የቀደሙቱ ዳያስፖራዎች ሌሎችን ይጠራሉ Featured

03 Sep 2015

ለረጅም ጊዜያት አሜሪካ ኖሯል፡፡ ከአገር የወጣው የደርግ ሥርዓት ካስከተለበት የስጋት ሕይወት ለመዳን ሲሆን፤ አወጣጡም በሱዳን በኩል ነው፡፡ አሜሪካ ሄዶ ተማረም ሰራም፡፡ ነገር ግን ዘወትር የአገሩ ነገር እንቅልፍ ይነሳው ነበር፡፡ በተማረው ሙያ አገሩን ለማገልገል የሚችልበትን ጊዜ ሲናፍቅ ኖሯል፡፡ ዛሬ አዲስ ቴክኖሎጂ የሆነውን የፋይበር ግላስ ቴክኖሎጂ በማስፋፋት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ ለሴከንድ እንኳ ጊዜ የለውም፡፡ ቴክ ፋይበር ግላስ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ደረጀ ብርሌ የዘመን እንግዳችን በመሆን ያወጋንን እነሆ ብለናል፡፡

ዘመን፡- አቶ ደረጀ የት ተወልደህ አደግህ?

አቶ ደረጀ፡- የተወለድኩት ጐንደር አዘዞ ከተማ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1962 .ም ነው። ዕድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ እዚያው አዘዞ አፄ ፋሲል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማርኩ። በዚያን ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እዚያ ባለመኖሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጐንደር ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ተምሬአለሁ። ከዚያ በኋላ በአባቴ ድርጅት ውስጥ በሹፍርና እሠራ ነበር። ጊዜው ለወጣቶች ጥሩ ስላልነበረ በኋላ ላይ በሱዳን አድርጌ ወደ አሜሪካ ተሰደድኩ። እናም በ1984 .ም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ካሊፎርኒያ ገባሁ። እዚያ እንደደረስኩ ቀጥታ ወደ ትምህርት ቤት ነበር የገባሁት። ያው እንዳልኩህ አገሬ እያለሁ በቴክኒክ ሙያ ላይ ስለነበርኩ የቴክኒክ ትምህርት ቤት ነው የገባሁት። ትምህርት ቤቱ ግሊንደል ኮሙኒቲ ትምህርት ቤት ይባላል። እዚያ የአውሮፕላን (air craft) ጥገና ሥራ አሠልጥነው የሙያ ፍቃድ ይሰጣሉ። ይሄን ትምህርት ተምረህ ፍቃድ ሲሰጡህ የትኛውም የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ መሥራት ትችላለህ። በዚህ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ነው ያገኘሁት። ከዚያ በሙያው ተሰማርቼ ስሰራ ቆይቼ በኋላ ሥራው ስላልተመቸኝ ተውኩት፡፡ ሥራው በአብዛኛው ጐማ፣ ፍሬንና የመሳሰሉትን ማጽዳት በመሆኑ ብዙም ሊያሳድገኝ እንደማይችል ስለተረዳሁ ተመልሼ ወደ ትምህርት ዓለም ገባሁ።

ኖርትሮፕ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ በኤሮስፔስ ኢንጅነሪንግና ኤርክራፍት ማኑፋክቸሪንግ አጥንቼ በሁለቱም ተመረቅሁ። በልጅነቴ ጐበዝ ስለነበርኩ ገና ትምህርቴን ሳልጨርስ አሜሪካ ውስጥ የታወቀ የመከላከያ አውሮፕላን የሚያመርት ኖርትሮፕ የሚባል ኩባንያ ተቀጠርኩ። ኩባንያው F18ና ሆርኔት የሚባሉ አውሮፕላኖችን ያመርት ነበር። እዚያ በኢንጅነሪንግ የሥራ ክፍል ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። አሁን የምሠራውን የፋይበር ግላስ ሥራ እዚያ ኩባንያ ውስጥ ነው የለመድኩት። እዚያ በተለያዩ የሥራ መስኮች እየተዘዋወርኩ ሰራሁ፡፡ በተለይ የኮምፖዚት ሥራን እዚህ ነው የለመድኩት፡፡ ኮምፖዚት የሚባለው ንጥረ ነገር ከፋይበር ግላስ በጣም የተሻለ የማዕድን ዓይነት ነው። በጣም ውድና ለአውሮፕላን ሥራ የሚጠቀሙበት ነው። ለመኪናና ለጀልባ ሥራም ይውላል። ቴክኖሎጂው ከፋይበር ግላስ ጋር ተመሳሳይ ነው። የማዕድኑ ዓይነት ነው ልዩነቱ። እዚያ ኩባንያ ውስጥ በኢንጅነሪንግ ሙያ እየሠራሁ እያለሁ በአጋጣሚ ወደ አስተዳደር ሥራ አዛወሩኝ። በዚህ አጋጣሚ ዕድሉን አግኝቼ ብዙ የሥራ ክፍሎች ውስጥ እዘዋወር ነበር። እንደሚታወቀው አውሮፕላን የሚሠራው ከአልሙኒየም ነው። እዚያ ኩባንያ ውስጥ ግን ከ70 እና 80 በመቶ በላይ በኮምፖዚት ነበር የሚሠራው፡፡ እና በዚያ አጋጣሚ ኮምፖዚት ንጥረ ነገር እንዴት እንደሚሠራ? ምን ላይ እንደሚሠራ? አወቅሁ። በዚህ ዘርፍ ጥሩ ዕውቀት ገበየሁ። የዚያን ጊዜ እኔ ወደ አገሬ የመመለስ ፍላጐቴ ከፍተኛ ነበር። እናም በመሐል አገሬን ሄጄ ማየት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ያኔ ደርግ አልወደቀም ነበር ግን የፈለገውን ያድርገኝ ሄጄ ማየት አለብኝ አልኩ። እንግዲህ አሜሪካ አገር ትላልቅ ኩባንያዎች ውስጥ ስትሠራ እንዲህ ዓይነት የጉዞ ፕሮግራም ስታደርግ ከ6 ወር በፊት አሳውቀህ ፕሮግራም ትይዛለህ። እናም ለኩባንያው አስተዳደር በቃ አገሬን ሄጄ ማየት አለብኝ ብዬ ፕሮግራም ያዝኩ።

