«የናጠጡ ሀብታሞችንና የነጡ ድሆችን አምጥቷል» አቶ ገብሩ ገብረማርያም ስለ ግንቦት 20፤ Featured

27 Aug 2015

የግንቦት ሃያ ልዩ እትማችንን ስናዘጋጅ ይህ ዕለት ያመጣቸውን ለውጦች እንዲገልፁልን ከጋበዝናቸው በርካታ የዘመን እንግዶቻችን አንዱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ዋና ፀሃፊ የሆኑት አቶ ገብሩ ገብረማርያም ነበሩ፡፡ እሳቸውም ቀኑ ይዟቸው የመጣቸውን ጉዳዮች ሳስብ የተደበላለቀ ስሜት ይፈጥርብኛል ይላሉ፡፡

ዘመን፡- ግንቦት 20 ለእርስዎ ምን ማለት ነው?

አቶ ገብሩ፡- እኔ ግንቦት 20ን ዴሞክራሲ የተወለደበት ቀን ነው ብዬ ነበር የምወስደው ግን እንዳሰብኩትና እንደተመኘሁት ዴሞከራሲው አልሰፈነም። የሆኖ ሆኖ ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲን ምንነት ያወቀበት ዕለት ነው፡፡ በተለይም በግንቦት 20 የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተሠራው ሥራ የዴሞክራሲ ፍንጭ የታየበት ጊዜ ስለነበር ለሕዝቡ ለውጥ ማምጣቱ የማይካድ ሃቅ ነው።

ዘመን፡- አቶ ገብሩ ዘርዘር አድርገው ይንገሩኝ። በግንቦት 20 የተገኙ ድሎችንና ውጤቶችን እንዲሁም ከግንቦት 20 በኋላ የታጡ ነገሮች ካሉ ይጥቀሱልኝ፤

አቶ ገብሩ፡- እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ለግንቦት 20 የተደበላለቀ አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ የተደበላለቀ ነው የምልበት ምክንያት የዴሞክራሲ ጉዳይ ፣የሕገ መንግሥት መውጣት፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ ፌዴራሊዝምን ለመመስረት ያደረጉት ጥረት የራሱ ችግሮት ቢኖሩትም እነዚህ ሁሉ በግንቦት 20 የተገኙ ውጤቶች ናቸው።

ያጣናቸውም ደሞ እንደዚያው አሉ። በግንቦት 20ና ከዚያም በፊት በነበረው ጦርነትና ውዝግብ ኤርትራ ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ተገንጥላለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ትልቁን ነገር ማለትም ወደብን የሚያክል ነገር አጥታለች። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን የባህር በር አጥታ ዛሬ ለጅቡቲ በቀን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየከፈለች ነው ሸቀጦች የምታስገባው። ይህ የግንቦት 20 ውጤት ነው። እና ጥሩ ጥሩውን ብቻ አይደለም ቁስሉንም እናነሳለን። ለአገራቸው ያገለገሉና ከፍተኛ ውለታ የዋሉ ብዙ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት አይወድቁ አወዳደቅ ወድቀው በረሃብ ጭምር የሞቱ አሉ። ለአገራቸው ሲሉ ብዙ ጀብዱ የሠሩ ሰዎች እንደ ደርግ አሽከር ተቆጥረው በየቦታው ተጥለዋል።በግንቦት 20 ምክንያት ብዙዎች በተለይም የኦሮሞ ልጆች ወደ እስር ቤት የተጋዙበትና ታጉረው ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ እኔ ለግንቦት 20 ያለኝ አመለካከት ድብልቅልቅ ያለ ነው። ጥሩውን ብቻ አይደለም እነዚህንም ጥሩ ያልሆኑ ገጽታዎቹን አያለሁ።

ዘመን፡- በኢኮኖሚው ረገድ ግንቦት 20 ያስገኘውን ውጤትስ እንዴት ያዩታል?

