የመልካም ገፅታችን እመርታዎች Featured

03 Sep 2015

በእርግጥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና መቆየቷ ይታወቃል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫም ሆና ቆይታለች፡፡ ይህም ለረጅም ዘመናት ሀገሪቱ ነጻነቷን ጠብቃ ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ስትታገል በመቆየቷ ያገኘችው ክብር መሆኑም ይታወቃል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በእርስ በእርስ ጦርነት፣ በረሃብና በድህነት በተለያዩ አጋጣሚዎች የምትነሣና ከዚህም አንጻር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጀንዳ ሆና መቆየቷ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ የታላቋንና የታሪክ ባለቤት የሆነችውን ሀገር ኢትዮጵያን ገጽታ አነሰም በዛም አጥቁሮት ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በ1983 .ም ካበቃ በኋላ የተገኘው ሰላም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ልማቱ ደረጃ በደረጃ እንዲያድግ ማድረጉ፣ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታው ከጊዜ ጊዜ አስተማማኝ ወደመሆን መሻገሩ ለዚህች ሀገር የተስፋ ዘመን መምጣቱን ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የሚጠቁም ነበር፡፡ ስለዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ዘላቂ ትብብሮችን ከዚህች ተስፋ ካላት ሀገር ጋር ለማድረግ አልዘገዩም፡፡ ስለዚህ ለነበራት እርምጃ ሁሉ ከጊዜ ጊዜ እያደገ የመጣ ዘርፈ ብዙ ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ሀገሪቱም በአጸፋው አስደሳች ዕድገትን በየመስኩ በማስመዝገብ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍና ትብብር ምላሽ ሰጥታለች፡፡ በመሆኑም የትናንት አሳሳቢ መልኳ ተለውጦ ዛሬ ዛሬ ሁሉንም ወገን የሚስብ የሚማርክ ውብ ገጽታ በመላበስ ላይ ነች፡፡ ይህ የመልካም ገጽታ እመርታ ግን በምን ይገለጻል ከምንስ የመነጨ ነው የሚለውን ማንሣት ግን አግባብ ይሆናል፡፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለምሥራቅ አፍሪካዊቷ ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ ያለው ትኩረት ከጊዜ ጊዜ ጨምሯል፡፡ የታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች መድረክ፣ የበርካታ ሀገራት መሪዎች የጉብኝት መዳረሻ፣ የታላላቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አጀንዳ እየሆነች ነው፡፡ ይህ የተለያዩ ኃይሎች ምላሽ ታዲያ ምክንያታዊ የመሆኑ ነገር የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች ማንሣት ይቻላል፡፡

 

ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት

 

‹‹ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ ካያችኋት ከአፍሪካ ትንሣኤ ጋር ተያይዘው ከሚነሡ ወሳኝ ሀገራት አንዷ እንደሆነች አስባለሁ›› ያለው የሲኤንቢሲ አፍሪካ (CNBC Africa) የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ጁሊያንስ አምቦኮ (Julians Amboko) ገለጻ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚስማማት ነው፡፡

ያለፉትን ዐሥር ዓመታት ብቻ ብንመለከት ኢትዮጵያ በአማካኝ ከ10 በመቶ ያላነሠ የኢኮኖሚ ዕድገት በየዓመቱ ስታስመዘግብ ቆይታለች፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ዕድገት ደግሞ ከ1983 .ም ወዲህ በሁሉም ወገን ተስፋ ተደርጎ የነበረውን የብልጽግና ተስፋ አለምልሞት በመታየቱ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በፊት እንደነበረው ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች፣ በጎ አድራጎት ላይ የሚያተኩሩ መንግሥታት እና የሰብአዊ ድጋፍ ተቋማት ከንፈራቸውን እየመጠጡ የሚጎበኙአት ሳይሆን በተመዘገበው ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት የተደመሙ ሚዲያዎች፣ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በረከት ለመጠቀም የቋመጡ ኢንቨስተሮች፣ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ልዑካን፣ ወዘተ ገባ ወጣ የሚሉባት ሀገር ሆናለች፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ኢኮኖሚስቶችና ታላላቅ ሚዲያዎች እየተቀባበሉ ‹‹የአፍሪካ አንበሳ›› ፤ ‹‹ከፍ ወዳለው የእድገት ደረጃ የምትሳብ የአፍሪካ ነብር›› እያሉ የሚያንቆለጳጵጿት ሀገር ሆናለች፡፡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በዓለም ላይ ካሉ አምስት እጅግ በጣም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቶች አንዱ የኢትዮጵያ ነው ማለቱ ይታወቃል፡፡ ሀገሪቱም መልካም ገጽታዋ እየተለወጠ ያለው በዚሁ ፍጥነት መሆኑ አይካድም፡፡

