ባለትዳሮች ስትነጋገሩ Featured

14 May 2015

ባልና ሚስት ተፋቅረው እንደተጋቡ አንዳቸው ለአንዳቸው እምነት እንዳላቸው ያስባሉ፡፡ ስለዚህም አንዱ ለአንዱ መልካም ባል ወይም ሚስት መሆኑንን ወይም መሆኗን የትዳር አጋሩ ወይም አጋሯ እንደሚያምኑ ስለሚታሰብ ያንን በአንድም በሌላም መልዕክቶች ውስጥ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ

ሚስት ትጠይቃለች፥«ጉዳዩን ጨረስክ

ባል «ጨርሻለሁ»

«መፅሃፉን የት አደረግከው»

«መደርደሪያው ላይ አለ»

«ዛሬ አንድ ጉዳይ ነበረኝ ልጆቹን ከትምህርት ቤት ብታመጣቸው»

«እኔም አይመቸኝም»

ድርቅ ያለ ንግግር፣ የፍቅር ቅመም የጎደላቸው ቃላት፣ ወዳጃዊ ያልሆኑ አቀራረቦች::

የእናንተንስ ጎጆ ከስሩ ታውቃላችሁ? የመጠላላት የመኮራረፍ ያለመረዳዳት ያለመተጋገዝ የስልቸታ ሁሉ

ምንጩ የምትነጋገሩበት አግባብ፣ የምትነጋገሩበት ጊዜ፣ የምትነጋገሩበት ስሜትና የመሳሰሉት ተደማምረው የትዳራችሁን ደስታ ይነጥቃሉ ይላሉ የጋብቻን ጉዳይ የሚመረምሩ ምሁራን፡፡ በአነጋገር ስሜቶች ያለመጣጣም ደስተኛ ወዳልሆነ የትዳር ጎጆ ይመራል፡፡ መልካም ያልሆነ የንግግርና የስሜት አለመጣጣምም ለረጅም ግብ የታሰበውን ትዳር መራር ያደርጋል፡፡ በአንዳንድ ወዳጆቻችሁ ቤት ጎራ ትሉ ይሆናል፡፡ በቤቱ ወስጥ የሰው ህይወት የሌላ እስኪመሰል ድረስ በሚያስፈራ የፀጥታ ድባብ ተውጦ በባልና ሚስቱ ዘንድ ያለው የንግግርና የስሜት መራራቅ እንደተራራ ገዝፎ አይታችሁት ይሆናል፡፡ ድርቅ ያለና ጣዕም የሌለው ንግግር፣ ግዴለሽናትና ስልቸታን የተሞላ ምልልስ ትሰማላችሁ፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ፊት ለፊት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ጀርባ በሁለቱ መካከል ያለው የንግግርና የስሜት መጣጣም ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ታያላችሁ፡፡

የግንኙነት ክህሎት በትዳር ውስጥ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ብዙ የሥነልቡና ሊቃውንትም በዚህ ይስማማሉ፡፡ መቼም ትዳር ሲባል በሁለት ሰዎች ማለትም በወንድና ሴት መሀል ለዘላቂ ሕይወት የሚደረግ ተፈጥሮን መሠረት ያደረ ጥልቅ ግንኙነት ነው፡፡ በመሆኑም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሐሳብ፣ መረጃ፣ ስሜትን እና የመሳሰሉትን ለኑሮአቸው የሚበጁ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ በየዕለቱና በየሰዓቱ በቃል፣ በጽሑፍ ወይም በምልክት መልእክትን ይለዋወጣሉ፡፡ ግንኙነት ሲባልም ሁልጊዜም ታሳቢ የሚሆኑት መልእክት ሰጨው፣ መልእክት ተቀባዩና መልእክት ማድረሻ ምህዋር፣ በዚያ ላይ ተጽዕኖ የሚሳድሩ እንቅፋቶችና ግብረ መልሶች ናቸው፡፡

የትዳር አጋሮች አንዱ ለአንዱ በሚኖራቸው ግንኙነት ውስጥ መልእክትን ማለትም ሊያስተላልፉ የፈለጉት የሐሳብ፣ የስሜት ወይም የመረጃ ይዘትን ይመለከታል፡፡ በትዳር ውስጥ ለአጋራችን የምናስተላልፈው መልእክት ይዘት በትዳራችን ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ለፍሬያማ ግንኙነት ግን በምናስተላልፋቸው መልእክቶች ይዘት ምን መምሰል እንዳለባቸው የሚሠጡ አንዳንድ ምክሮችን ማስታወስ ይበጃል፡፡

