጣው፤ ሁሉም በእኩልነት ነው የሚስተናገደው፡፡ ኢትዮጵያም ሰላም ሆና የምታድገው ይሄንን መጠበቅ ስትችል ነው፡፡ ሌላው ወሳኝ ነጥብ የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣሪን አማኝ ነው፡፡ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ፈጣሪን ያምናል፡፡ ሌላጋ እንዲህ እየሆነ አይደለም፡፡

ዘመን፦ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ያበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ምንድነው?

አቶ ዘመዴነህ፦ እዚህ ከመምጣቴ በፊት ብዙ ሥራዎች ሠርቻለሁ፡፡ በተለያዩ ሀገራት፡፡ እንደ አስተዋጽኦ ካየነው በተለይ ለታናናሾቻችን እንዲማሩበት የእኔ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም አብረውን የሚሠሩ ፓርትነሮች አስተዋጽኦ ምንድነው ይሄንን እውቀትን መሠረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ቢዝነስ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ባለሙያዎች እውን ማድረጋችን ትልቅ ውጤት ነው እላለሁ፡፡ እኛጋ አንድም ፈረንጅ ቢሯችን የለም፡፡ ከከፍተኛ ማኔጅመንት እስከ ታች ድረስ በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ፈረንጆቹ ራሳቸው አንዳንዴ ግራ ይጋባሉ፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ሲታይ ፈረንጆች አሉ፡፡ እኛጋ ብቻ ነው ይህ የሆነው ስለዚህ ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል አስተዋጽኦ ነው፡፡ ኒውዮርክና ለንደን ከሚሠራው ሥራ እኩል የሆነ ጥራት ባለው መንገድ እኩል እንሠራለን፡፡ ስለዚህ በአፍሪካ ያሉትን የአቪዬሽን የማማከር ሥራዎች የሚሠሩት በሙሉ ኢትዮጵያውን ናቸው፡፡ አሁን ዑጋንዳ ጀምረናል፡፡ ሩዋንዳና ናይጄሪያም በተመሳሳይ እየሠራን ነው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ከፍተኛ የእውቀት አገልግሎት ከኢትዮጵያ ኤክስፖርት ማድረግ ማመንጨት ይቻላል ለሚለው ምሳሌ ነው፡፡

በግል ደረጃ ከታየ ግን ትልቁ ውጤታማነቴ ልጄ ነው፡፡ ዝም ብሎ በሥራዎች ላይ ብቻ ሳሳልፍ ነበር የቆየሁት፡፡ ስለዚህ ማይክን ወልጄ እንዲህ ሆኖ ማየቴ እጅግ ያስደስተኛል፡፡ ከቢዝነስም ሁሉ የበለጠ የሚያስደስተው እርሱ መሆኑን አይቻለሁ፡፡ ያኔ እንደዚህ አላስብም ነበር፡፡ አሁን ግን ልጅ አለኝ ማለት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በሥራ ደረጃ ሌሎች ብዙ ሥራዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አሁን መዘርዘር አስፈላጊ አይደለም እንጂ ብዙ ፕሮጀክቶች እንሠራለን፡፡

ዘመን ፡- እናመሰግናለን።

አቶ ዘመዴነህ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 

] አዘጋጅ ማለደ ዋስይሁን

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137297
TodayToday108
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week8
This_MonthThis_Month3379
All_DaysAll_Days137297

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።