ከኢኮኖሚው ጋር ተያይዞ የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኢውጌኔ ኦውሱ (Eugene Owusu) ‹‹ኢትዮጵያ ለመልማት እየፈጠነች ነው፤ በዚህ የፍጥነት ምጣኔ ለማደግ ማሰብ ለሀገራት የማይቻል መስሎ ሊታያችሁ ይችላል፤ ይህ ግን ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን በራስ የመተማመን ደረጃ የሚያንጸባርቅ ነው፤ የፖለቲካ አመራሩን ጽኑ ፍላጎትና ትጋት የሚያሳይም ነው›› በማለት በቅርቡ የሠጡት አስተያየት ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉትንና ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ውይይት ያደረጉት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ አማካሪ የሆኑት አንድሪያ ሪችተር ሁም (Anedrea Richter Hume) የተመዘገበው እድገት ከፖሊሲው ትክክለኛነት የተነሣ መሆኑን አበክረው ሲገልጹ ‹‹እጅግ በፍጥነት የምታድግ አስደናቂ ልዩ ሀገር ናት፤ ሁሉም ፖሊሲዎች በተገቢው ሁኔታ የሚሠራባቸው ናቸው፤ ድርጅታችን ከኢትዮጵ መንግሥት ጋር ተባብሮ ለመሥራት ሁሌም ዘግጁ ነው›› ብለው ነበር፡፡

ኢትዮጵያ እጅግ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉት ከብራዚል፣ ከሕንድ ከቻይናና ራሺያ የኢኮኖሚ የእድገት ዘይቤ ጋር ዘርፍ ይዛ ትታያለች፡፡ ይህ ሁሉ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በእጅጉ እየለወጠው ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

በእርግጥም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አምስተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ የምትመራው ኢትዮጵያ ባላት ተስፋ ምክንያት በርካታ የውጪ ኢንቨስተሮች ልዑካን የሚጎኟት ሆናለች፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የሀገሪቱ የውጪ ኢንቨስትመንት በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ የሀገሪቱ መልካም ገጽታ የበለጠ እየተገነባ በመጣ ቁጥር መጠኑ እንደሚጨምር የሚጠበቅ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ 1ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት መሳብ የቻለች ሲሆን፤ እንደ ፋይናንሻል ታይምስ ግምት ደግሞ በዚህ ዓመት እስከ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት ልትስብ እንደምትችል አስቀምጧል፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ላይ 44 በመቶ የነበረው ድህነትም ባሳለፍነው ዓስርተ ዓመታት በተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት አሁን ላይ ወደ 30 በመቶ ወርዷል፡፡ መንግሥትም በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ የሚሌኒየም የልማት ግቦችን አሳክቶ ለመገኘት እየሠራም ነው፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት በጀት የሚመደበውም ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ እና መሠረተ ልማትን ለመሰሉ ድህነትን መዋጋት በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲውል ነው፡፡ የሥራ አጥነት ምጣኔውም እየወረደ ነው፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንጻር ሲታይ የአሜሪካን ዶላር ሚሊየነሮች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማማ የሚያደርጓት ከራሷ አልፎ ለጎረቤቶቿ በቂ ኃይል ማቅረብ የሚያስችላት ከፍተኛ የኃይል ልማት ፕሮጀክቶች፣ የመንገድና የባቡር ሐዲድ፣ የቴሌኮም ግንባታዎችን አከናውናለች፤ በመከናወንም ላይ ናቸው፡፡ የመጀመሪያውም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዚህ ዓመት ተጠናቆ፤ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሊተገበር በዝግጅት ላይ ነው፡፡

ይኸው ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሀገሪቱን በኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ከአሁኑም በተሻለ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ እንድትስብ የሚያደርግ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታትም በየዓመቱ ከ1 ቢሊየን ዶላር ያላነሰ ከኢንደስትሪ ልማት ዘርፉ ጋር ተያያዥ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ይውላል፡፡

የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ በዚህ ምክንያት እየተለወጠ በመምጣቱም የፋይናንስ ችግሮች ማነቆ እንዳይሆኑ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ነገር በመጽሔታችን ባለፈው ዕትም ላይ አስተያየት የሰጡት የጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ ዕቁባይ ሲናገሩ ‹‹ዓለም እያየንና እየጠበቀ ያለው ኢትዮጵያ በምስራቅ እስያ እንደሚገኙ አገሮች ትሆናለች ብሎ ነው፡፡ እኛ ከምንገምተው በላይ ነው ዓለም እያየን ያለው፡፡ ቀደም ሲል ስለ ኢትዮጵያ የነበረው ገጽታ ምንድን ነው ብንል ኢትዮጵያ የምትታወቀው በጦርነትና በረሃብ ነበር፡፡ አሁን ይሄ ተቀይሯል፡፡ አሁን በፋይናንስ ዙሪያ ለምሳሌ ከአሁን ቀደም ስንበደር የነበረው እንደ መንግሥት ሆነን ነው ብዙውን ብድር የምንወስደው፡፡ ከሌላ መንግሥት ዋስትና ሳያገኝ የሚበደረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ነው፡፡ በጣም ጥሩና አስተማማኝ ቁመና ስላለው፡፡ አሁን ግን የብድር አማራጮች ራሳቸው ሰፍተዋል፡፡ ከሀገሮችና ከተለያዩ አግዚየም ባንኮች እያገኘን ነው፡፡ ከቱርክ፣ ከሕንድ፣ ከቻይና ወዘተ እናገኛለን፡፡ ከአሜሪካ እናገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአሜሪካ አግዚየም ባንክ ዋስትና እየተሰጠው ነው የሚበደረው፡፡ ስለዚህ ይህ አንደኛ ሰፍቷል፤ ሁለተኛ በኮሜርስ ብድር መልክ የምንበደርበት አማራጭ እየሰፋ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ ከባቡር መስመሮች ስናይ ከአዋሽ እስከ ወልዲ ሀራ ገበያ ያለውን ቱርኮች ናቸው የሚሠራው ከቱርክ ድርጅት ነው፡፡ አንድ ቢሊየን ብር አካባቢ የተገኘው ክሬዲት ስዊ ከተባለ የስዊስ ባንክ ነው፡፡ ስለዚህ ስዊስ ብድሩን ሲያመጣ ከ5 እና ስድስት አገሮች የልማት ባንኮች ነው፡፡ ይህም ትልቅ ትርጉም ነው ያለው፡፡ ይህ ተበዳሪ አስተማማኝ ነው እተባልን ነው ያለንው፡፡ ቅድም እንደጠቀስኩት ባለፈው ለፓርኮች 750 ሚሊዮን ዶላር የመደብንው ከሸጥንው ዩሮ ቦንድ ነው፡፡ ስለዚህ ገበያ ሄደን መበደር የምንችልበት ዕድል አግኝተናል፡፡ በዚህ የመበደር አቅምም የቢ ፕላስ ሬቲንግ አግኝተኛል፡፡ ስለዚህ ብድር አማራጮች እየሰፉ ነው ያሉት፡፡ አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ፋይናንስ እንደ ማነቆ አይሆንም፡፡›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይሄንኑ ማሳያ በሚሆን መንገድም ኢትዮጵያ ባለፈው የበጀት ዓመት የተሳካ ዓለም አቀፍ የቦንድ ሽያጭ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ገበያ ማከናወኗ የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ሀገሪቱ በአኮኖሚ ልማት ውስጥ የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ስልትና በዚሁ ስልት የመልማት አቅም ከፍተኛ መሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራምን ጨምሮ በመላው ዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት የገባቸው ኃይሎች ሁሉ በአርአያነት የሚጠቅሱት አካሄድ ሆኗል፡፡ ይህ በመሆኑ የተገኘው መልካም ገጽታ ደግሞ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ልማቷ ደጋፊና ተባባሪ ለማግኘት ሰፊ ዕድል አስገኝቶላታል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስልቱ እንቅፋቶችን ለማስወገድ የአቅም ውስንነቶችን ለመቅረፍ የድርድር አቅሟን እንድታጎለብት አስችሏታል፡፡

 

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ

 

የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን መልክ በሁለት መንገዶች ለውጧል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ የሚያህል ግዙፍ ፕሮጀክት በራሷ የፋይናንስ አቅም ውጤታማ አደርጋለሁ ብላ እንደማትጀምር ብዙው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እያሰበ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በዚህ እርምጃ ውስጥ መግባታቸው ከዚያም አልፎ ደረጃ በደረጃ ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን ፕሮጀክቱን በየደረጃው በታለመለት ጊዜና ሁኔታ እያስኬዱት መሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ያለውን አመለካከት እንዲቀይር አስገድደውታል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱን ለማከናወን ብትወስን እንኳን የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ግብጽና ሱዳንን ማሳመን ላይ የማይቻላት መሆኑን ያስቡ የነበሩ አለም አቀፍ ወገኖች ነበሩ፡፡ እነዚህ ወገኖች የዚህ ግድብ ሥራ መጀመር እያስገረማቸው እያለ በዲፕሎማሲው መስከ ኢትዮጵያ ሱዳንንና ግብጽን በሰለጠን መንገድ ችግሮች እንዲፈቱ በጋራ ተጠቃሚነትና በመተማመን መንፈስ ተባብረው ለመሥራት መስማማታቸው ፕሮጀክቱ እንደተጀመረ ለፍጻሜው እንደሚደርስ ተስፋ ሰጥቷል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በአካባቢው ሀገራት እያገኘች ያለችው አመኔታና የምትከተለው ሥልጡን የዲፕሎማሲ ዘይቤ በዚህ በሕዳሴው ግድብ ላይ ጎልቶ በመውጣቱ ለሀገሪቱ መልካም ገጽታ መጎልበት አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል፡፡

 

ቱሪዝም የገጽታችን መስታወት

 

‹‹ኢትዮጵያ ፍጹም የሆነች የባህል ማእከልና የባህልቅርሶች ለማየት ለሚሹ ትክክለኛ መዳረሻ በእግዚአብሔርም የተመረጠች ሀገር ናት›› ይህ ቃል የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የፕሮፌሰር አንቶን ካራጌ (Anton Caragea) ቃል ነበር፡፡ ይህን የተናገሩትም እርሳቸው የሚመሩትና መቀመጫውን ሩማኒያ ያደረገው ምክር ቤት ኢትዮጵያን የ2015 የዓለማችን ምርጥ የቱሪስቶች መዳረሻ አድርጎ ከመረጠና ካበሠረ በኋላ የተናገሩት ነበር፡፡ እርሳቸው ባቀረቡት ሪፖርትም መሠረት ኢትዮጵያ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ኮሪያን የመሳሰሉ ሀገራት ያገኙትን ምርጥ የቱሪስት መዳረሻነት ክብር ተጎናጽፋለች፡፡

