የፅንፈኛውና የጥቂቱ «ዳያስፖራ» ሌላው መልክ «በሶሻል ሚዲያ ላይ ባለ ቁስለኛ እና ሞት የሚገኝ ድል ካለ ኋላ እናየዋለን» - አቶ ጌታቸው ረዳ Featured

03 Sep 2015

ከፕሬዚዳንት ኦባማ የተሳካ ጉብኝት ተነስተን በተለያዩ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሬስና የፐብሊሲቲ ሚኒስትር ዴኤታ ከሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ነበረን።

ዘመን፦ ሰሞኑን እንግዲህ ትልቁ ዜና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት ነው፡፡ እንደ መንግሥት የጉብኝቱን ውጤት እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ጌታቸው፦ የጉብኝቱ ውጤት በዋናነት መገለፅ ያለበት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ከማጠናከር አንጻር ነው፡፡ ኢትዮጵያና አሜሪካ የረጅም ጊዜ ግንኙነት አላቸው፤ መቶ አስር ዓመት አካባቢ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከደርግ መንግሥት መምጣት ጋር በተያያዘ ምናልባት ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል ችግር ውስጥ የገባ ግንኙነት ከመሆኑ በቀር ከዚያ ውጪ በጣም ሰላማዊ፤ በጣም ቅርብ የሚባል ግንኙነት ነው የነበራቸው፡፡ ከ1983 ወዲህ ደግሞ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ማለትም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በመከላከያ፣ በልማት በጸጥታ በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ግንኙነቶቹ ደረጃ በደረጃ እየተሻሻሉ የመጡበት ሁኔታ ነበር፡፡ በእኛ በኩል ከአሁን በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ አሁን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ አሜሪካ ጉዞ ተደርጎ ከተለያዩ የአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር የተገናኘንበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ከ2009 ወዲህ በሁለቱ አገሮች ዘንድ የሁለትዮሽ ውይይት በቋሚነት ተደርጎ በኢኮኖሚ፣ በጸጥታ እና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ቀጣይ ውይይት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት ስኬት መለካት ያለበት ይህን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ካለው አስተዋፅዖ አንፃር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ማየት ተችሏል፡፡ ከአሁን በፊት ዓይን ለዓይንም አንተያይ በሚባልባቸው ጉዳዮች ሳይቀር ግልፅ የሆነ ውይይት ያለ ምንም ጥርጣሬና ያለ ምንም ይሉኝታ ማንሳት የቻልንበት ይሄንንም ተመስርቶ ቀጣይ ግንኙነታችን የሁለቱንም አገራት ጥቅም ማስከበር የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ብሎ ማመን ይቻላል፡፡

ስለዚህ አጠቃላይ የጉብኝቱ ጠቀሜታ ግምገማችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በጸጥታም ሆነ በመከላከያ ረገድ ያሉት ግንኙነቶች ወደተሻለና ወደ ተቋማዊ ወደ ሆነ ደረጃ ማደግ የሚያስችላቸው ሁኔታ የተፈጠረበት ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

ዘመን፦ አንዳንዶች በተለይም በውጭ ያሉ ጭፈን ተቃዋሚዎች የኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ዋነኛ ትኩረት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ መሆኑን ሲገልፁ ሰንብተው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንደሚፈጠርም የጠበቁ ወገኖች ነበሩ፡፡ ወደዚህ አገር እንዳይመጡ ያደረጉት ውትወታም ነበር። ውጤቱ ግን በተቃራኒው ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር የተገኙ ስኬቶችና ያደረጋችሁት ውይይት እንዴት ነበር?