በፕሮግራሜ መሠረት ልክ ልመጣ ሁለት ሳምንት ሲቀረኝ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ገባ። ያኔ አስታውሳለሁ ከአሁኗ ባለቤቴ ጋር ጓደኛሞች ነበርን። ወንድሞቼ ወደሚኖሩባት ካናዳ እየተጓዝን እያለን መንገድ ላይ ደርግ እንደተወገደና ኢህአዴግ አገሪቷን እንደተቆጣጠረ ሰማን። ቀደም ሲል ዝም ብዬ በጨለማው ፕሮግራም ይዤ ቲኬት ቆርጫለሁ እና ምንድን ነው የማደርገው? ስል አሰብኩ። ፕሮግራሜን አልሰርዝም አልኩ። እና ኢህአዴግ በገባ በሁለተኛው ሳምንት አገሬ መጣሁ። በወቅቱ አንዳንድ ነገሮች ያልተረጋጉ ነበሩ። ግን በጣም ጥሩ ጊዜ አሳለፍኩ። እንግዲህ ወደ አገሬ የመመለስ ጉጉቴ ጨመረ። አገሬ እንደመጣሁ ብዙ ፒክ አፕ መኪኖች አየሁ፡፡ እነኚህ እኮ ኬሪቦይ ቢገጠምላቸው ጥሩ መኪና ይወጣቸዋል ብዬ አሰብኩ። ደግሞ በየቦታው የውሃ ታንከሮች በየቤቱ ተሰቅለው አየሁ። ግን በጣም የዛጉ ነበሩ። እና ይሄንንም በሌላ መቀየርና መሥራት ይቻላል የሚለው ሃሳብ መጣልኝ።

ዘመን፡- ይሄ ሃሳብ የመጣልህ አዲስ አበባ ከመጣህ በኋላ ነው ወይስ አሜሪካ እያለህ ነው ?

አቶ ደረጀ፡- እዚያ እያለሁ የመምጣቱ ሃሳብ ብቻ ነው የነበረኝ። ከመጣሁ በኋላ ነው ይሄ ሃሳቡ የመጣልኝ፡፡ እና ይሄንን ሃሳብ ይዤ ወደ አሜሪካ ተመለስኩ። ከዚያ በኋላ ከባለቤቴ ጋር በ1992 እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ለጋብቻ ወደ አገራችን መጣን። በአጋጣሚ ሠርጋችን አዲስ አበባም ጐንደርም ነበር። ከሠርጉ በኋላ እርሷም ያለውን ሁኔታ አየች። ሃሳቤን ነገርኳት። ገንዘብ ባይኖረንም ዕውቀት አለን። እርሷ የጥርስ ሐኪም ናት። እኔ ኢንጅነር ነኝ፡፡ እና አገራችን ተመልሰን በሙያችን ለምን አንሠራም? አልኳት። ተስማማች፡፡ ከሠራን ሠራን ካልሠራንና ካልተስማማን ልጆች ነን ተመልሰን አሜሪካ እንሄዳለን ተባባልን። አሜሪካም የገዛነው ቤት ነበረን። እሠራበት የነበረው ኩባንያ ሊለቀኝ አልፈለገም። በኋላ ውሳኔዬን ሲረዱ እንዴት እንርዳው? ብለው በጣም ረድተውኛል። የረጅም ጊዜ ጊዜአዊ ስንብት ሰጡኝ። ይሄንን ዕድል በዚያ ትልቅ ኩባንያ ውስጥ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። ይሄ ጥቅሙ በተመለስኩ ጊዜ ያለምንም ችግር ወደ ሥራዬ መግባት እንድችል ያደርገኛል። ያኔ የመጣሁ ጊዜ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ኃላፊው አቶ ታደሰ ኃይሌ ነበሩ። በጣም ረዱኝ። ወደ አገሬ ገብቼ እንድሰራ ያበረታቱኝ ነበር። እንደመጣሁም ሥራዬን በተመለከተ ኤግዚቢሽን አዘጋጅቼ እንዳሳይ ነገሩኝ፡፡ ከዚያ ኢምፔሪያል ሆቴል በጣም ተባብሮኝ የማሳይበት ቦታ በነፃ ሰጥቶኝ ኤግዚቢሽኑን አሳየሁ። ጉዳዩ በሚዲያ ሁሉ ተላለፈ፡፡ ብዙ ሰውም ጐበኘው። ብዙዎቹ ባዩት ነገር ተገርመው ነበር።