ኢትዮጵያ ይሄንን ስምና ከብር ያገኘችው በከንቱ አይደለም ሀገሪቱ ባላት ዕምቅ የቱሪዝም አቅም፣ የቱሪዝም ኢንደስትሪውን ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ በወሰደችው ማሻሻያ እርምጃዎችና ባላት ሰፊ የባህልና ታሪካዊ ቅርሶች ምክንያት ነው፡፡ ከዚሁም ጋር ተያይዞ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የአውሮፓ የቱሪዝም አካዳሚ የክብር አባልነት መዓረግን እንዲጎናጸፉ መደረጉ ይኸው ከመልካም ገጽታ ተገኝቶ ለመልካም ገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሽልማት ሆኗል፡፡

ይሄንኑ አስመልክቶ ብራስልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ተመርጣ ስሟ መናኘቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ውስጥ ያሉ ቱሪስቶች የጸጥታና ደህንነት ስጋት የሌለባቸውን በሰላም ጉዞ አድርጎ ለመመለስ የሚያመቹ በቂ ዕውቀትና ተመጣጣኝ ገበያና የቱሪዝም ዋስትና የሚያገኙባት ልዩ መዳረሻ መሆኗን አመልካች ሆኗል ሲል አስታውቆ ነበር፡፡ ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ካሉ አምስት ምርጥ የቱሪስት መዳረሻዎች ኢትዮጵያን አንዷ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ የቱሪዝምን ሴክተር በየጊዜው እያጎለበተች መምጣቷን የሚያሳየው በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የቱሪስቶች ፍሰትና ከዚያው ጋር ተያይዞም ሀገሪቱ እያገኘች ያለችው ገቢ መጨመሩ ነው፡፡ የቅርብ ጊዜውን ለውጥ እንኳን ለማስታወስ ብንሞክር በ2000 .ም ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት ቱሪስቶች ቁጥር 135954 (አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ሺ ዘጠኝ መቶ ሃምሳ አራት) የነበረ ሲሆን በ2005 ላይ 227398 (ሁለት መቶ ሃያ ሰባት ሺ ሦስት መቶ ዘጠና ስምንት ደርሶ ነበር)፡፡ በገቢም ረገድ በ2000 .68 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የነበረው በአምስት ዓመት ውስጥ ማለትም በ2005 .139599940 (አንድ መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ሚሊየን አምስት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺ ዘጠኝ መቶ አርባ) የአሜሪካን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድም (2002 እስከ 2007 .) 770000 (ሰባት መቶ ሰባ ሺ) ቱሪስቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን ከ2ነጥብ9 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ያላነሰ ገቢም ተገኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ያስባሏት ቅሪቶችን ፣ የአክሱምን ሐውልት፣ የፋሲል ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር ቤተክርስቲያን፣ የሐረር ጀጎል ግንብን፣ የኮንሶ የባህል መልክአምድር፣ የታችኛው የአዋሽና የኦሞ ሸለቆዎች የዓለም ቅርስ ሆነው በዩኔስኮ የተመዘገቡ መሆናቸው በዚህ ረገድ የሀገሪቱን መልካም ስም የበለጠ ማድመቂያ እየሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም የሰሜንና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች፣ የመልካ ቁንጥሬ ፓሊዎሎቲክ መካነ ቅርስ፣ የሼክ ሁሴን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርስ፣ የጌዴዎ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መልክአ ምድር፣ የሶፎሞር ዋሻን የመሳሰሉ ቅርሶች ሁሉ ከፍተኛ ቱሪስት ሳቢ መካነ ቅርሶች እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ በእርግጥም የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦም አድርጓል፡፡

በዩኔስኮ የተመዘገበውን የመስቀል ደመራ በዓልን ጨምሮ ጥምቀት፣ ኢሬቻ፣ ጨምበላላን የመሳሰሉ የማይዳሰሱ ቅርሶችም በየጊዜው የሚከበሩበት ሥርዓት ደማቅ እንዲሆን በመደረጉ የቱሪስት ስበቱን ጨምሯል፡፡ በከተሞች የሚዘጋጁ ልዩ ልዩ ዐውደ ርእዮችና የንግድ ትርኢቶች፣ የሥዕል ጋላሪዎች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ በመደራጀት ላይ ያሉ ሙዚየሞች ወዘተም ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ቱሪዝም ላይ አተኩረው ዘገባ የሚሠሩ ሚዲያዎች የሚያስተጋቡት ዕውነት ነው፡፡ እነዚህን ስበቶች መነሻ አድርገው ወደ ሀገራችን የሚጎርፉ ቱሪስቶች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ገቢ ለማግኘት ከመጥቀማቸውም ባሻገር የሀገሪቱን የመልካም ገጽታ እመርታ ከፍ በማድረግ በኩልም ድርሻ ነበራቸው፤ ይኖራቸዋልም፡፡