አቶ ጌታቸው፡- ይሄ ነገር ከሁለት የተሳሳቱ ግንዛቤዎች የመነጨ ነው፡፡ አንደኛ ነገር የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ፖሊስ ነው ከሚል የተሳሳተ አቋም የሚመነጭ ነው፡፡ ለነገሩ ራሳቸው አሜሪካኖቹም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ራሳቸውን የሰብዓዊ መብት ፖሊስ አድርው የሚያቀርቡበትና በየዓመቱ የየአገሩን የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ካርድ የሚያትሙበት ሁኔታ ስላለ ከዚያ አንፃር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በጠቅላላ ከዚህ የሰብዓዊ መብት ፖሊስነታቸው ጋር የሚሄድ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አለ፡፡ አሜሪካኖቹ ግን የሰብዓዊ መብት ፖሊስነት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሰጡ ይምሰል እንጂ የአሜሪካን ጥቅሞች የሚያስከብሩ ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን መመስረት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ፤ በዚያም ላይ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ብቻ ነው የሚለው የተሳሳተ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው የምንለው ሌላው ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊ መብትም ሆነ ለዴሞክራሲ ያለው ቆራጥነት ለአሜሪካ መንግሥት ፍጆታ ሲባል የሚገባው ቃል እንጂ ከዚያ በዘለለ ትርጉም ያለው አይደለም የሚል አስተሳሰብም እንደ መነሻ ያገለግላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በተደጋጋሚ መንግሥት ሲል የቆየው የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ጉዳይ ምንም ያክል ቁጥር ያላቸው ራሳቸውን የሰብዓዊ መብት ፖሊስ አድርው የሚቆጥሩ አገራት ቢኖሩም በዋናነት ተጠቃሚ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው የሚል አቋም ያለው መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ የአሜሪካ መንግሥት በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ ለማስጠንቀቅ ነው የመጣው የሚለው ከሁለቱ መነሻዎች አንጻር ሲገመገም የተሳሳተ ነው፡፡ ይሄም ማለት ግን የሰብዓዊ መብና የዴሞክራሲ ጉዳዮች አይነሱም ማለት አይደለም፡፡ ተነስተዋል፡፡ የተነሱበት አውድ ግን አሁን ከተጠቀሱት ውጪ ያሉ ወገኖች በሚጠብቁት ወይም ተስፋ ያደርጉት በነበረው ማስፈራራትና ማስጠንቀቅ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ በተለይ ትኩረት ያደረገው ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ትኩረቶች ተቋማዊ መሠረት በሚይዙበትና በአሜሪካ በኩል አዎንታዊ ድጋፍ መስጠት በሚቻልበት መልኩ ፕሬዚዳንቱ ግልጽ ሆነው ማንሳት ችለዋል፡፡ በእኛም በኩል ጀማሪ ዴሞክራት ነን ከባሕል ጋር በተያያዘ አንዳንድ ችግሮች አይከሰቱም ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ ችግሮች ሲከሰቱ ከመቅረፍ አንጻር የአቅም ግንባታ ሥራዎች፣ የትምህርት ማስፋፋት ውስጥ፣ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ ስለሚችሉበት መንገድ ሃሳቦች ተነስተው ተንሸራሽረዋል፡፡

አሜሪካኖች የመጡት ግን ለምንድን ነው የሚለው ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ አንድ ርዕስ ነው ሊባል ቢችልም ከምንም ነገር በላይ ግን ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነቡ ካሉ አገሮች አንዷ ነች፤ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ሳትቆጠብ በአገር ውስጥም ሆነ በአካባቢው ፀጥታና መረጋጋት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ያለች አገር ነች፡፡ ሰላምን በማስጠበቅ፤ ሽብርን በመዋጋት፤ የተለያዩ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል፤ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ያለች አገር ነች ብለው ያምናሉ፡፡ አሜሪካኖችም በዚህ ዙሪያ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ያምናሉ ፡፡ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መስራት ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ሊማሯቸው የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ያውቃሉ፤ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ያለውን