እያዝናኑ አገር መምራት Featured

03 Sep 2015

 

አብዛኛውን ጊዜ በዴሞክራሲያዊ አገሮች መሪዎች ሕዝቡን መስለው፤ ከሕዝቡ ጋር ተዋሕደው፣ እንደ ተራ ዜጋ በጎዳና ሲመላለሱና ተራው ሕዝብ የሚያደርገውን ሲያደርጉ ይታያል፡፡ መሪዎች ከተማ መሀል በእግራቸው እየተዘዋወሩ ሲጎበኙ፣ ‘ወክ’ ሲያደርጉ፣ ገበያ ወርደው ሲሸምቱ… ማየትም አልፎ አልፎ የሚዘወተር ነው፡፡

በዚህ አይነት ጉዳይ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ናቸው፡፡ ኦባማ ከዕጩነታቸው ዘመን ጀምሮ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡም በኋላ ከቢሮ ሹልክ ብለው የምርጫ ዘመቻውን ለሚሠሩላቸው ባልደረቦቻቸው ሳንድዊች ገዝተው ይመጣሉ፡፡ ወይ ደግሞ ከልጆቻቸው ጋር ከረሜላና ቸኮሌት ለመግዛት ወጣ ይላሉ፡፡ አንዳንዴም ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው መናፈሻዎች ተገኝተው እያንዳንዱን ሰው እየጨበጡ ስለ ጤንነታቸው ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

ኦባማን እንደ ጉዳይ አንስተን ለዛሬ እንድንቃኝ የሚያደርገን ግን ይሄን የመሰለው ተግባራቸው አይደለም፡፡ ዛሬ የምንዳስሰው ይህ የመጀመሪያ ጥቁር የአሜሪካ መሪ ከመዝናኛው ኢንዱስትሪ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ነው፡፡ ከመመረጣቸው አስቀድሞ በዓለም ላይ በሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ጭምር ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩት ባራክ ሁሴን ኦባማ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በመጻሕፍትና ከመሳሰሉት የጥበብ ሥራዎች ጋር ያላቸው ቁርኝት ጥብቅ ነው፡፡

ይህ የኦባማና የመዝናኛው ዓለም ግንኙነት ገና በ2006 ኔይል ያንግ የተባለ አሜሪካዊ ድምጻዊ ኦባማን በዘፈኑ ግጥም ውስጥ ሲያካትት ይጀምራል፡፡ ድምጻዊው “Lookin’ for a_ Leader” (መሪን ፍለጋ) በተሰኘ ሥራው የኦባማን ስም ጠቅሶ ሙስናን ጠራርጎ በማጥፋት አገሪቱን ጠንካራ ለማድረግ ወጣት መሪ እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ ቀጥሎም ይሄ ወጣት መሪ ኦባማ ሊሆን እንደሚችል በዜማ ይተነብያል…

Looking for somebody

Young enough to take it on

Clean up the corruption

and make the country strong…

may be its Obama

but he thinks that he’s too young

በእርግጥ ከዚህ በኋላም ኦባማ ስፍር ቁጥር በሌላቸው የጥበብ ሥራዎች ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ መሪ እንደመሆናቸውም ከያኒንን ሁሉ አነሳስተዋል፡፡ ለድምጻውያን እና ለጥበብ ሰዎች የኦባማን ስም በየሥራዎቻቸው ውስጥ ማካተተም ቋሚ ነገር ሆኖ ነበር፡፡

ኦባማ ግን በጥበብ ሥራዎች ውስጥ ከመጠቀስም በላይ ራሳቸው እንደ ድምጻዊ እያዜሙ፣ እንደ ዳንሰኛ እስክስታ እየወረዱ፣ እንደ ኮሜዲያንም አስቂኝ ቀልዶችን እየተናገሩ ራሳቸውን እንደ መሪ እና እንደ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን ሰዋዊ ጎናቸውንም ማሳየት ችለዋል፡፡ በዚህም የበርካቶችን ድጋፍ እና አድናቆት አግኝተዋል፡፡ በእርግጥ ይሄ ምርጫን ለማሸነፍና ወደ ብዙኃኑ ሕብረተሰብ ለመቅረብ የተደረገ ሙከራ ተብሎ ሊታይ ይችል፡፡ ሆኖም ዓላማው ምንም ይሁን ምን ፕሬዚዳንቱ የሚያደርጉት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በቪዲዮ እየተቀረፀ ዩትዩብ የተባለው የቪዲዮ ማጋሪያ ድረ ገጽ ላይ ሲጫን የተመልካቹና የአድናቂው ቁጥር በሚሊዮኖች ነው፡፡ ይሄም ኦባማ ወደ ሕዝቡ ልብ ውስጥ ዘልቀው እንዲገቡና ተቀባይነታቸውም እንዲሰፋ አስችሏቸዋል፡፡