 

የመሠረተ ልማት መስፋፋት

 

ወደ ሀገራችን የሚመጡ ወገኖች የሀገራችንን ማንነት በውል ተረድተው ለሌሎችም እንዲያስረዱ ወደ ሀገራችን የሚመጡበት የጉዞ መሠረተ ልማትና በሀገር ውስጥ ሲቆዩ በምቾት የሚስተናገዱባቸው መሠረተ ልማቶች መስፋፋታቸው ለዚህ የመልካም ገጽታችን እመርታ ድርሻ አለው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የውጪ ሀገር እና የሀገር ውስጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ዕያደገና እየሰፋ መምጣት ኢትዮጵያን የሚጎበኙአትን ወገኖች ቁጥር ከፍ አድርጎታል፡፡ መጎብኘት ብቻ ሳይሆን ለኢንቨስትመንት፣ ለኤክስፖርት ገበያ ማበብ፣ ለኢትዮጵያ ምርቶች መታወቅና የሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ለውጥ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየታወቀ ለመምጣቱ ድርሻው የላቀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 91 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ 52 ያህሉ በአፍሪካ ናቸው፡፡ ወደ 24 የዓለማችን ከተሞችም የጭነት ማጓጓዝ አገልግሎቶችን መስጠቱ ለሀገሪቱ መልካም ገጽታ አስተዋጽኦ ማድረጉን መቀጠሉን ያሳያል፡፡ ይልቁንም ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ሆኖ መታየቱ ፓን አፍሪካኒዝምንም በማጠናከር ሀገራችን በአፍሪካውያን ዘንድ ያላትን መልካም ስም አስጠብቃ እንድትቆይ እያደረገ ነው፡፡

ሌላው ወሳኝ ለውጥ ደግሞ በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ መዝናኛ ስፍራዎች እየተስፋፉና በስፋት እየተገነቡ መሆናቸው ቱሪስቶችም ሆኑ ሌሎች እንግዶች የኢትዮጵያን ማንነት በጥልቅ ለመረዳት የሚያስችል፣ ያላትን ዓይነተ ብዙ ፍሬዎች ቀምሰው ለማጣጣም የሚያስችል ቆይታ እንዲኖራቸው እያደረጉ ነው፡፡ የሆቴልና የመዝናኛ አገልግሎቶች በዋጋ ተመጣጣኝ፣ በደረጃ ልዩ ልዩ ሆነው መገኘታቸውም እንግዶች እንዳሻቸው በየአቅማቸው ቆይታ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡

በሀገር ውስጥ የመንገድ ግንባታዎችና የባቡር መስመሮች በሰፊው እየተስፋፉ መሆኑ እስከ አሁን ከነበረውም በላይ በዚህ ረገድ ሰፊ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ከዓየር ጉዞ በመለስ ጎብኚዎች ውስጥ ለውስጥ ከጥግ እስከ ጥግ በመጓዝ የሀገራችንን የተፈጥሮ ባህል የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን እንዲጎበኙ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲያዩ ጥልቅ ጥናት አድርገው እንዲሰማሩ እያደረገ ነው፡፡

 

ስኬታማ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ

 

አፍሪካ በሰሜን፣ በምስራቅና በምዕራብ አካባቢዎቿ አልቃይዳን፣ አልሸባብን፣ አንሳርዲን፣ ቦኮሃራምን እና አይሲስን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች እየናጧት ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥም ሆነ በቀጣናው ያሉ የሽብር እንቅስቃሴዎችን በብቃት እየመከተች መሆኗ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አድናቆት እያተረፈላት ነው፡፡ ሀገሪቱ ሽብርን ለመከላከል የሚያስችል ሕግ አውጥታ፣ የጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በጥብቅ ተባብራ፣ የጸጥታና ደኅንነት ኃይሏን ዝግጁና በተጠንቀቅ የቆመ እንዲሆን በማድረግ ሽብርን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ ኢትዮጵያን በጥንካሬ ስሟ እንዲነሣ አድርጓል፡፡

ሌላው የኢትዮጵያን መልካም ስም እንዲገነባ ያደረገው የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ውስጥ ሀገሪቷ የድርሻዋን በአግባቡ መወጣት መቻሏ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ባገኙና ድርጅቱ በሚመራቸው የተለያዩ የሰላም ማስከበር ስምሪቶች ንቁ ተሳታፊ በመሆኗ በአራት የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ውስጥ በርካታ ወታደሮችን በማዋጣት በዓለማችን ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ በዳርፉር ባለው የሰላም ማስከበር ተልእኮ (UNAMID) በደቡብ ሱዳን አቢዬ ግዛት ባለው የሰላም ማስከበር ተልእኮ (UNISFA) እንዲሁም በላይቤሪያና ኮትዲቯር የሰላም ማስከበር ተልእኮ በመሰማራት አኩሬ ተግባር ፈጽመዋል እየፈፀሙም ነው፡፡ በዚህ ተግባርም ኢትዮጵያ የታወቀችና እምነት የሚጣልባት ሀገር መሆኗን አሳይታለች፡፡ እስከ አሁንም በአራት የሰላም ማስከበር ተልእኮ እስከ 7697 ወታደሮችን ማዋጣቷ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይህ በሰላምና ደኅንነት ፖሊሲዋ ያገኘችውን መልካም ስም አመላካቻ ነው፡፡