የሚያበረታታ መልእክት

የትዳር አጋራችን ሊሰማው የሚመኘው የሚያስደስተውንና የሚጠብቀውን መልእክት ቢሆን መልካም ነው፡፡ ባልና ሚስት ተፋቅረው እንደተጋቡ አንዳቸው ለአንዳቸው እምነት እንዳላቸው ያስባሉ፡፡ ስለዚህም አንዱ ለአንዱ መልካም ባል ወይም ሚስት መሆኑንን ወይም መሆኗን የትዳር አጋሩ ወይም አጋሯ እንደሚያምኑ ስለሚታሰብ ያንን በአንድም በሌላም መልእክቶች ውስጥ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ እርሱን በማግባቷ ወይም በማግባቱ ደስተኛ መሆኗን/መሆኑን/ የሚገልጽ መልእክት ትዳርን የሚያንጽ ነው፡፡ በትዳር ውስጥ በራስ መተማመንን ያሳድጋል፡፡ ተዘውትሮ የሚታይ የመተቸት ዝንባሌ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ በቀጣዮቹ የትዳር ጊዜያት ላይ መተማመንን ያሳጣል፡፡ ተስፋ መቁረጥ ያስከትላል፡፡

አንድ ቢሊ የሚባል ሰው ናስቲ ስለተባለች ሚስቱ የግንኙነት ዘይቤ ሲናገር ያለው የምሬት ቃሉን ላስታውሳችሁ ‹‹ሚስቴ ሁሉን ነገር ማጥቂያ ታደርገዋለች፡፡ አነጋገሯ የሚያበሳጭና ለቁጣ የሚጋብዝ ነው፤ ለምን እንዲህ ማድረግ አልቻልክም? ለምን ይሄን አላደረግህም? ወዘተ በሚሉ ጥያቄዎች ልትጀምረው ትችላለች፤ ቃላቶቿ ብቻ አይደሉም የምትናገርበት ድምፀት ችግር ያለበት ነው፤ ናስቲ የማታከብርና በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ስህተት ፈላጊ ነች፡፡ ለምን እንዲህ ታደርጊያለሽ ስላት ያነሳሁትን ሐሳቤን ለማስቀየር ትጥራለች፤ ወዲያው ሌላ ስህተት ትሰራለች፤ ለዓመታት ያ ሆኖብናል፡፡ በችግሯ ላይ መወያየትንም ትቃወማለች፡፡ ስለዚህ ብወዳትም በዚህ ግንኙነት መንፈስ ከእርሷ ጋር መቆየት አልቻልኩም፤ በዚህ ጊዜ የፍቺ ጥያቄ ሳቀርብላት አላቅማማችም ምክንያቱም ስሕተት ሠራሁ ብላ አሁንም አታስብምና፡፡›› ብሏል፡፡

አንዳንዴ ትችት ብቻ ሳይሆን ሁሌ ተቃራኒ የመሆን ፍላጎቶችን ማሳየትም አንዱ የማያበረታታ ግንኙነት ነው፡፡ ሰማዩ ሰማየዊ ሆኖ ሳለ ሰማየዊ ሰማይ ነው ስትል አይ ዳመና አለው እያሉ በነገር ሁሉ ለመቃረን መሞከርም ዝንባሌው የግንኙነት እንቅፋት ነው፡፡

ገርነት ለመልካም ግንኙነት

እንዲህ ያሉ የሚያበረታቱ መልእክቶች ደግሞ የሰመረ የመልእክት ምህዋር በሆኑ መልካምና ልባዊነቱን በሚያመለክቱ አቀራረቦች ሲተላለፉ ለመልእክት ተቀባዩ የተረዳና የሚያረካ ይሆናል፡፡ ለመልካምም ግብረ መልስ ይጋብዛል፡፡ ከመልካም አቀራረብ ጋር አያይዘን የምናነሳቸው ተያያዥ የሆኑ የሚከተሉትን በጎ ልማዶችን መያዝ ጠቃሚ ነው፡፡ የመጀመሪያው ገርነት ነው፡፡ ኃይለኛ፣ ሸካራና ግትር መሆንን ከመሳሰሉ ለትዳር ጠንቅ የሆኑ ልማዶችን ማስወገድ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ጠንቆች ካሉ ከትዳር አጋር የሚወጡ መልእክቶች የሚያበረታቱ ሳይሆኑ በትችት የተሞሉ፣ አስቆጪና ተስፋ አስቆራጭ መልእክቶች ይሆናሉ፡፡