ትብብር ጠንካራ ለማድረግ እና ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ለመስራት ነው፡፡ እዚህ ላይ ማንም ሰው ልብ ሊለው የሚገባ ነገር ቢኖር አሜሪካኖችም በትክክል የሚገነዘቡት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ እያስመዘገበችው ያለው ዕድገት፤ በፀጥታ እና በመረጋጋት ዘርፍ ያለው እጅግ የሚያኮራ ተግባር የፖለቲካ ስርዓቷ በራዕይ ላይ የተመሠረተ፣ የሕዝቦችን ሰፊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችልና ምቹ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት ሂደት ውጤትም ጭምር ነው፡፡ ያለ ሕዝብ የተሟላ ተሳትፎ የሚረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ሂደት የለም፡፡ ያለ ሕዝብ የተሟላ ተሳትፎ የሚረጋገጥ ምንም ዓይነት ፀጥታና መረጋጋት የለም ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ፀጥታና መረጋጋት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፤ አካባቢው ውስጥ ለምንጫወተው ፀጥታና መረጋጋትን የማረጋገጥ ሥራ ይሄንንም ተሸክሞ ለመሄድ የሚያስችል ኢኮኖሚ የመገንባት ሥራ እነዚህን ሁሉ ካለ ሕዝብ የተሟላ ተሳትፎ ሊፈፀሙ የማይቻሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሜሪካኖቹም ሆኑ ሌሎች ወገኖቻችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት አለ ሲሉ ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች ሲሉ፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ነው ሲሉ በዋናነት እየገለፁ ያሉት ኢትዮጵያ ይሄን ለማረጋገጥ ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት እና ተቀባይነት ያለው ስርዓት መገንባት ጀምራለች ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ጥያቄ የሚሆነው አሜሪካኖቹ ይሄንን ስርዓት የበለጠ ጥልቀትና መሰረት እንዲኖረው የሚያደርጉት የራሳቸው ጥረት ሊኖር ይችላል፡፡ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመስርቶ እስከተሰጠ ድረስ እንደዚህ ዓይነቱን ስርዓታችንን የሚያጠናክር ምክር ከማንም ቢሆን የማንቀበልበት ምክንያት የለም፡፡ ይሄ ግን ግንኙነቱ በሰጪ እና በተቀባይ፣ በመካሪና በተመካሪ፣ በቆንጣጭ እና በተቆንጣጭ፣ መካከል እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ በውጭ ያሉት እንግዲህ አይፈርድባቸውም፤ በአንድ ይሁን በሌላ መንገድ አለን ይሉት የነበረው የፖለቲካ ጥቅም የተጎዳባቸው ወገኖች ይሄንን ነገር በተንሸዋረረ መልኩ ቢገነዘቡት ብዙም የሚገርም አይደለም፡፡ አሜሪካን የሚያክል አገር ውስጥ ለረጅም ዘመናት ኖረው እንኳ አሜሪካና ፖለቲካዋ እንዴት እንደሚዘወር በትክክል ማወቅ የማይችሉ መሆናቸው እንደ ወዳጅ እንደ ዘመድ ሊያሳዝኑ ነው የሚገባው። ሠላሳ ዓመት አሜሪካ ውስጥ የኖረ ሰው የአሜሪካ መንግሥት ከሌሎች አገራት ጋር ያለው ግንኙነት የሚመሠረተው በተንሸዋረረ መልኩ በሚረዱት የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ብቻ ነው የሚል የዋህ ዕምነት መያዛቸው ምናልባት ረጅም ጊዜ በትምህርት ተቋማት መኖር ብቻውን ለዕውቀት እንደማያበቃ እንደ አንድ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ትልቁን ነገር እንደ ተራ ግብዓት አድርገው ከተረዱት ያሳዝናል፤ ነገር ግን ተራ ጉዳይ አለመሆኑን ሰውየው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከተከናወነው ተግባር መረዳት ይቻላል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለአገራቸው ጠንካራ አቋም አላቸው፤ አሜሪካንን በሚመለከት ጥቅምዋን ለማስጠበቅ ከሀገራት ጋር ያላቸው ግንኙነት በምን ላይ መመስረት እንዳለባቸው ይረዳሉ፤ ስለዚህ በየመንደሩ ኢትዮጵያን በሚመለከት የአርማጌዶን ወሬ የሚያወሩ የተምታታባቸው ተቃዋሚዎች የሚሰጡትን ትንተና አይደለም ፕሬዚዳንቱ ግምት ውስጥ አስገብተው የሚጎበኙትን አገር የሚመርጡት፡፡ ይሄ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፤ በተግባር ግን የሆነው የተረጋጋ ኢኮኖሚ፤ የተረጋጋ ስርዓት፤ ሕዝቡን በተሟላ ሁኔታ ማሳተፍ የጀመረ ዴሞክራሲ መገንባት እየጀመረች ያለች አገርና ውጤትም እያሳየች ያለች አገር ናት፡፡ ከዚች አገር ጋር መስራት ምንም ተኪ የሌለው፤ ለንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋትም እጅግ ሁነኛ እና ተመራጭ ቦታ እንደሆነ በትክክል የተገነዘበ የአሜሪካ መስተዳድር ነው አሁን ያለው፡፡ ያደረጉትም ጉብኝት ስኬታማ ነበር፡፡