በቅርቡ የዓለም አቀፉ የሰላምና ልማት ተቋም በኢትዮጵያ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ጥናት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አበበ አይነቴ ‹‹ኢትዮጵያ ራሷን በአግባቡ ማረጋጋት የቻለች ሀገር ናት፤ ከዚህ በፊት የሰላም ማጣት ሰለባ ሆና የኖረች ሀገር ስለነበርች የሰላም ጥማት ያሰቃያት የነበረች ሀገር ስለነበረች የሰላምን ጥቅም ታውቃለች ለዚህም ነው በሌሎች ሀገራት የሰላም መቃወስ ሲደርስ ፈጥና በመድረስ ምላሽ የምትሰጠው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በሦስት ስልታዊ ጠቀሜታ ባለቸው የሰላም ማስከበር መስኮች ትሰማራለች የመጀመሪያው በቀጥታ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ፣ሁለተኛው ሸምጋይ በሆኑ ተልእኮዎችና በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ሽብርን ከምንጩ በማድረቅ የመከላከል ተልእኮ ነው…›› ብለው ነበር፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲሰጣት አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስፈላጊ በሆኑ አካባቢዎች የኢትዮጵያ የደኅንነት ኃይሎች ቁጥጥር እንዲያደርጉ ይፈቅድ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ በመተማመን ላይ የተመሰረት የሁለትዮሽ ግንኙነት ከሌሎች ሉዓላዊ ሀገራት ጋር እንዲኖራት አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ራሷን ከጦርነት የጸዳች ማድረጓ እንዳለ ሆኖ በሌሎች አካባቢዎች የሰላም ማስከበር ሂደት ውስጥ በመሳተፍ በጎረቤት ሀገራትና በዓለም ሰላም እንዲሰፍን የበኩሏን ሚና በመጫወት ሽብርንም በጽናት በመመከት ያስመዘገበችው ውጤት በመልካም ገጽታ ረገድ ላስመዘገበችው እመርታ አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

 

የውጪ ግንኙነቱ ፍሬያማነት

 

ኢትዮጵያ ባለፉት ሥርዐቶች ከውጪ ግንኙነት አንጻር የነበረባት ውስንነት ፖለቲካዊ መስመርን ወይም የኢኮኖሚ ሥርዐትን በብርቱ ተጽዕኖ በሚያሳርፉ ርዕዮተዓለማዊ ጎራዎች ወይም ቡድኖች ጋር የመለጠፍ ነበር፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የደርግ ሥርዐት ነው፡፡ ለሶቪየት ሕብረት የፖለቲካ ጎራ ገባሪ ስለነበር ለሌላው ዓለም የነበረው የግንኙነት ፖሊሲ የተዛባ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የምዕራቡ ዓለም ለኢትዮጵያ የነበረው አተያይ ጥሩ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ገጽታ በአሉታ እንዲሣል አስተዋጽኦ አድርጎ ነበር፡፡ ከጎረቤት ሀገራትም ጋር የነበረው ግንኙነት መልካም የሚባል አልነበረም፡፡ በጥርጣሬ የመተያየት የመጠላለፍ አንዱ በአንዱ ላይ የሚያሴርበት የግንኙነት ሁኔታ ነበር፡፡

እነዚህን ሁኔታዎች በመለወጥ፣ በሀገራችን ሰላም በማስፈንና የወደቀውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከመጠገን አንጻር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረባረብ በማግባባት የጀመረው ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ዛሬ ዛሬ ከተጠበቀው በላይ ለኢትዮጵያ መልካም ገጽታ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እጅግ መተማመን የሰፈነበት ለኢኮኖሚያዊ ውህደት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተመሠረተ ነው፡፡ በአፍሪካም ሀገሪቱ የነበራትን ተቀባይነት እጅግ በደመቀበት ሁኔታ የበለጠ እንዲያብብ አድርጓል፡፡ ሻዕቢያ ከሚመራው የኤርትራ መንግስት በስተቀር በዓለም ላይ ከእያንዳንዱ ሀገር ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እየታየ ነው፡፡

በዚህ ግንኙነት መሠረትም ሀገራት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ የሀገሪቱንም እርምጃዎች ያደንቃሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ ዓለማችን ተደማጭ መንግሥታት መሪዎች ሀገራችንን እየጎበኙ ነው፡፡ ከአውሮፓ ከምስራቅና ከምእራብ ሀገራት መሪዎች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድባቸው ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት እውቅና በሚሰጥ አግባብ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሰመረ ግንኙነት መስርተዋል፡፡

ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና በየመስኩ የሚሰሩ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶችም ከኢትዮጵያ ጋር አብረው እየሠሩ መሆናቸው ለሀገራችን መልካም ገጽታ ማበብ አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