ትችት ግንኙነትን ይመርዛል፡፡ ከእያንዳንዱ ቃል ጀርባ ሐሳብ አለ፡፡ የትችት ቃላት የሚይዙት መልእክት ደግሞ የሚያበረታታ አይሆንም፡፡ ነገር ግን በገርነት ውስጥ ግንኙነትን የሚመሩ ሰዎች ለትዳራቸውና ትዳራቸውን የሚያንጽ ትችት በመሰንዘር አጋራቸውን በሚያበረታታ መንገድ መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡

ንቁ አዳማጭነት ለመልካም ግንኙነት

የሚያበረታታ መልእክት ለማስተላለፍም ይሁን ለመቀበል ብቁና ንቁ ሆኖ የትዳር አጋርን ለመስማት/ለማዳመጥ/ መዘጋጀት ያሻል፡፡ የትዳር አጋሮች መልእክት በሚያስተላልፉ ጊዜ ሁሉ በንቃት ጆሮን መስጠት ማክበርን፣ ትኩረት መስጠትን ያመለክታል፡፡ ይህ የበለጠ የሚገለጸው የትዳር አጋር መልእክት ሲያስተላልፍ በቀጥታ ወደ እርሱ እያዩ መልእክት በመቀበል፣ ሌላ የሚፈጽሙት ጉዳይ ካለ ከትዳር አጋር በላይ እንዳልሆነ በሚገልጽ አግባብ ለጊዜው ተወት አድርጎ ለመስማት መሻትን በማሳየት ነው፡፡ ከተቻለም አክብሮ የትዳር አጋርን መልእክት በጉጉት ለመስማት መቻልን ለማረጋገጥ በቃላት ወይም በመልእክት በሚገለጽ ግብረ መልስ ማጀብ ብልህነት ነው፡፡

ማደመጥ የትዳር አጋር በሚስቱ ወይም በባሏ ዘንድ ዋጋ እንደሚሰጠው እንዲያስብ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ማዳመጥ የሰመረ ግንኙነትና ክብካቤ ማሳያም ነው፡፡ ለራሳቸው ብቻ እንደሚያወሩ የሚሰማቸው ከሆነ ከትዳር አጋራቸው ያገኙት አንዳችም ነገር እንደሌለ በማሰብ፣ ከዚህ ወይም ከዚህች ሰው ጋር የመኖሩ አስፈላጊነት ምንድነው ብለው እንዲጠይቁ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ለጠንካራ ጎን እውቅና መስጠት

ከዚህ በተጨማሪ በሚተላለፉ መልእክቶች ውስጥ የሚያበረታታ መልክ እንዲይዝ የሚያስችለው ሌላው ነገር ጠንካራ ጎኖችን ወይም የትዳር አጋር ያገኛቸውን/ያገኘችውን ስኬት በጉልህና በተደጋጋሚ መግለጽና እውቅና መስጠት ነው፡፡ አንዳንዶች በድክመታቸውም ለመማር ለመታነጽ ዝግጁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ጠንካራው ሲነገራቸው የሚያውቁትን ደካማ ጎን ለማስተካከል እስኪችሉ ብርታት ያገኛሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የማያውቁትን ያላስተዋሉትን ደካማ ጎናቸውን በትዳር አጋራቸው እንዲነገራቸው እስኪጋብዙ ድረስ ፈቃደኝነት ሊታይባቸው ይችላል፡፡

የቃላት ኃይል በግንኙነት ውስጥ

ቃላት ያማሉ፤ ይፈውሳሉም፡፡ በትዳር ውስጥ ያላቸው ሚና እንዲሁ ነው፡፡ ትዳርን ያፈርሳሉ ወይም ያንጻሉ፡፡ የስድብ፣ የመመካት፣ የትምክህት፣ የሚያስቆጣ፣ የሽሙጥ፣ የምጸት፣ የጥርጣሬ፣ የቂም በቀል፣ የአድልዎ፣ የሚያገሉ፣ ወዘተ ቃላት እጅግ አደገኛና በትዳር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸው ናቸው፡፡ የርህራሄ፣ የፍቅር፣ የተስፋ፣ የሚያጽናና፣ የስኬት፣ የማክበር፣ የትህትና፣ የምስጋና፣ የግልጽነት፣ የይቅርታ ወዘተ ቃላት ደግሞ ትዳርን እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያንጹ ናቸው፡፡ ስለዚህ ባለትዳሮች አንዳቸው ለአንዳቸው የሚነጋገሩበትን ቃላት በግዴለሽነት ሳይሆን በጥንቃቄ በጭካኔ ሳይሆን በርህራሄ መንፈስ ከልባቸው መዝገብ አውጥተው መናገር ይገባቸዋል፡፡