ዘመን፡- በኤግዚቢሽኑ ላይ ያቀረብከው ምን ነበር?

አቶ ደረጀ፡- አሁን የምሠራውን የፋይበር ግላስ ሥራ ነበር ያቀረብኩት። የውሃ ታንከር፣ ኬሪቦይ (ፒክ አፕ መኪና ላይ የሚገጠም)፣ የባኞና የሻወር ዕቃዎችን ወዘተ...ነበር ያቀረብኩት፡፡ የሁሉም ሃሳብ የሚያበረታታ ነበር። እናም የመጀመሪያውን ሥራዬን ያሰራኝ ፖስኩዋ ጁሴፔ የሚባል ዮሴፍ አካባቢ ያለ የኢጣሊያ የብረት ኢንዱስትሪ ነበር። ጣሊያኖች ናቸው፡፡ ይሄንን ቴክኖሎጂ እነርሱም መሥራት ይፈልጉ ነበር። ይሄን ነገር በሚዲያ ሲሰሙ በጣም ተገርመው ማታውኑ እኔ ጋ መጡ። አብረንህ ልንሠራ እንፈልጋለን አሉኝ።

እነርሱ የእዚሁ አገር ተወላጅ ጣሊያኖች ናቸው። የሚሠሩት ሥራ ከነዳጅ ማደያ ጋር የተገናኘ ሥራ ነበር። ለምሳሌ የነዳጅ ማደያ ካኖፒ፣ የነዳጅ ታንከርና የመሳሰሉትን ይሠሩ ነበር። ውጭ አገር እነዚህ የነዳጅ ማደያዎች ብዙ ነገራቸው ለምሳሌ ካኖፒው፣ ሴሊንጉ፣ ጥላው፣ መብራቱ፣ ማደያ መሸፈኛው ሁሉ በፋይበር ግላስ ነው የሚሠራው። እና እነዚህ ሰዎች ያለ ምንም ፕሮጀክትና ፕሮፖዛል ቀጥታ ሰባራ ባቡር ፒያሳ አካባቢ የነበረ ትንሽ ቶታል ነዳጅ ማደያ እንድሠራ ሰጡኝ። አሁን ምናልባት በመንገድ ሥራው ፈርሶ ይሆናል እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቀለም ብቻ ነበር የሚቀቡት። ይህ ማደያ ለሃያ ዓመት ምንም ሳይሆን አገልግሏል። የመጀመሪያው የፋይበር ግላስ ሥራዬ ይህ ማደያ ነው። ከዚያ በኋላ ይሄን ሥራዬን አይተው ሌላ የማደያ ዲዛይን ሰጡኝ። ወደ መገናኛ አካባቢ ሠራሁ። በኋላ በዚሁ ሥራ ሐዋሳ ጐንደርና ብዙ ቦታ ሠራሁ። መሬት ውስጥ የሚቀበሩ የነዳጅ ታንከሮች እንዳይዝጉና ቀዳዳ እንኳን ቢኖራቸው እንዳያፈሱ በፋይበር ግላስ ይጠቀለላሉ። በኋላ ሼል ኢትዮጵያ ይሄንን እንድትሠራልን ደቡብ አፍሪካ ሄደህ ሠርተፊኬት ይዘህ መምጣት አለብህ አሉኝ። እዚያ ሄጄ የሚያስፈልጉትን መሥፈርቶች አሟልቼ መጣሁ። ከዚያ ለሼል ኢትዮጵያ ይሄን ሥራ ሠራሁላቸው። የካኖፒ ሥራም ሠራሁላቸው። በኋላ ኦይል ሊቢያ ሆነ አብረን ሠራን። ኖክም መጣ፡፡ እዚህም መሬት የሚቀበሩ የካኖፒ ሥራ ሠራን። እስካሁንም እየሠራን ነው።

እነዚህን ሥራዎች ከሠራሁ በኋላ አሜሪካ ተመልሼ እሠራበት ለነበረው ኩባንያ መልቀቂያዬን አስገባሁ። ከባለቤቴ ጋር ተነጋገርን፡፡ ሁኔታዎችን አመቻችቼ ተመልሼ መጥቼ እንደምወስዳት ነገርኳት። ተስማማን። ያኔ መጣሁ። ተመልሼ ወደ አሜሪካ ሄጄ አላውቅም።

ዘመን፡- ስንት ዓመት ሆነህ ከመጣህ?