ባለፈው እትማችን ለመጽሔታችን ማብራሪያ የሰጡት የውጪጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ደኤታ የሆኑት አቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ‹‹በዓለም ላይ ካሉ ሁሉም ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸው ሀገራት እጅግ በጣም ጥቂት ሀገራት ብቻ ናቸው፤ ይህ በእውነት ልዩ ነገር ነው፡፡ አሜሪካና ራሺያ ቢሳሳሙም ቢገፋፉም የእኛ ጉዳይ አይደለም፤ የማንንም ጥቅም አንነካም፤ እኛ የምናየው የራሳችንን አጀንዳ ብቻ ነው፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የሄደበት ርቀት ተአምር ነው፡፡›› ማለታቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡

 

የዲፕሎማሲ ማእከል

 

ኢትዮጵያ ትናንት የአፍሪካ አንድነት መቀመጫ ሆና ከነበራት የዲፕሎማሲ ማእከልነት በጎላ መልኩ አንድነት ድርጅቱ ሕብረት ከሆነ በኋላ የበለጠ የደመቀ ሆኗል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ወሳኝ የስራ ክፍሎችና ሌሎችም የፓን አፍሪካ ተቋማት ሁሉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የሁሉም አባል ሀገራት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ (PRC)፣ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤቱ (PSC)፣ የአፍሪካ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኮሚቴ (CISSA) ይገኛሉ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ብርጌድ ዋና መሥሪያ ቤት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል የሎጂስቲክ ማእከል፣ የፓን አፍሪካ የንግድ ቻምበር እና የመሳሰሉትም በአዲስ አበባ የከተሙ ናቸው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችም ማስተባበሪያዎቹ በዚሁ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማእከልነቷ የተረጋገጠና በየጊዜውም እየደመቀ የመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኢጋድ፣ በሳዴቅና በኔፓድ በመሳሰሉ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ረገድ ባሉ የትብብር መድረኮች ሁሉ ጉልህ ሥፍራ ይዛ መገኘቷ በሀገሪቱ የተለያዩ ጉባኤዎች የሚካሄዱባት የዲፕሎማሲ ማእከል እንድትሆን አድርጓታል፡፡

በየዓመቱ የሚዘጋጀው የህብረቱ የመሪዎችና የሚንስትሮች ጉባኤ፣ የህብረቱ ልዩ ልዩ ክፍሎችም የሚያዘጋጇቸው ባለሙያዎችን ታዋቂ ሰዎችና ዲፕሎማቶችን የሚመለከቱ ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ሁሉ የአዲስ አበባን የአፍሪካ መዲናነት እያጎላው ነው፡፡ የአፍሪካ ደራሲያን ጉባኤ፣ የአፍሪካ የሚዲያ አመራር ጉባኤ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ጉባኤዎች መደረጋቸው ይታወቃል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንም (UNECA) እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ጽሐፈት ቤት በአፍሪካ በተመሳሳይ በዚህ በአዲስ አበባ መከተማቸው ሀገራችን ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆንና ገጽታዋ መልካም ሆኖ እንዲታይ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከመቶ በላይ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችም በአዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡

ሌሎች የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የቻይና የህንድ የብራዚልና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ልዩ አካላት፣ ሌሎችም የዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅቶችና የሰብአዊ ጉዳይ ድርጅቶች ወኪሎችም በዚህችው ከተማ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ ከፓን አፍሪካን ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ብቻ በየዓመቱ በአማካይ ከ1100 ያላነሡ ልዩ ልዩ ደረጃና መጠን ያላቸውን ስብሰባዎች የማስተናገድ ዕድል እያገኘች ነው፡፡ በጥር ወር ላይ በሚዘጋጀው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ስብሰባ ብቻ ከ40 ያላነሡ የሀገራት መሪዎችንና ከ7200 ያላነሱ ልዑካንን ታስተናግዳለች፡፡

ይህ ነገር ግን በአህጉር ደረጃ ሳይወሰን ታላላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችም የሚዘጋጁባት ሀገር እንድትሆን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተመራጭ እየሆነች መምጣቷ ያላት መልካም ገጽታ መልካም እየሆነ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ለዚህም እ... 2011 ህዳር ወር ላይ በአዲስ አበባ የተዘጋጀው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽን፣ በርካታ ሳይንቲስቶች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትን ጨምሮ 10.000 (ዐሥር ሺ) እንግዶችን በማስተናገድ ሰፊ ከነበረው የኤድስና ሌሎች ተላላፊ የአባላዘር በሽታዎች ጉዳይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአፍሪካ (ICASA) መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቅርቡ የተደረገውም ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤም ከ200 ያላነሱ የሚዲያ ሰዎችን፣ የሀገራት መሪዎችን ከፍተኛ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ባለሙያዎችንና ባለሥልጣናት ጨምሮ እስከ እስከ አስር ሺ እንግዶች አዲስ አበባ እንድታስተናግድ መደረጉ ሀገሪቱ እያገኘች ያለችውን ክብር የሚያሳይ ሲሆን በተለያዩ መልኮች ተጠቃሚም እንድትሆን አድርጓታል፡፡ እንዲህ መሰል ጉባኤዎች እየተዘወተሩ መምጣታቸውም አዲስ አበባን ኒውዮርክ ሎንደንን ከመሰሉ ተዘውታሪ የዓለም አቀፍ ጉባኤ መዳረሻዎች ተርታ የሚያስመድባት ሆኗል፡፡