እናም ውጤቱ ያልተጠበቀ የሆነባቸው ሰዎች የኢትዮጵያን ሁኔታ መረዳት የማይፈልጉ ሰዎች ናቸው፡፡ አሜሪካኖቹ ጥቅማቸውን በጥንቃቄ ነው የሚይዙት፡፡ ሀገራዊ ጥቅማቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነቶች ከሰይጣንም ጋር ቢሆን ያደርጋሉ፤ እንኳን እንደ እኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ላይ ያለ፤ የራሱንና የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ላይ ያለ፤ እጅግ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ የጀመረ፤ በርካታ ሚሊዮን ሕዝብ ያለው አገር ይቅርና በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ለአሜሪካ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል ብለው ከሚያስቡት ትንሽ አገርም ጋር ቢሆን ግንኙነት ከመመስረት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ስለዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ የነበረው በኦባማ ጉብኝት እዚህ አገር የነበረው እጅ ተጠምዝዞ እነሱ የፈለጉትን ብቻ ያሳካሉ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ብቻ ናቸው የተምታታባቸው የሚሆኑት፡፡ በፕሬዚዳንት ኦባማና በመስተዳድራቸው በኩል ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚኖራቸው ግንዛቤ አስገራሚ የሚሆንባቸው ሰዎች ካሉ እነሱ ናቸው የሚሆኑት፡፡ ለእኛ አስገራሚ አልነበረም፡፡ በቀጣይ ግንኙነታችንም ወቅት መረጃ እንለዋወጣለን፡፡ አገራችንን በሚመለከትም ሰፊ ግንዛቤ አላቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሲናገሩ ሰምተሻቸው እንደሆነ ገዥው ፓርቲ ሰፊ ተቀባይነት እንዳለው አሜሪካኖቹ ይገነዘባሉ፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ተረት አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በርካታ ብሔረሰብ፣ በርካታ ሃይማኖት በርካታ ዓይነት የሕዝብ ስብጥር ባለበት ቦታ ወጣት ሴት ሽማግሌ በምትይው የተቀላቀለ ኀብረተሰብ በሰላም እንዲኖር በመረጋጋት ለማቆየትና ዘላቂ የሆነ ዕድገት ለማስመዝገብ የሰፊውን ሕዝብ የተሟላ ተሳታፊነት ማረጋገጥ የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ይነስም ይብዛም ያ የፖለቲካ ስርዓት በሌለበት ሁኔታ መረጋጋትም አይኖርም የማረጋጋት ሚና መጫወትም አይቻልም፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብም አይቻልም፡፡ ስለዚህ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብም ሆነ በአካባቢው የምንጫወተውን የማረጋጋት ሚና ለመወጣት የጀመርነው የዴሞክራሲያዊ ሂደት ግንባታ ይነስም ይብዛም የሕዝቡን ተሳታፊነት ለማረጋገጥ በሚያስችል ደረጃ መንቀሳቀስ በመጀመሩ ነው፡፡ ስለዚህ አሜሪካኖቹ ይሄንን ይረዳሉ፡፡ የእኛ ተቃዋሚዎች በፕሬዚዳንት ኦባማ መግለጫ እንደደነገጡት በስሜት እና በተራ ውዥንብር የሚመሩ አይደሉም፡፡ ዕውነትን መሠረት ያደረገ ትንታኔ ስለሚያደርጉ፡፡ ይሁንና ፕሬዚዳንት ኦባማ ስለ እኛ ጥሩ ግንዛቤ መስጠታቸውና ጥሩ መግለጫ መስጠታቸው እንደ አንድ አዎንታ የሚወሰድ ሆኖ፤ ፕሬዚዳንቱ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበራቸው አቋም የተለየ ቢሆን ብለን ብናይ፤ የዴሞክራሲ ግንባታችን ከማንም በላይ ለህዝባችን ብለን የምናደርገው ነው፡፡ ብልፅግናና ዕድገት፤ ድህነትን መቅረፍ፤ ሁሉን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት፤ ወሳኝ ነው ብሎ የሚንቀሳቀስ መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንት ኦባማ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በምንፈልገው ደረጃ ጥሩ ነው ብለን አናምንም የሚል መግለጫ ቢሰጡ ኖሮ ዞሮ ዞሮ እንደ አንድ ወዳጅ በቅንነት የተሰጠ ሂደታችንን ወደ ኋላ የሚመልስበት ወይም ወደ ፊት እንዲሄድ የሚያደርበት ዕድል አለ ብሎ መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡ ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሂደት በትክክል መገንዘባቸው በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ሊታዩ የሚችሉ ችግሮች ድጋፍ መስጠት የሚያስችል ዝግጁነት ማሳየታቸው እንደ አንድ ትልቅ አዎንታ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚያ በዘለለ ግን የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሂደት ወደ ፊት መሄድም ወደ ኋላ መመለስም የሚወሰነው በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በጎ ጥረት እንጂ በሌሎች ይሁንታ ላይ ተመስርቶ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ተገረሙ ያልሻቸው ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው ያልሻቸው ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ በተወናበደና ውዥንብር በተሞላበት መልኩ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሂደት ከሕዝብ ተሳትፎ ይልቅ በአንድ የበለፀገ አገር መሪ ይሁንታ መኖር አለመኖር ላይ የተመሠረተ ነው ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ ይብላኝ ለነሱ ከዚህ ውጪ በተግባር ሂደታችንን የሚቀይረው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡

ዘመን፦ አሁን የዳያስፖራ ቀን እየተከበረ ነው። በሌላ መልኩ የኢትዮጵያን ለውጥ ፈፅሞ የማይቀበል፣ ሁሌ ጨለማ ጨለማውን ብቻ የሚናገር ዳያስፖራ አለ፡፡ ይህኛውን መልክ በተመለከተ ምንድን ያለዎት አስተያየት ?

አቶ ጌታቸው፡ አሁን አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ እንግሊዝ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ ሳዑዲ ውስጥም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ አሁን አንቺ ዳያስፖራ የምትያቸው እነዚህ ኢትዮጵያውያን፤ ዘጠና ዘጠኝ በመቶው ማለት ይቻላል መልካም ነገር ይመኛል፡፡ አቅሙ በፈቀደው መጠን የቤተሰቦቹን ሁኔታ ለመቀየር፤ የቤተሰቡን ሕይወት ሲቀይር እዚያው እያለ የማህበረሰቡን ሕይወት ለመቀየር አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ስለዚህኛው ግን ብዙ ጊዜ ሲወራ አንሰማም፡፡ የቋጠሯትን ጥሪት ይዘው አገር ቤት መጥተው ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ በማንኛውም የዓለም ጥግ ግን ሲጮሁ ሰምተናቸው አናውቅም፡፡ እንግዲህ እንደ ትልቅ ርዕስ በየመድረኩ የምንሰማው 99.9 ካልኩሽ ትርፍ ውስጥ በጩኸት ላይ የሚሰማራ ምናልባት አሜሪካ ውስጥም ይሁን እንግሊዝ ውስጥ የረባ ሥራ በመስራት የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችለው የጨዋ ሥራ መስራት ላይ ብዙ ጊዜ ችግር አለበት፡፡ ጊዜውን በጩኸትና ጊዜን በተቃውሞ ማሳለፍ የሚፈልግ ወገን አለ፡፡ ይሄኛው በጣም ስለሚጮህ ይሰማል፡፡ ስለዚህ እየሰማን ያለነው ይሄኛውን ጯሂውን ክፍል ከሆነ የትኩረት አቅጣጫችን ተዛብቷል ማለት ነው፡፡ ዋናው የትኩረት አቅጣጫችን ሊሆን የሚገባው ብዙ የማይጮኸው ግን አገሩንና ቤተሰቡን በመለወጥ ሂደት ውስጥ ለሚንቀሳቀሰው ወገን ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በቅርቡ የሚከበረው የትውልደ ኢትዮጵውያን ቀን ዋና ዓላማው እንደዚህ ዓይነቱ ራስን በመለወጥ፤ አገርን በመለወጥ፤ ቤተሰብን በማገዝ፤ ውስጥ ለመሰማራት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውን ወገን ዕውቅና ለመስጠት የምናደርግበት መድረክ ነው የሚሆነው፡፡ በአገር ልማትና በአገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ መጫወት የጀመረውንና ሊጫወት የሚገባውን ገንቢ ሚና መጫወት እንዲችል ማትጊያ እና ማነቃቂያ መድረኮች የሚፈጠሩበት ነው፡፡ ያኛው ወገን በጩኸት የተሰማሩ ጥቂት ሰዎች፤ አንዳንዶቹ ይሄ ስርዓት ለውጥ ሲመጣ የሰፊውን ሕዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል ለውጥ ሲጀምር ትንሽ ጥቅማቸው የተጎዳባቸው ሰዎች አሉበት፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከየዋህነት በሚመነጭ እኛ የምናምነው መስመር ብቻ ነው ትክክለኛው ብለው የሚያምኑ ግን ደግሞ በምክንያት እና እውነት ላይ ለተመሠረተ መረጃ ዝግጁ ያልሆኑ፤ በመፈክር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ የሚያራምዱ ወገኖች ያሉበት ነው፡፡ ግን ቁጥራቸው ከጩኸታቸው ጋር የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛ ከቁጥራቸው ይልቅ ጩኸታቸው የሚያሳስበን ከሆነ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ ያ ማለት ግን እነዚህም ቢሆን እንደ ጋንግሪን ጣት ተቆርጠው ይጣሉ ማለት አይደለም፡፡ መዳን የሚችሉበት ዕድል ካለ በማንኛውም አጋጣሚ እንዲድኑ ጥረት መደረጉ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን እነሱን ለመንከባከብ በሚደረግ ጥረት ሌላውን ጣት ይዘው እንዳይጠፉ ደግሞ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ዘመን፦ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ መንግሥት እነዚያን ሰዎች ለማነጋገር እና ለማዳመጥ ቦታም አልሰጣቸውም፤ ሆደ ሰፊ ሆኖ ቀርቦም አላነጋገራቸውም ምናልባት ተቀራርቦ መነጋገር ቢቻል ውጤት ይኖረው ነበር ብለው ይወቅሳሉ፡፡ መንግሥት በዚህ በኩል ምን ያክል ርቀት ሄዷል ይላሉ?