በሚጋበዙበት የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ ቶክሾው፣ የእራት ግብዣና የመሳሰለው ዝግጅት ላይ ሁሉ ባይዘፍኑና ባይደንሱ እንኳን ቢያንስ አንድ አስቂኝ ንግግር ጣል አድርው ማለፋቸው የተለመደ ነው፡፡ ለሕዝቡ ልብ የቀረቡ አዝናኝ መሪ ሆነው መታየት እንዳስቻላቸውም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይሄንን ደግሞ የሚረዱት ኦባማ ብቻ ሳይሆኑ ባለቤታቸው ሚሼልም ይመስላሉ፡፡ ሚሼል ኦባማ በታዋቂዋ የቶክ ሾው አዘጋጅ ኤለን ሾው ላይ ቀርበው ከአዘጋጇ ጋር Uptown Funk የተባለ ዘፈን አስከፍተው “ቅልጥ ያለ” ዳንስ ደንሰዋል፡፡ ይሄም በጤና ላይ ይሰሩት የነበረውን ዘመቻ ከግብ ለማድረስ የታለመ ሲሆን ዋይት ሀውስ ውስጥ ቀዳማዊት እመቤቷ በጉዳዩ ላይ ከሚሠራው የጤና ዘመቻ ቡድናቸው ጋር በመሆን ይህንኑ ዳንስ ተቀርፀው ሚሊዮኖች አንዲያዩት ተደርጓል፡፡ ከጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ደግሞ ፕሬዚዳንቱ በተመሳሳይ ሾው ላይ ተጋብዘው ሲቀርቡ ዓለምን እንደማይመሩና የአንዲት ኃያል አገር ፕሬዚዳንት መሆናቸውን “ረስተው” ቀስ ባለ ዳንስ “እያረገዱ” ነበር ወደ መድረክ የወጡት፡፡

ዳንስና ኦባማ የሚተጣጡ ነገር አይደሉም፡፡ በቅርቡ ደግሞ አፍሪካን ለመጎብኘት የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው በኢትዮጵያና በኬንያ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ በኬንያ በተዘጋጀላቸው የራት ግብዣ በአገሪቱ ተወዳጅ የሆነውን ሊፓፓ የተባለ የዳንስ ዓይነት ከድምጻዊውና ከሌሎች ተጋባዦች ጋር በመሆን “ላባቸው ጠብ እስኪል” አስነክተውታል፡፡

ኦባማ ድምጻዊም መሆን ይችሉበታል፡፡ ይሄም በተለያዩ አጋጣሚዎች የታየ ሲሆን ከእነዚህም አንዱ የብሉዝ ኮንሰርት ነበር፡፡ በ2012 ዋይት ሀውስ ውስጥ የብሉዝ ሙዚቃ ኮንሰርት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይ የታዋቂውን የብሉዝ ሙዚቃ ንጉስ የቢቢ ኪንግን Sweet Home Chicago ይዘፍናሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም፡፡ ኦባማ ግን የድምጽ ማጉያውን ተቀብለው፣ በወቅቱ በነበረው ባንድ ታጅበው ይሄንን ሙዚቃ አስረቅርቀውታል፡፡ በተመሳሳይ ዓመትም አል ግሪን የተባለውን የታዋቂውን የአሜሪካ ድምጻዊ አንድ ዘፈን ሲጫወቱ የሚያሳይ ቪዲዮ ዩትዩብ ላይ ተጭኖ ብዙዎች ሊያዩት ችለዋል፡፡

ኦባማ በቅርብ ጊዜ “ጉሮሯቸውን ያስፈተሹት” ደግሞ በመዝሙር ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ውስጥ በደረሰ ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡት ፓስተር በተዘጋጀ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንቱ ወዳጅ ዘመድን የሚያጽናና ንግግር በማድረግ ብቻ አላቆሙም ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ Amazing Grace የተባለ መዝሙር ሲዘምሩ ምዕመኑ ሁሉ በስሜት ተሞልቶ አብሯቸው ይዘምር ነበር፡፡

መዝናኛና ኦባማን በተመለከተ ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ፊልም ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዓለምን እየተቆጣጠራት ያለው የአገራቸው የአሜሪካ ሲኒማ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ፊልም ላይ የፕሬዚዳንቱን ስም ካልጠራችሁ ፊልማችሁ አይታይም የተባሉ ይመስል በእያንዳንዱ ፊልም ላይ ቢያንስ ስማቸውን መጥቀስን ልማድ አድርገው ነበር፡፡ ባራክ ኦባማ ፊልምም ሰርተዋል ወደሚል ጨዋታ እየተንደረደርኩ አለመሆኑን ልብ በሉ፡፡ ሆኖም ፊልም ምን ያክል ተፅዕኖ እንዳለው የሚረዱት ኦባማ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በነበረበት ወቅት ያጋጠማቸውን አንድ ችግር ለመቅረፍ ፊልምን እንዴት እደተጠቀሙበት እናነሳለን፡፡