አቶ ደረጀ፡- በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1996 .ም ነው የመጣሁት። እንደመጣሁ ቀጥታ ወደ ሥራ ነው የገባሁት። ቴክኖሎጂው አዲስ ነበር። የሥራ ዘርፉም ሰፊ ነው። በእርግጥ የሥራውን ሁኔታ ለማስገንዘብ መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። ምክንያቱም ኅብረተሰቡ ከለመደውና ከነበረበት ሁኔታ ለመውጣት የማዝገም ነገር ነበር። እንደአሁኑ ቶሎ አልተቀበለውም ነበር። ያኔ እንግዲህ ቦታም አልነበረኝም። ቤት ተከራየሁ። እዚያው የተከራየሁበት ቤቴ ነበር ሥራውን የጀመርኩት። በዚያን ሰዓት በመንግሥትም የተቀረፁ ፖሊሲዎች አልነበሩም። ፍላጐቱ አለ ግን እንቅስቃሴውና እውቀቱ አልነበረም። በኋላ ማዘጋጃ ቤት ሊዝ ቦርድ ሄጄ ተመዘገብኩ። ቦታ ለመውሰድ ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር። እውቀቱ ስለሌለ እንጂ ቦታ ያለመስጠት መፈለግ ጉዳይ አይደለም። ሥራው ሁሉ አንድ ቦታና አንድ ላይ ነበር የሚሠራው። ኢንቨስተሩም ሌላውም አንድ ላይ ነበር የሚስተናገደው። እኔ ግን ያኔ ቆርጬ ስለመጣሁ ምንም አልተሰማኝም። በኋላ ይሄ አሁን የምሠራበት ቦታ በ1993 እንደ እኛ አቆጣጠር በሊዝ ተሰጠኝ። ይሄን ድርጅት አቋቁሜ መሥራት ጀመርኩ። ከዚህ በኋላ ሥራው እየሰፋና ከአቅም በላይ እየሆነ መጣ። ያኔ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ነበርና የእኔን አመጣጥ የሰሙ ሰዎች አየር ኃይል በትንንሽ ብልሽት ምክንያት ሥራ ያቆሙ አውሮፕላኖችንና ሄሊኮፕተሮችን እንድጠግን አዘዙኝ፤ ሠራሁ። ከዚያ በሙያዬ ከአየር ኃይል የሥራ ግብዣ መጣልኝ። የጥገና ሥራዎችን ሠራሁ። በኋላ የሥራው ጫና እየበዛ መጣ። እነርሱ እዚያው ጠቅልዬ እንድሠራ ነበር ፍላጐታቸው። እኔ ደግሞ ከአሜሪካም ስመጣ የነበረኝ ራዕይ በኢንቨስትመንቱ የመሰማራት ነበር። ብቃት ያላቸውን አንድ አሥር አሥራ አምስት ሰዎችን አዘጋጁልኝ አልኳቸው። ቦታም ሰውም አዘጋጁልኝ። ከዚያ ወርክ ሾፕ ነገር አቋቁሜ ለሁለት ዓመት እውቀቴንም ጊዜዬንም መስዋዕት አድርጌ አሠለጠንኩላቸው። አሁን የፋይበር ግላስ ወርክ ሾፕ አላቸው። ሠልጣኞቹ ከዚህም ሌላ የሲቪል ሥራዎችንም እየሠሩ ነው ያሉት። አልፎ አልፎ ጥያቄ ሲኖራቸው እየተገናኘን ድጋፍ እሰጣቸዋለሁ። አሁን ሙሉ ጊዜዬን እዚህ ሥራዬ ላይ ነው የማሳልፈው። ለብዙ ሰውም የሥራ ዕድል ፈጥረናል። ሥራውንም እያሳየናቸው ነው። እንዲያውም ብዙ ልጆች ከእዚህ ወጥተው የራሳቸውን ተመሳሳይ ድርጅት የከፈቱም አሉ።

ዘመን፡- በድርጅትህ ውስጥ ስንት ሠራተኞች አሉ?

አቶ ደረጀ፡- በአሁኑ ሰዓት ወደ 42 ሰራተኞች አሉን። ሥራው ጨምሮ በሚመጣበት ጊዜ የሰው ኃይሉ እስከ 70 እና 80 የሚደርስበት ሁኔታ አለ።