አቶ ጌታቸው ፦ መንግሥት በጣም ብዙ አገር ለመለወጥ ጥረት ያደርጋል፡፡ እየተሳካለትም ነው፡፡ አገር ለመለወጥ በምታደርጊው ጥረት ውስጥ አንተ የጀመርከው መንገድ ፍጥነት ያንሰዋል፤ ፍጥነት መጨመር የሚያስችል መንገድ አለ ከሚል ሰው ጋር ጊዜ ሰጥተሸ ትደማመጫለሽ፡፡ አዎ፤ የጀመራችሁት ድልድይ ግንባታ ጥሩ ቢሆንም ድልድዩን ግን ከዚህ የበለጠ ጠንካራ ማድረግ እንችላለን ከሚሉ ሰዎች ጋር መደማመጥ ትችያለሽ፡፡ ግድብ መሥራት ጀምራችኋል እሰየው ግን ግድቡ ቁመቱ በጣም አንሷል፤ ኢትዮጵያውያን ከዚህ የበለጠ ግድብ ይገባናል ከሚሉ ሰዎች ጋር መደማመጥ ትችያለሽ፡፡ ግድብ መስራትም ድልድይ መስራትም ተገቢ አይደለም፤ ሌሎች አማራጮች አሉ ከሚሉ ሰዎችም ጋር እንዲሁ መነጋገር ትችያለሽ፡፡ የድልድይ እና የግድብ መሠራት ላይ ጠንካራ እምነት ኖሮሽ ከእነሱ ጋር ባትስማሚም አማራጮች አሉን እስካሉ ድረስ ትደማመጫለሽ፡፡ የተሠራ ግድብ መፍረስ አለበት፤ የተሠራ ድልድይ መደርመስ አለበት፤ የተሠሩ መንገዶች መፈራረስ አለባቸው፤ የተረጋገጡ የልማት ጎዳናዎች መቀልበስ አለባቸው፤ የተረጋገጡ ምርቶች መቀመቅ መውረድ አለባቸው ከሚሉ የጥላቻ መልዕክተኞች ጋር በየትኛው ስሌት ነው መግባባት የምትችይው? በየትኛው ስሌት ላይ ተመስርተሽ ነው ቦታ ሰጥተሸው መደማመጥ የሚኖረው? እነዚህ ሰዎች እኮ እርስ በርስ ለመደማመጥ እንኳ ዕድል የላቸውም፡፡ ፈረንጆቹ Shouting Match የሚሉት ነገር አለ፡፡ እኔ የበለጠ እጮሃለሁ ብለው የሚፎካከሩ ሰዎች መደማመጥን ሳይሆን የሚያሳዩት አንዱ ከሌላኛው የበለጠ መጮህ እንደሚችል ነው የሚያሳዩት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች አለን የሚሉትን የጥፋት መልዕክት በከፍተኛ ጩኸት ከማሰማት ከእርስ በርስ የጩኸት ውድድር በዘለለ ከሌላ ሰው ጋር በምክንያት፣ በመረጃ እና በእውነት የተመሠረተ ውይይት ከሌሎች ጋር ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ስለዚህ መንግሥት እንዲያውም ሊወቀስ ከተገባው እነዚህን ሰዎች በተመለከተ አሁን ባነሳሽው ደረጃ ምን ልናደርጋቸው እንችላለን የሚል አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ መግባት ካልሆነ በስተቀር በመንግሥት ደረጃ እንደዚህ አይነቱን Dead Wood የሚሉትን ቢቻል ተነቅሎ ቢወጣልሽ የምትመኚው ማለት ነው፡፡ ግን ደግሞ እንዳልኩሽ እንደ ጋንግሪን ጣት ሌላ ሰው ይዞ እንዳይጠፋ ብቻ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሻል፡፡ እንጂ ለእነኚህ ጥቂት በጩኸት፣ በመፈክር ላይ ተመስርተው ለሚንቀሳቀሱ ወገኖች ምንም ቦታ ብትሰጪ ድልድይ እንዴት እናፍርስ በሚል ጉዳይ ላይ መወያየት አንችልም፡፡ ግድቡን እንዴት እንናደው በሚል ጉዳይ ላይ መወያየት አንችልም፡፡ የተሠሩት ሕንፃዎች እንዴት ይፍረሱ፣ የትኛውን ድማሚት እንምረጥ በሚል ጉዳይ ላይ ልንወያይ አንችልም፡፡ ስለዚህ ጥያቄው የምንወያይበት አጀንዳ አለ ወይ ነው፡፡ ስለዚህ የምንወያይበት አጀንዳ በሌለበት ሁኔታ ከእንደዚህ ዓይነት ወገን ጋር እንዳልኩሽ ሌላውን ደህናውን ጣት ይዞ እንዳይጠፋ ጥንቃቄ ከማድረግ በዘለለ ብዙ መደረግ የሚችል ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡

ዘመን፦ በተለይ ከግል ፕሬስ ጋር በተያያዘ ደክሟል በሚል አሁንም በርካታ ወገኖች ወቀሳ ያቀርባሉ፤

አቶ ጌታቸው፡ ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛ የአቅም ጉድለት አለ፡፡ አሁን እዚህ አገር አቡጊዳ ጨርሻለሁ ያለ በሙሉ ጋዜጣ ማቋቋም እፈልጋለሁ ይላል፡፡ ስሜት መግለጽ ጥሩ ነው፡፡ ማንኛውም ዜጋ ተማረም አልተማረም ስሜቱን መግለጽ መቻል አለበት፡፡ ማንኛውም ዜጋ የመጀመሪያ ዲግሪ ኖረውም አልኖረውም፤ ሁለተኛ ዲግሪ ኖረውም አልኖረውም በጽሑፍም ሆነ በሌላ መንገድ ስሜቱን መግለጽ መቻል አለበት፡፡ ጋዜጣ ማቋቋም ሲባል ግን ትንሽ ሙያ ይጠይቃል፡፡ ሙያ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን መረዳትም ይጠይቃል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን አሽቀንጥሬ እጥላለሁ፤ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን አላምንበትም፤ ወይ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉ አንቀፆችን አልቀበላቸውም ግን ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን አክብሬ አንቀፆቹን ለመለወጥ እታገላለሁ የሚል ፖለቲከኛ መብቱ እንደሆነው ሁሉ ቃር ቃር እያለውም ቢሆን በሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ ተገዝቶ ለሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ ያለውን ተቃውሞ የሚገልጽ ጋዜጠኛም ችግር የለውም፡፡ ከጅምሩ ግን በጋዜጠኝነትና በታጋይነት መሀል የተምታታበት፤ በጋዜጠኝነትና በትጥቅ ትግል አራማጅነት መሀል የተምታታበት ወገን እንዲፈጠር ያደረገ አንደኛ የብቃት ማነስ፤ የሙያ ስነ ምግባር አለመጠበቅ ሁለተኛም እንደዚህ ዓይነቱን ገንቢ የጋዜጠኝነት አውድ በመፍጠር ትልቅ ሚና ያላቸው ለምሳሌ ሚዲያ ካውንስል የሚባሉት ነገሮች አለመጠናከር የፈጠረው ነው፡፡ ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶች የመጻፍ፣ የመደራጀት ወዘተ ነጻነቶችን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መረጋገጥ ያለባቸው ተቋማዊ እና አስተሳሰባዊ መሠረቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት የሚጠበቁ ነገሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ እንዲህ ዓይነት ነፃ የሚዲያ ተቋማትን ማጠናከር፤ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ መስጠት፡፡ ያ ማለት ሱቅ ከፍተሸ ታደራጃቸዋለሽ ማለት አይደለም፡፡ ጋዜጠኞች መንግሥት ቀብቷቸው እነዚህ ናቸው ነፃ ጋዜጠኞች ብሎ ያስቀምጣቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ወደዚህ ዓይነት ሥራ ውስጥ መገባት የለበትም፡፡ ግን ለሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ አክብሮት ያላቸው በሙያ ደረጃም አለ የሚባል ነገር ማሟላት የቻሉ ሰዎች ብቻ ናቸው እንደዚህ ዓይነት ፕሮፌሽን ውስጥ መግባት ያለባቸው፡፡ ከዚህ ውጪ የመጀመሪያ ቅፅ ጋዜጣውን አመጽ እንዴት እንደሚነሳና አገር እንዴት እንደሚበጠበጥ የሚገልፅ ጋዜጣ ጋዜጠኛ ነው ተብሎ እንዴት እንደሚወሰድ አይገባኝም፡፡ ሽፍትነት አላዋጣ ስላለው፤ ምክንያቱም መንገድ ተሠርቷል አሁን፤ አባይ በረሃም ላይ መሸፈት አይቻልም አሁን፤ ተከዜም ላይ መሸፈት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ጋዜጣ ውስጥ መሸፈት እችላለሁ ብሎ አዲስ አበባ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሰው ለምን ራሱን እንደ ጋዜጠኛ እንደሚቆጥር ወይም ጥፋት አጥፍቶ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሕግ እርምጃ ሲወሰድበት ጋዜጠኛ ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው ተብሎ የፕሬስ ነፃነት ለማፈን የተደረገ እርምጃ ነው ተብሎ እንደሚወሰድ አይገባንም፡፡ ስለዚህ በጋዜጠኝነትና በሽፍትነት መካከል ያለውን ልዩነት ማስቀመጥ መቻል አለብን፡፡ ለሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ ያለን አክብሮት ነው እዚህ ላይ ወሳኝ የሚሆነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ተቋማዊ ድጋፍ መስጠት ያለብን አካባቢዎች አሉ፡፡ በዚያ ደረጃ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ ከዚያ አንፃር መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ግን ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ይከበር፤ ለሕገ መንግሥት መሰረታዊ የሆነ አክብሮት ያለው ተቋም ተቋቁሞም ጭምር ፕሮፌሽናሊዝም ትልቅ ነገር ነው። የሙያ ስነ ምግባር፡፡ ድሮ የጭቃ ጅራፍ ማጮህ ነበር፡፡ ድሮ በድንጋይ መወራወር ሰፈር ውስጥ ሆነሽ፡፡ አሁን ጋዜጣ ውስጥ ተደብቆ በግለሰቦችም ላይ በፓርቲዎችም ላይ እንደዚሁ ድንጋይ መወራወር የሚመስል ተግባር ላይ የሚገቡ ሰዎች ዞሮ ዞሮ ህብረተሰቡ ለጋዜጦች፣ ለፕሬስ ነጻነት ያለውን አክብሮት የሚያሳንሱ፤ ህብረተሰቡ የእንደዚህ ዓይነት ነጻነቶች እድገት አካል ሳይሆን ጭራሹኑ በነሱ ተንገሽግሾ እነዚህንስ ከማየት ወደሚል ነገር ሊያስገቡት የሚችሉ ስለሆኑ በዚህ ደረጃም መሰራት ያለባቸው ሥራዎችም ይኖራሉ።