2011 የአሜሪካ ሕዝብ የባራክ ኦባማ የትውልድ ስፍራ አሜሪካ አይደለም በሚል አሉባልታ እየታመሰ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱም የልደት ካርዳቸውን እንዲያሳዩ ይወተውቱ ነበር፡፡ የነገሩን አሳሳቢነት የተረዱት ኦባማ ትክክለኛውን የልደት ካርዳቸውን ከማሳየት ይልቅ “የልደት ቪዲዮ” ነበር ያሳዩት፡፡ የሚገርመው ነገር ይህ የልደት ቪዲዮ ኦባማ ሲወለዱ የሚያሳይ ፊልም አይደለም፡፡ በዚህ ፋንታ እጅግ ተወዳጅ ከሆነው የሕጻናት የካርቱን ፊልም The Lion King ላይ አንድ ትዕይንት ቆርጠው አውጥተው እሱን አሳይተዋል፡፡ በዚህ ትዕይንት ላይ ሲምባ የተባው የአንበሳ ደቦል አፍሪካ ውስጥ ሲወለድና የአባቱ አማካሪ የሆነው ብልህ ዝንጀሮ ደቦሉን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ሲያነሳው ይታያል፡፡ ታዲያ ፕሬዚዳንቱ ልክ ይሄን አሳይተው ሲጨርሱ እደተለመደው አንድ አስቂኝ ንግግራቸውን ጣል ያደርጋሉ፡ ‹‹አደራ እንግዲህ… ይሄ ደግሞ ትክክለኛ አወላለዴ አይደለም፤ እደግመዋለሁ ይሄ ትክክለኛ ውልደቴ አይደለም›› በማለት በቦታው የነበሩትን ሁሉ ፈገግ አሰኝተዋል፡፡

እኚህ አዝናኝ መሪ ከዕለት ተዕለት ሩጫቸው ጊዜ አግኝቶ አረፍ ባሉ ቁጥር ለትልቋ ልጃቸው የሚያነቡላት አንድ መጽሐፍ አለ - ሐሪ ፖተር፡፡ ይሄ በሰባት ክፍሎች መጽሐፍ በበርካታ ሚሊዮን ኮፒዎች የተሸጠ ባራክ ኦባማም ሰባቱንም ክፍሎች አንብበው የወደዱት ሥራ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ልጃቸው አልጋዋ ላይ ጋደም ብላ ከዚህ መጽሐፍ አንድ ሁለት ምዕራፍ ሲያነቡላት መስማት የምትወደው፡፡ በእርግጥ የእርሳቸው አነባበብ የማንንም ልብ የሚገዛ፣ በሽልማትም የተረጋገጠ ነው፡፡

1995 የጻፉት Dreams From My Father የተባለ የሕይወት ታሪካቸውን የያዘ በራሳቸው የተጻፈ መጽሐፍ በድምጽ አስቀድተው አሰራጭተዋል፡፡ ይሄም በምርጥ የድምጽ መፅሐፍ (Audio Book) ዘርፍ የግራሚ ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡ Audacity of Hope የተሰኘ ሌላኛው መጽፋቸው ደግሞ በኦፕራ ዊንፍሬይ “ምርጥ መጽሐፍ” የሚል ማዕረግ ከተሰጠው በኋላ ከፍተኛ ሽያጭ አስመዝግቧል፡፡

 

ማሕበራዊ ሚዲያ

 

ምንም እንኳ ከመዝናኛው ዓለም ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ባይሆንም የባራክ ኦባማን የማሕበራዊ ድረ ገጽ አጠቃቀምም በጨረፍታ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው ከመጠቀምም በላይ ማንኛውም የመንግሥት መስሪያ ቤት የራሱ የሆኑ የማሕበራዊ ሚዲያ ገፆች እንዲኖሩት የሚያስገድድ አዋጅ የወጣው በእርሳቸው የስልጣን ዘመን በ2011 ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሁሉም የአሜሪካ መንግሥት መስሪያ ቤቶች እንደ አንድ የሥራ ክፍል የሚንቀሳቀስ የማሕበራዊ ሚዲያ የሥራ ክፍል አላቸው፡፡

ኦባማ ማሕበራዊ ሚዲያን በግላቸው ሲጠቀሙ በጣም ውጤታማ ናቸው፡፡ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ሊንክድኢን በመሳሰሉ ማሕበራዊ ድረ ገፆች በርካታ ተከታዮች እና ጓደኞች አሏቸው፡፡ በፌስ ቡክ ከአርባ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ሲኖራቸው ዩትዩብ ላይ ደግሞ ከአንድ ሺ በላይ ቪዲዮዎችን ጭነዋል፡፡ ይሄም በሁለቱም ምርጫዎች አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ እንዳስቻላቸው የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪ ቢሯቸው ይናገራል፡፡

 

አዘጋጅ ሙሉጌታ አለባቸው

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137308
TodayToday119
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week19
This_MonthThis_Month3390
All_DaysAll_Days137308

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።