በተለይ ከትዳር አጋር ጋር ወይም ከሌላ አካል ጋር በተፈጠረ አለመስማማት ውስጥ የሚነገሩ ቃላት በዘላቂ ግንኙነት ውስጥ የማይረሱ ጠባሳዎች ጥለው እንዳይቀሩ ቃላትን መርጦ በትዕግስት ውስጥ ሆኖ ራስን ተቆጣጥሮ መናገር አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በትዳር ውስጥ የሚያጋጩ ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ምክንያታዊ የሆኑና ከቁጥጥር ውጪ የማይወጡ ግጭቶች መራር ቃላትን ሊያስተናግዱ አይችሉም፡፡ በአንጻሩ ግን ሆን ተብሎ ተዘውትሮ የሚፈጸም ምክንያታዊ ያልሆነ ወይም ከልኩ በላይ የሆነ የቃላት ጦርነትና ስሜታዊ በቃላት የሚፈጸም ረገጣ ውሎ አድሮ ትዳርን ለጥፋት ይዳርጋል፡፡

ቃላት ከፍተኛ ሐሳብን የተሸከሙ በመሆኑ በንግግራችን አንድን የትዳር አጋር አካልና መንፈስ የሚጎዳ መዘዝ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ብዙ የሕመም ዓይነቶች ሊተክሉ ይችላሉ፡፡ በርካቶች ከአጋሮቻቸው የተነገሩ ቃላትን እያሰቡ ምን ሊለኝ /ልትለኝ/ ፈልጎ ነው እያሉ ሲተረጉሙ የሚውሉ፣ ለምን እንዲህ ብዬ መልስ አልሰጠሁም የሚል የበቀልን የቁጭት ሐሳብ ተሸክመው የሚውሉ የሚያድሩ፣ ወዘተ ጊዜያቸውን የሚጨርሱ፣ ለሥራ ያላቸውን ትኩረት በማጣት ባዝነው የሚውሉ፣ ከረጅምና ተከታታይ ጭንቀት የተነሳም ለአእምሮና አካላዊ ህመም የሚዳርጉ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡

በአንጻሩ ደግሞ የአጋሮቻቸው የሚያበረታቱ ቃላት ከፍተኛ የመንፈስ ጥንካሬ የሚሠጣቸውና ስኬት በስኬት የሚሆኑ፣ ፍቅራቸውም ከጊዜ ጊዜ የሚጨምርባቸው በርካታ ሰዎችም ይኖራሉ፡፡

ዐውድን ያገናዘበ የቃላት ልውውጥ

ባለትዳሮች በሰዎች ፊት ሲወያዩና ለብቻቸው ሆነው ሲወያዩ የሚኖረው ዐውድ ሊለያይ ይችላል፡፡ በሰዎች ፊት ሲወያዩ የሚቀባበሉአቸው ቃላት በጥንቃቄ የተሞሉና የፍቅርና መከባበር መንፈስ በተሞላበት ሁኔታ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ በሰዎች ፊት ሆነው ሲያወሩ ሊሰሟቸው የሚፈልጉአቸውና የማይፈልጓቸው ቃላት ይኖራሉ፡፡ ለብቻ ሆነው ሲወያዩ የሚነጋገሩባቸውን ቃላት መጠቀም ለአንዳንዶች ሊያስቆጣቸው ይችላል፡፡ ወይም አያስደስታቸው ይሆናል፡፡ በዚያም ምክንያት የትዳር አጋራቸውን በሰው ፊት ይዘው መቅረብ የማይፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ አንጻር ሁኔታዎችን ከግምት ያስገቡ የንግግር ቃላትን መጠቀም የሚችሉ፣ የትዳር አጋሮቻቸውን በማንም ፊት ይዘው ቢቀርቡ የማያፍሩ ምናልባትም ከትዳር አጋር ጋር ሆኖ መታደም ኩራት የሚፈጥርላቸውም በርካቶች ይኖራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ችግርን ለመፍታት በሚደረጉ በአንዳንድ ጥብቅ ጉዳዮች ላይ ከተቻለም ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሚደረጉ ውይይቶች የሚደረጉበትን ጊዜና ሁኔታ መምረጥ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የትዳር አጋር በሌሎች ምክንያቶች ተቆጥቶ ሳለ ተበሳጭቶ ሳለ ወይም ተርቦ እያለ ቸኩሎ እያለ… ትኩረትና እርጋታ የሚፈልጉ ጉዳዮችን አንስቶ ለመነጋገር መሞከር በግንኙነት ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎች ሰዎች ፊት ሲሆኑ የትዳር አጋሮቻቸው እስከሚገረሙ ድረስ ደስ የሚያሰኙ ማራኪ ቃላትን የሚጠቀሙ ሰዎች ወደቤቶቻቸው ሲገቡ ተለውጠው ለትዳር አጋር እንደኮሶ የሚመሩ ቃላትን የሚያዘንቡም ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ያሉት በልማዳዊ ንግግሮች ‹‹የውጪ አልጋ የቤት ቀጋ›› የሚባለው ዓይነት አቀራረብ ያላቸው ናቸው፡፡ በውጪ ምስጉንና የመልካም ቃላት ባለቤት ሆነው ሳለ በቤት ግን ትዳራቸውን ለማነጽ በማይጠቅሙ ኃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮች የሚታጀቡ ይኖራሉ፡፡