ዘመን፡- በዋናነት የምታመርቷቸው ምርቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ደረጀ፡- በከተማ ውስጥ በብዛት በየቤቱና በየድርጅቶች ውስጥ የሚታዩ የውሃ ታንከሮች፣ የመኪና አካል (body)፣ ብርሃን አስተላላፊ የጣሪያ ቆርቆሮዎች፣ የተለያዩ ጀልባዎች፣ የባኞና የሻወር ቤት ዕቃዎች፣ ሲንኮች ወዘተ... ናቸው። አብዛኛዎቹ እነኚህ ዕቃዎች ከውጭ የሚገቡ ነበሩ። ቅድም ያልኩህ ፒክ አፕ መኪኖች ላይ የሚገጠም ኬሪ ቦይም እንሰራለን። ለብዙ ድርጅቶች ገጥመንላቸዋል። ትልልቅ የገልባጭና የጭነት መኪናዎች አሁን አሁን የተለያዩ አካሎቻቸው የሚሰሩት ከፋይበር ግላሰ ነው። እነኚህ መኪኖች ሲጋጩ ዕቃዎቻቸው ከውጭ ነው የሚመጣው። አሁን ግን እኛ መሥራት ጀምረናል። ስለዚህ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች እኛ ነን መኪኖችን የምንጠግንላቸው። እንደ አዲስም ሰርተን እንሰጣቸዋለን።

ዘመን፡- አሁን ያለው የአገራችን ሁኔታ ዳያስፖራውን የሚያበረታታ ነው? እንዳንተ ያሉ በውጭ የሚኖሩ ዜጐቻችን ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን ይዘው መጥተው ለአገርም ለራሳቸውም አስተዋፅኦ ማበርከት የሚያስችላቸው አበረታች ሁኔታ ተፈጥሯል?

አቶ ደረጀ፡- ከእኔ ብጀምር ጥሩ ነው። እኔ በመጣሁበት ጊዜ ዳያስፖራ የሚባል ስምም አልነበረም። እኔ በመጣሁበት ጊዜ ምንም ፖሊሲም አልነበረም። የተለየ ነገር አልነበረም። ውሃና መብራት ለማስገባት ከኅብረተሰቡ ጋር ተሰልፈህ ነው። በጣም ከባድ ነበር። ይሄን ሁሉ አልፈን ነው ዛሬ የደረስነው። አሁን መንግሥት ከተለያዩ ነገሮች ተምሯል። በተለያዩ ጊዜአት በተካሄዱ የምክክር መድረኮችና እኛ በሰጠነው አስተያየት ነገሮች ተመቻችተዋል። አሁን መንግሥት በራሱ የኢንዱስትሪ መንደር አዘጋጅቷል። መሠረተ ልማት ተዘጋጅቶ ኑና ሥሩ የሚባልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። በተለያዩ ቦታዎች የኢንዱስትሪ መንደር ተብሎ መሥሪያ ቦታ ሳይቀር ተዘጋጅቶ በሊዝ ገዝተህ የመሥራቱ ሁኔታ የተመቻቸ ነው። እና እኔ የሄድኩበትን አካሄድ ብታየው ፈታኝ ነበር። በእርግጥ እኔን አበረታቶኛል። እና አሁን ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። መሥራት የሚፈልግ ሰው እንደአቅሙ መጠነኛ ቦታ ተከራይቶ መሥራት ይችላል። ሰፋፊ መሬት ወስደህ ሳይሆን ትንሽ ቦታ ተከራይተህ አነስተኛ ኢንዱስትሪ ከፍተህ መሥራቱ ነው የሚያዋጣው። በዚህ ዘርፍ በብዙ የሚቆጠር ሥራ ሞልቷል፤ ለሚሠራ ሰው። ውጪ ያሉ ወንድሞቻችን መጥተው ቢሰሩ በጣም ብዙ የሥራ ዘርፍ አለ። መንግሥት በሰጣቸው ዕድል እየተጠቀሙ ነው። ለምንድን ነው የእኛ ልጆች እነርሱ የሚሰሩትን ሥራ መጥተው የማይሰሩት? ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ። እና የእኔን እህቶችና ወንድሞች ጨምሮ የዳያስፖራው አባላት ቢመጡ አገራቸውንም ራሳቸውም ይጠቅማሉ። ብዙዎቹ እዚያ ያሉት ወገኖቻችን ሃሳባቸው እዚህ ነው። ግን ለመምጣት የሚይዛቸው የፖለቲካ ጉዳይም ጭምር ነው።

ነገሮችን ከፖለቲካ ጋር ሳታያይዝ ሥራህን መሥራት። የምትሰማራበትን ዘርፍ ማቅረብ። አይተህ ካልተመቸህ እንኳን መመለስ ትችላለህ። እኔ ለወንድሞቼ እንኳን የተለያዩ ፕሮጀክቶች ቀርጬላቸው ነበር። አዎ! ሁለት ወንድሞቼ፣ ሁለት እህቶቼና እናት አባቴ ውጭ ናቸው። የልጅ ልጆችና ዘመዶቼም አሉ። ከአሥር ዓመት በፊት በተለይ ለአንድ ወንድሜ ጥሩ ፕሮጀክት ቀርጬለት ነበር፤ እዚህ መጥቶ እንዲሰራ። ግን ሊሰማኝ አልቻለም። በኋላ ላይ እንደአጋጣሚ እዚህ ኢትዮጵያ የቤተሰብ ችግር ተፈጠረና ሁሉም መጡ። ሲያዩት ያለውን ሁኔታ ሊያምኑ አልቻሉም። ያ ፕሮጀክት ደግሞ ዘግይቶ ስለነበር መተግበር አልተቻለም። እና በመጡ ጊዜ ሊያምኑ አልቻሉም። እዚያ የሚወራው ሌላ እዚህ እንደዚህ ሆኗል እንዴ? ነው ያሉት። እና ያን ያህል ተገርመው በነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ አዝነው ነው የሄዱት። አሁን ደግሞ ሌላ ፕሮጀክት ቀርጬላቸዋለሁ። አፅድቄላቸው በሂደት ላይ ነው።