አቶ ገብሩ፡- በኢኮኖሚ ረገድ የተገኙ ውጤቶችም አሉ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ የሚያቆስሉም ነገሮች አሉ። የሚታዩና የማይታበሉ እንደ መንገድ እንደ የባቡር ያሉ የሚሠሩ ሥራዎችና የተገኙት ውጤቶች ለማንኛውም ህብረተሰብና ዜጋ የሚያገለግሉ ስለሆኑ እነሱ በበጐ ጐኑ የሚታዩ ናቸው። እንደ ግድብ፣ የግብርናና የጤና ኤክስቴንሽኖችንና የመሳሰሉ ስራዎችን መካድ አይቻልም። ነገር ግን ኢኮኖሚው የተመጣጠነና ፍትሐዊ አይደለም። ይሔ ነው ጭቅጭቃችን። እዚህ አዲስ አበባም ሆነ በትልልቅ ከተሞች የሚታዩ ፎቆች የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ንብረቶች ናቸው። ስለዚህ ግንቦት 20 በአገራችን ውስጥ የናጠጡ ሀብታሞችንና የነጡ ድሆችን አምጥቷል፡፡እና መራራቁ ምን ያህል እንደሆነ መመልከት ይቻላል። ስለዚህ ኢኮኖሚውን ስናነሳ በዚህ መልኩ ነው ማየት ያለብን።

ዘመን፡- ባለሀብቶችንና ኢንቨስትመንትን ማበረታታት ተገቢ አይደለም? ባለሀብቶች የአንድ አገር የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ናቸው ተብሎ ይታሰባል። ከሥራ ዕድል ፈጠራና የአገርን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አንፃር የእነሱ ሚና ትልቅ ነው፡፡ይሔ ደግሞ የካፒታሊስት ሥርዓትም መገለጫ ነው፤

አቶ ገብሩ፡- ካፒታሊዝም የራሱ የሆኑ ባህሪያት አሉት። እነዚያ ባህርያት አይደሉም እዚህ የሚታዩት። አንዳንድ ጊዜ የዕዝ ኢኮኖሚ አይነት ነገርም ነው የማየው፡፡ ምከንያቱም የኢህአዴግ ፍልስፍናም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው። ይሄ ደግሞ ከሶሻሊዝም ፍልስፍና አንዱ ገጽታ ነው። ሌላው አንተ እንደምትለው የአገራችን ባለሀብቶች እየተበረታቱ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ መበረታታት ሲገባቸው እንዲያውም ተስፋ እንዲቆርጡ ተደርጎ ከንግዱ ዓለም የተወገዱ አሉ። የኢህአዴግ ድርጅቶች በንግዱ ዓለም በመሰማራታቸው ምክንያት የባለሀብቱ ተሳትፎ ኮስሷል። ስለዚህ አንተ የምትለው የካፒታሊዝም መገለጫዎች የሚታዩቡት ኢኮኖሚ አይደለም ያለው፡፡

ዘመን፡- ቅድም የወደብ ነገር አንስተዋል። ይሄ የወደብ ጥያቄ ምናልባት የአንድ አገርንና ሕዝብን ሉዓላዊነት መድፈር አይሆንም? ምክንያቱም የኤርትራ ሕዝብ የራሱን ሉዓላዊነት መርጦ የሄደ ሕዝብ ነውና፤

አቶ ገብሩ፡- ሉአላዊነቱ እንግዲህ ከታሪኩ ጋር የሚሄድ ነው። ኤርትራ ሉአላዊ አገር የሆነችው ከመቼ ጀምሮ ነው​? ኤርትራ ከመቼ ጀምሮ ነው የነበረችው? እንዲያውም በአበሻው ታሪክ ባህረ ነጋሽ እየተባለች ከኢትዮጵያ ጋር የነበረች አገር ነበረች። እንዲያውም ከእኛ ከኦሮሞዎች ይልቅ እነሱ ናቸው ኢትዮጵያ የተባለችውን አገር የቆረቆሩት። እና ይሔ ኢትዮጵያ ወደብ ትጣ የሚለው ነገር የኤርትራን ሉአላዊነት ይጐዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሲጀመር ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ ማጣት አልነበረባትም፡፡የባህር በር ማጣት የለባትም ሲባል አሁን በቅርቡ አቶ ታምራት ላይኔ እንደመሰከሩት አቶ መለስ ናቸው ለብቻቸው የወሰኑትና ወደቡን የሰጡት እኛ የለንበትም ነው ያሉት። እና ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ እንደሚባለው አቶ ታምራት ይሔን የድሮ ሚስጢራቸውን ገሐድ አድርገውልናል። እና እኛ ይህንን ወደብ መጠየቅና መደራደር ይቻላል ነው የምንለው። ዋናው ነገር የሁለቱን አገሮች ሰላም መልሶ ማስፈንና ሁለቱ አገሮች ድርድር ሲያካሂዱ ወደቡን እንዴት አድርገን እንጠቀምበት? የሚለው ነገር ይታያል። ዞሮ ዞሮ እንደ አፍሪካም ካሰብነው እንደ አገርም ካየነው ኤርትራ ሉአላዊነቷ ሳይነካ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት ማድረግ ይቻላል። መነጋገርም ይቻላል። እኔ እሱን ነው እያልኩ ያለሁት።