የይቅርታ ኃይል በግንኙነት ክህሎት

ግንኙነት ሁልጊዜ የሰመረ ላይሆን ይችላል እንኳን ትዳርን በመሰለ የረጅም ዘመናት ተቋም ቀርቶ በየዕለት አጋጣሚዎቻችን በሚኖረን የሥራ፣ የንግድ፣ የማህበራዊ ኑሮ፣ ወዘተ ግንኙነት ውስጥ ታግሰን ልናልፋቸው ያልቻልናቸው ያልተሳኩ ግንኙነቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የግንኙነት እንቅፋቶች ከምንጠቀምባቸው የቃላት ጥራት፣ ከመልእክቱ ተቀባይ ግንዛቤ እጥረት፣ ወይም ከመስሚያና መናገሪያ አካላችን ችግር ጋር በተያያዘ ሳይሰሙ ወይም በደንብ ሳይናገሩ በሚፈጠር የግልጽነት ችግር የሚያጋጥሙ የግንኙነት እንቅፋቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በትዳር ውስጥ ባይዘወተሩም አልፎ አልፎ ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በምላስ ወለምታ፣ ባልሰማ ጆሮ፣ ወይም ባልሰከነ ሐሳብ ምክንያት መግባባት አለመቻል ከዚያም የመነጨ የተዛባ ግብረ መልስ መስጠት የሚያመጣው መዘዝ ሊኖር ይችላል፡፡

ሁልጊዜ አለመግባባት ራሱን በቻለ በሌላ አግባብ መታየት ሊኖርበት ይችላል፡፡ በአጋጣሚና አልፎ አልፎ በትዳር ውስጥ በምናስተላልፈው መልእክት ምክንያት የሚያጋጥሙ የግጭት ምክንያቶች ግን ስህተት ሲሆኑ የተሳሳተው ይቅርታን በመጠየቅ፣ የተበደለው ይቅርታ በማድረግ ግንኙነትን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ የባለትዳሮች ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ይቅርታ የተሰበረ የግንኙነት ሁኔታን ለመቀጠል፣ ለመፈወስ እጅግ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

መሳሳትን ማጽናትም ሆነ መሳሳትን አለመፍቀድ ከጤናማ ግንኙነት ፈላጊዎች የሚጠበቅ አይሆንም፡፡ ሁሌ መሳሳትም ሆነ በአጋጣሚ የተፈጠሩ የግንኙነት ስህተቶችን በይቅርታ አለማየት የትዳር ግንኙነትን እጅግ ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥሉ የፍቺ ዋዜማዎች ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

መልካም ግንኙነት ባለበት ሁሉ መልካም ትዳር አለ፡፡ የመልካም ግንኙነት መሠረት ደግሞ መልካም ቃላት፣ መልካም ስነምግባር፣ አስተዋይነት፣ ዕውቀትና ይቅርባይነት ናቸው፡፡ እነዚህ ለትዳር ሕይወትን ይሰጡታል፡፡ ከታመመ ይፈውሱታል፡፡ ስለዚህም በመልካም ባለትዳሮች ልብ፣ ቃልና ሥራ ውስጥ ሁሉ አይለዩም፡፡

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137268
TodayToday79
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week1282
This_MonthThis_Month3350
All_DaysAll_Days137268

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።