 

ሌሎች ለገጽታችን መልካምነት አስተዋጽኦ ያደረጉ ጉዳዮች

 

እጅግ የበለጠ ሊሠራባቸው የሚገቡ ቢሆንም በስፖርትና በባህል ልማት ረገድ የሚሠሩ ተግባራትም አስተዋጿቸው የሚናቅ አይደለም፡፡ አረንጓዴው ጎርፍ በመባል የሚታወቀው የአትሌቲክስ ቡድናችን ዋልያዎቹና ሉሲዎቹ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ቦታ እያገኙ መምጣታቸው አትሌቶቻችን በዓለም አቀፋዊ ውድድሮች አሸናፊ ሆነው ባንዲራችንን ከፍ ከፍ ባደረጉ ቁጥር የኢትዮጵያን ማንነት በማስተዋወቅና የበለጠ ክብር እንድታገኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡

በተለይ የአትሌቲክሱ ዘርፍ እያስመዘገበ የነበረው ውጤት ከአትሌቶቻችን ጋር የኢትዮጵያን ስም ከፍ ከፍ ያደረገ ነበር፡፡ እነዚህኑ የስፖርት ዘርፍ የውድድር ዓይነቶች እየሰፉ ቢሄዱና በእግር ኳሱም የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ጥረቶች እንዲጠናከሩ ቢደረግ ከውድድር ስፖርት ሽልማቶች ከሚገኘው የውጪ ምንዛሪ ሌላ በሀገር ውስጥ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማዘጋጀትን ዕድል ሰፊ ስለሚያደርግ የበለጠ ተጠቃሚና የመልካም ስም ባለቤቶች ሆኖ መቀጠል ይቻላል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን የመሰሉ ውድድሮችም መስፋት ከቻሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎችን ወደ ኢትዮጵያ መሳብ ይቻላል፡፡ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረትም የሚስብ ስለሚሆን ለገጽታ ግንባታው እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ ማሳደግ ይቻላል፡፡

በተመሳሳይ በሌሎች የባህል ልማቶችም ከመላው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውስጥ ያሉ ማራኪ የባህል እሴቶችን ይዞ በመገኘት ከቱሪዝም ልማት አንጻር ከገጽታ ግንባታ አንጻር ፍሬ እንዲያፈሩ ማድረግ ከተቻለ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ጎዳና ላይ መሆኗን ሁሉም ወገን ማረጋገጥ ይችላል ማለት ነው፡፡

 

እንደ ማሳረጊያ

 

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የምትታይበትን ገጽታ መልካም በማድረግ በኩል ድርሻ ያለው መንግሥት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ ነው፡፡ ትናንት በነበረው ሂደት ለተመዘገበውም ለውጥ ባለቤቱ መንግሥትና ሕዝብ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ሊመጣ ለሚገባው የተሻለ ውጤት ባለድርሻ የሚሆነው ሁሉም ወገን ነው፡፡ መልካም ገጽታ የመገንባቱ ጥረት የተጀመረ እንጂ ያለቀ አይደለም፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ መንግሥት ከዜጎች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ከላይ ባነሣናቸውን በሌሎችም ሴክተሮች የተሻለ አፈጻጸም ማሳየት ሲችል ነው፡፡ በአንድ በኩል ለመልካም ገጽታ ግንባታ ያሉንን እምቅ አቅሞች መጠቀም ነው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን መዲና መሆኗን በሚፈለገው ደረጃ ልትጠቀምበት የሚገባ ነው፡፡ አፍሪካውያን በእርግጥም ሁለተኛ ሀገራቸው እንደሆነች የምር እስኪሰማቸው ድረስ ዐውዱን ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ከማህበረሰባችን አስተሳሰብ ጀምሮ አገልግሎት መስጫዎችን ምቹና አፍሪካን አፍሪካን እንዲሸት ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎችም ከብዙ ነገሮች አንጻር ያሉንን አቅሞች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አደራጅቶ ለገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት ማዋል ከሚመለከታቸው ሁሉ ይጠበቃል፡፡

በሌላ አንጻር ደግሞ አሁንም መልካም ገጽታችንን የሚፈታተኑ ጉዳዮችን ለይቶ የሀገርን ገጽታ እንዳያጠለሹ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ የሆነውን ሕገወጥ ስደትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ ዜጎች በሀገራቸው ሠርተው የሚለወጡበት፣ የተረጋጋና ደስተኛ ሆነው የሚኖሩበት ሀገራዊ ዐውድ እንዲፈጠር ማድረግ ግድ ነው፡፡

 

አዘጋጅ ማለደ ዋስይሁን

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137298
TodayToday109
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week9
This_MonthThis_Month3380
All_DaysAll_Days137298

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።