ዘመን፡- በአጠቃላይ ግንቦት 20 የዴሞክራሲ ና የመድብለ ፓርቲ ሥርአትን በማስፈን ረገድ ያስገኘውን ውጤትስ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ገብሩ፡- የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ዴሞክራሲውን ጠብቆ መሆን በሚገባው አይነት እየተተገበረ ስላልሆነ ይሔ አልተሳካም። ኢህአዴግ በዚህ ረገድ ዴሞክራሲን ፣ፍትህን፣ እኩልነትንና የፕሬስ ነፃነትን አሰፍናለሁ ቢልም ዛሬ ላይ ቆመን ስናይ እነዚያ አብበው የነበሩት መጽሔቶችና ጋዜጦች የተወገዱበትና ወደኋላ የተመለስንበት ሁኔታ ነው ለእኔ የሚታየኝ፡፡ ኢህአዴግ እንደገባ ሕዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት ሕገመንግሥታዊ መብቱ የተጠበቀ ነበር፡፡አሁን ግን ይሄ ተከልክሎ በስንት መከራና በስንት መጻጻፍ ነው ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣው። ስለዚህ ኢህአዴግ ሲገባ የኢትዮጵያ ሕዝብ እፎይ እላለሁ ብሎ ነበር ተስፋ ሰንቆ የነበረው። ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ የሃይማኖቶች እኩልነት፣ ሰብአዊ መብት ከሁሉም በላይ የሕግ የበላይነት ይሰፍናል ብሎ ተስፋ ሰንቆ ነበር የተነሳው። ያ አልሆነለትም። በዚህ በኩል ኢህአዴግ ሊቆረቆርና ሊቆጨው ይገባል።

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱንም እንዲያብብ ማድረግና ምሥጋናውንም በተገቢው መንገድ ማግኘት ሲችል የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ እንዳይሠራ አድርጓል፡፡ዴሞክራሲውም ከመግባታቸው በፊት እንደተላለፈው ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በመቅረቱ በአንድም ሆነ በሌላ በኩል የመጻፍ መብት በድብቅ ወይም በእጅ አዙር ሳንሱር እየተደረገ ነው፡፡ይሄ ሁሉ በመሆኑ ና እነዚህ መብቶች ባለመረጋገጣቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቆጨዋል።

ዘመን፡- በዚህ ረገድ ግን የተጀመሩ ጅምሮችና ጭላንጭሎች የሉም​?

አቶ ገብሩ፡- ጭላንጭሉን ቅድም አነሳሁልህ እኮ፡፡ ኢህአዴግ በገባ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ታይተው የነበሩ ጭላንጭሎች ናቸው ዛሬ እየተዳፈኑ ያሉት፡፡

ዘመን፡-በመጨረሻ ግንቦት 20ን በተመለከተ መልዕክት ያስተላልፉ ፤

አቶ ገብሩ፡- እንግዲህ ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስገኝልኛል ብሎ የተመኘውን ሙሉ ለሙሉ ባያስገኝለትም ይሄንን ቀን ለማምጣት ለወደቁት ሰማዕታት ክብር ስላለኝ ግንቦት 20ን ለእነሱ ስል አስታውሰዋለሁ ፤ጓዶቻቸው ያንን በተፈለገው መንገድ ባያስኬዱትም ።

ዘመን፡- አመሰግናለሁ አቶ ገብሩ

አቶ ገብሩ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 

 

ፀሃፊው ሰለሞን በቀለ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137264
TodayToday75
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week1278
This_MonthThis_Month3346
All_DaysAll_Days137264

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።