በእግርጥ እዚያ በአንዳንድ ነገር ተይዘዋል። ቤት ገዝተው ሞርጌጅ እየከፈሉ ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን ምንም ነገር ቢሆን ትታችሁ መጥታችሁ መሥራት አለባችሁ እያልኩ እያግባባኋቸው ነው። እና እዚህ ልሥራ ካልክ መዓት የሥራ መስክ ነው ያለው። ለማንኛውም አስተዋይና ግልጽ ሁን። ዞር ብሎ የሚያይህ ወይም ተፅዕኖ የሚፈጥርብህ የለም፤ እዚህ። ቀደም ሲል ገቢዎች ላይ ችግር ነበር። የሚከፈለውን እኔ ነበርኩ የምከፍለው። አሁን ግን ምንም ችግር የለብንም። ሠራተኞች ናቸው የሚሰሩት፡፡ የሂሳብ አያያዝ ሠራተኞች አሉ። በሦስተኛ ወገን ሂሳባችንን እናስመረምራለን። ነገሮች መስመር እየያዙ ነው።

ዘመን፡- ስለዚህ በርካታ አበረታች ነገሮች አሉ ማለት ነው?

አቶ ደረጀ፡- በጣም! እኔ መንግሥት ባወጣው ማበረታቻ ተጠቃሚ ሆኛለሁ። ግን አንዳንድ የዳያስፖራ አባላት ይሄንን ማበረታቻ ባልተገባ ሁኔታ ተጠቅመውበታል፡፡ መሬት ወስደው የሸጡ አሉ።

ዘመን፡- አዎ! ይሄንን ጥያቄ ላቀርብልህ ነበር። አንዳንድ የዳያስፖራ አባላት እንዳልከው መሬት ወስደው እስከመሸጥና ለራሳቸው ጥቅም የመሯሯጥ ነገር የታየባቸው ሁሉ ነበሩ፤

አቶ ደረጀ፡- በእርግጥ እንደምሰማው እንዲህ ዓይነት ነገር አለ። እኔ ለዳያስፖራ ቤት መሥሪያ ተብሎ ተሰጥቶኝ ቤት ሰርቻለሁ። ለቤት መሥሪያ መሬት ከወሰዱ አብዛኞቹ ውስጥ እኔ ነኝ ቤት የሠራሁት። አብዛኞቹ ሸጠውት ቤት የሠራው ሌላ ሰው ነው። ይሄን እንግዲህ መንግሥት እንዴት እንደሚያየው አላውቅም። ይሄን የሚያደርጉት እዚህ የመኖርና የመሥራት ፍላጐት ስሌላቸው ነው። እና አንዳንድ ዳያስፖራዎች ለራሳቸው ተጠቅመው ብቻ መመለስ የሚፈልጉ አሉ። እኔ ከመጣሁ በኋላ መኪና ከቀረጥ ነፃ የማስገባት ዕድል ሁሉ ነበር። በዚህም ብዙ ያልተገባ ነገር ተሰርቶበታል። እኔ መኪኖችና ጀነሬተር ከቀረጥ ነፃ አስገብቻለሁ። ስለዚህ በማበረታቻው ተጠቃሚ ሆኛለሁ። ስለዚህ የምትሠራው ነገር ትክክል እስከሆነ ድረስ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው።

ዘመን፡- ስለዚህ በውጭ በርቀት ተጨባጭ ባልሆነ መረጃ ተወናብደው ያሉ ወገኖቻችን መጥተው ያለውን ለውጥ ተረድተው በልማቱ ሥራ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምን ትመክራለህ?

አቶ ደረጀ፡- እንደ እኔ መንግሥት መሥራት ያለበትን ሥራ መሥራት አለበት። የእኔን ወንድሞች ጨምሮ እነዚህ ሰዎች ስለ አገሪቱ በቂ የሆነ መረጃ የላቸውም። የአገሪቱን የለውጥ ሁኔታ መጥተው ቢያዩ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ያዝናሉ። እስከአሁን ምን ሆነን ነው ብለው እንደሚፀፀቱ ነው የማምነው። እኛ እኮ በዓይናችን ለውጥ እያየን ነው። ለውጡ በጣም ፈጣን ሆኗል። እኛም ከለውጡ ጋር አብረን ፈጥነን መሄድ አቅቶን እየተቸገርን ነው።

ዘመን፡- እስኪ መንግሥት ዳያስፖራውን በተመለከተ ማድረግ አለበት የምትለውን ብትነግረን ?

አቶ ደረጀ፡- የዳያስፖራውን ጉዳይ በቋሚነት መያዝ ያስፈልጋል። ሲፈለግ ብቻ አይደለም መስራት። ፕሮግራሞች ተቀርጾላቸው አገር ለማየት፣ ለበዓል፣ ለመዝናናት የሚመጡትን አንዳንድ ቦታዎች ወስዶ ማስጎብኘት፡፡ የተሰሩ ሥራዎችን ማሳየት፡፡ በእርግጥ በቴሌቭዥን ሊያዩ ይችላሉ። ግን ውሸት ነው ብለው ነው የሚያስቡት። ወደ አገር ቤት ሲመጡ በተደራጀ መልኩ አሰባስቦ ለውጡን በዓይናቸው እንዲያዩ ቢደረግ ለውጥ ይመጣል። በዚህ በኩል መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። አገሪቱ በተጨባጭ የሠራቻቸውና እየሰራቻቸው ያሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ይሄንን ማሳየት ነው። በቀላሉ የህዳሴውን ግድብ ውሰድ። እኔ አሁን በዚያ ፕሮጀክት ላይ ትልቅ ሥራ ለመሥራት ራዕይ ሰንቄአለሁ። እኔ በራሴ ያሰብኩት ዕቅድ አለ። የተዘጋጀሁበት ነገር አለ። ከአንድ የጃፓን ኩባንያ ጋርም ተነጋግሬበታለሁ። የምሠራው ሥራ አለ። ስለዚህ እዚህ አገር ላይ ሰፊ ዕድል አለ። እና እነዚህ በተለያየ ምክንያት ወደ አገራቸው የሚመጡትን ልጆች በተቻለ መጠን ማስገንዘብ። በኤምባሲዎች በኩልም መድረኮችን እየፈጠሩ ግንዛቤ መፍጠር ነው። አገራቸው ሲመጡም ከአየር መንገድ ጀምሮ ምን እየተሰራ እንዳለና እንደ እኛ ያሉ ድርጅቶች ምን እየሰሩ እንዳሉ ማሳየት ነው። አንድ ሰሞን እንዲህ ያለ የቡድን ጉብኝት ተጀምሮ ነበር። ይሄ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ይሄ ሲሆን አገራችንም ትጠቀማለች እነርሱም ተጠቃሚ ይሆናሉ። አገራችን ውስጥ የሚሰሩትን ሌሎች ከሚሰሩት የእኛ ልጆች ቢሰሩት ይሻላል። ምክንያቱም የውጭ ኢንቨስተሮች የሚያገኙትን ትርፍና ገንዘብ ወደ አገራቸው ነው ፈሰስ የሚያደርጉት፡፡ የእኛ ልጆች ግን ቢመጡ እየሰሩ የሚያገኙትም ነገር እዚሁ ለአገራቸው ልማት ይውላል። የትም አይወስዱትም። ስለዚህ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት። ያሉትንም ዳያስፖራዎች ዝም ብሎ ፔንሲዮን ብቻ ሳይሆን ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ መሥራት በሚችሉበት ሥራ ላይ ቢያሳትፍ። ምን ሰሩ? የት ደረሱ? እያለ ቢደግፍና ቢከታተል፣ አንተ አሁን እንደምትጠይቀኝ ወደፊትስ ምን ታስባላችሁ? እያለ ቢያወያየን ትልቅ ለውጥ ይመጣል። በተረፈ መንግሥት የተለያዩ አካላትን ያበረታታል እውቅናም ይሰጣል። ለምሳሌ አርሶ አደሩን፣ ወጣቱን፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የተሰማሩትንና ምሁራንን ወዘተ ይሸልማል ዕውቅና ይሰጣል። መልካም ሥራ ለሰሩና ሞዴል ለሆኑ የዳያስፖራ አባላትም ይሄን ማድረግ አለበት። ይሄ ሲሆን ይበልጥ ይበረታታሉ።

ዘመን፡- እንዳልከው ኤምባሲዎቻችንም ያለውን የአገሪቱን ገፅታ በማሳየት ትክክለኛ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ብዙ መሥራት አለባቸው፡፡

አቶ ደረጀ፡- ትክክል! እኔ በራሴ ወደ ሐዋሳ፣ ጐንደርና ሌሎች አካባቢዎች ስሄድ የማየው ለውጥ ያስገርመኛል፣ እዚህ እያለሁ። እነርሱ ደግሞ በናፍቆት ያሉ ሰዎች ናቸው። መጋበዝ ያስፈልጋል። ሰዎች ናቸው፡፡ የማይለወጥ የለምና መለወጥ ይቻላል።

ዘመን፡- መለወጥ ይቻላል ስትለኝ አንድ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው። እነዚህ ውጭ ያሉ በፖለቲካው ምክንያት የሚቆጡ ወገኖች አሉና እነርሱንም አሳምኖና አነጋግሮ ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል።

አቶ ደረጀ፡- እንደ እኔ እነርሱን መተው ይሻላል። የእነርሱ ከጥቅም ጋር የተያያዘ ስለሆነ መተው ነው። እንለውጣችሁ ብትላቸውም ሲለወጡልህ አይችሉም። እነርሱ ምንም ነገር ሳይሰሩ በሌላው ዳያስፖራ መዋጮ ብዙ ገንዘብ እያገኙ ያሉ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ እነርሱን ትቶ ሌላውን ብዙኃኑንና ሠራተኛውን አሳምኖ ማምጣት ይሻላል።

ዘመን፡- እና ልባቸው አገራቸው ያለ፣ አገራቸው ተመልሰው መሥራት የሚፈልጉትን ጠጋ ብሎ አነጋግሮና ለውጡን አሳይቶ እንዲመጡ ማድረግ ያስፈልጋል።

አቶ ደረጀ፡- ብዙዎቹ የፋይናንስም እጥረት ይኖርባቸዋል። ስለዚህ መንግሥት ሰባ ሰላሳ ብሎ የቀረፀው ፕሮጀክት አለ፡፡ ያንን መተግበር ነው። ሰላሳ በመቶ ገንዘብ አመቻችተውና ፕሮጀክታቸውን ቀርፀው ሰባ በመቶ ብድር ወስደው የመሥራት ሁኔታም አለ። ከእነሱ የሚጠበቀው መምጣት ብቻ ነው። ይሄንን እነርሱ ያውቁታል ብለህ ነው? አይመስለኝም። ስለዚህ እንዲህ ያለ የግንዛቤ እጥረትም አለባቸው፤ እዚያ። እና ይሄንን ማሳወቅ ነው። እዚያ ያለው ፕሮፓጋንዳ በጣም ኃይለኛ ነው። ብዙዎቹ የሚታለሉት በዚህ ሁኔታ ይመስለኛል። ስለዚህ ይህንን ነው መንግሥት እንደ ፕሮጀክት ቀርፆ በቋሚነትና በትኩረት መሥራት ያለበት።

ዘመን፡- አሁን ከነሐሴ 6 ጀምሮ የዳያስፖራ ቀን ይከበራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮችም በዚህ ረገድ አበረታች ሥራዎች ይመስሉኛል።

አቶ ደረጀ፡- ትክክል ነው። ለዚህ ፕሮግራም የሚመጡ ልጆች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ለእነዚህ ሁሉን ነገር ማሳየት ነው። መንገዱ የተመቸ ነው። ሆቴሎች አሉ፡፡ ሁሉ ነገር የተዘጋጀ ነውና በቡድን እየወሰዱ የሚሰሩትን ሥራዎች ማሳየት መቻል አለብን። ይሄን ሲያዩ ነው የሚያምኑት፡፡ አዲስ አበባ መጥተው ተዝናንተውና ጨፍረው የሚሄዱ በርካታ ልጆች አሉ።

ዘመን፡- አቶ ደረጀ የምትጨምረው ካለ?

አቶ ደረጀ፡- እኔ በዚህ አጋጣሚ ዳያስፖራው ወደ አገሩ መጥቶ ይሄን ምቹ የሆነ ዕድል ቢጠቀም ጥሩ ነው እላለሁ። ለእነርሱ እዚያ የሚወራውና እዚህ የሚሠራው አንድ አይደለም። ይሄንን ስል ዝም ብዬ አይደለም። እኔ ስመጣ እውቀት እንጂ ብር ይዤ አልመጣሁም። ግን ዛሬ ከአርባ በላይ ሰው አስተዳድራለሁ። ያ አርባ ሰው በስሩ ሌላ አርባ ሰው ሊያስተዳድር ይችላል። እና ይሄ ያስደስተኛል። ገባሁ ከአገሬ ሰው ጋር ነው። ወጣሁ ከአገሬ ሰውና ከወንድሞቼ ጋር ነው። ይሄ አይገኝም፡፡ እና መሥራቱ ብቻ ሳይሆን የመደጋገፍ ባህላችንንም እያዳበርን መሄዱ ትልቅ ነገር ነው። ውጭ አገር በጥገኝነት መኖሩ ጊዜአዊ እንጂ ቋሚ መሆን የለበትም። እና ይህን ስላደረጋችሁ በጣም አመሰግናለሁ።

ዘመን፡- አመሰግናለሁ አቶ ደረጀ።

አቶ ደረጀ፡- ምንም አይደለም እመጣለሁ ስትለኝ የሥራ ቱታዬንና ጫማዬን አውልቄ ነው ስጠብቅህ የነበረው። እኔ ለሴኮንድም ጊዜ የለኝም፡፡ በጣም ሥራ ይበዛብኛል። ሆኖም ለእናንተ ይህችን ጊዜ በመቆንጠሬ ደስ ይለኛል።

 

አዘጋጅ ሰሎሞን በቀለ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137296
TodayToday107
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week7
This_MonthThis_Month3378
All_DaysAll_Days137296

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።