እነርሱ የተደራጀ ተሳትፎ ባደረጉ ቁጥር እርስ በርስ የሚማማሩበትና የጨዋታውን ህጎች አክብሮ መንቀሳቀስ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው የሚረዱበት፤ በዛ ላይ የተመሰረተ በእርስ በርስ መማማር ላይ የተመሰረተ ስርዓት የሚያጎለብት ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ይሄ ከሦስቱም ወገን ኮሚትመንት ይፈልጋል። ከመንግሥትም ከህዝብም በሙያው ከተሰማሩ ወገኖችም። ይሄን ማድረግ ከተቻለ ነጻ ፕሬስ ላንድ ሀገር ትልቅ ሀብት ነው። መንግሥት የፈለገውን ያክል ጥሩ ዓላማ ቢኖረው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሥራቸው ውስጥ የፓርቲም ይሁን የመንግሥት ሥራቸውን በሚመለከት እርስ በርስ የሚያደርጉት ግምገማ በጣም ምህረት የለሽ ግምገማም ቢሆን ሦስተኛ ወገን ሥራቸውንና አፈጻጸማቸውን በሚመለከት ያለው ግንዛቤ በነጻው ፕሬስ በኩል በቀናነት ሲንጸባረቅ ደግሞ የበለጠ ግብዓት የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው። ስለዚህ ለሀገር ዕድገት ለሀገር ፖለቲካ ስርዓት መገንባት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው። ይህን ትልቅ አስተዋጽኦ መጫወት ግን የሚችለው ቅድም ያነሳኋቸውን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ግምት ውስጥ አስገብቶ የተንቀሳቀሰ እንደሆነ ብቻ ነው። የጭቃ ጅራፍ የሚያጮህ ሚዲያ ህገመንግሥታዊ ስርዓቱን ለመናድ አስር አቋራጮች የሚል ማብራሪያ በየቀኑ እየሰጠ የሚውል ሚዲያ በምንም ስሌት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትን ገንቢ አካል ሆኖ ይወጣል የሚል ግምት የለም፡፡ ስለዚህ አትኩሮት መደረግ ያለበት እንዴት ነው? ያንን አዎንታዊ ሚናውን መጫወት በሚያስችለው ደረጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችለውስ እንዴት ነው? ከዚህ አንጻር ከሦስቱም አካላት ከመንግሥትም ከህዝቡም ከባለሙያዎችም የሚጠበቅነገር ይኖራል። እሱን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ይሆናል።

ጥያቄ፦ ከሰሞኑ በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች የትጥቅ ትግል ጀምሬያለሁ ስለሚል ወገን እየተወራ ነው ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የሚሉት ምንድን ነው?

አቶ ጌታቸው፦ፍላጎት አለ፡፡ ፍላጎትና ድርጊት አይገናኙም። አንድ ወቅት አልቃኢዳ ብዙ ነገር የማድረግ አቅም ነበረው። አሜሪካን ድረስ በአውሮፕላን ህንጻዎች አፍርሷል። የኋላ ኋላ ጥቃቱ ሲበዛበት አልቃኢዳ ወደ ምንም ወረደ.. በየሰፈሩ የሚነሱ ግጭቶች ሳይቀር ኃላፊነት መውሰድ ጀመረ። አንዳንዴ ሊቢያ አካባቢ ነዳጅ ጋዝ ፈንድቷል ከተባለ እኔ ነኝ ያደረግኩት ይላል። ኬንያ አካባቢ በጎሳዎች ግጭት ምክንያት አንድ የነዳጅ በርሜል ተቃጠለ ከተባል እሱንም እኔ ነኝ ያደረኩት ይላል። አልቃኢዳ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የእውነት የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ያደርጋል። የኛ ሰዎች ከአላማ አንጻር ሽብር ላይ የተሰማሩ ስለሆነ ከአልቃኢዳ ጋር የሚለዩበት ምክንያት የላቸውም፡፡ ግን እንደመታደል ይሁን ወይም እንዳለመታደል እነዚህ ሰዎች ከድርጊታቸውና ከአቅማቸው ይልቅ ፍላጎታቸው ነው አይሎ የሚወጣው። እናም ሽፍቶች አንድ አካባቢ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሳይቀር እኛ ያደረግነው ነው ወዘተ... ይላሉ። ግን እሱ አይደለም ጠቃሚው ነገር። ፍላጎታቸው ነው። ፍላጎት አላቸው ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይ የምልመላ እና የስልጠና በተለይ ከሻዕቢያ ጋር በመሆን ሙከራዎች ያደርጋሉ። የሚልካቸው መንግሥት ካሁን በፊት በመቶ ሺዎች ከሚቆጥር ሰራዊቱ ጋር ሆኖ ሊያደርጋቸው ያልቻለ እንቅስቃሴዎች በነዚህ ጥቂት ሰዎች በኩል ክላሽን አንጠልጥለው በሚመጡ ሰዎች በኩል አስፈጽማለሁ የሚል እምነት አለው ወይ ጄንዩንሊ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ግን ፍላጎት አለው ነው። ፍላጎት አለው ብቻ ሳይሆን በአንድም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ሰዎችን አሾልኮ በማስገባት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ለማድረስ የተደረጉ ሙከራዎች አሉ። አሁን ይሄ ትጥቅ ትግል ጀምሬያለሁ የሚለው ከዚህ በዘለለ ሰሞኑን ሞቅ ደመቅ ተደርጎ የተወራበት ምክንያት መሪዎች ነን የሚሉት ሰዎች ቀለብ ሊሰፈርላቸው ይገባል። ብዙዎቹ ቅድም ላይ አንስቼልሽ ነበር የረባ የጨዋ የሚባል ሥራ ላይ ተሰማርተው ራሳቸውንም ቤተሰባቸውንም መደጎም የሚችሉ ሰዎች አይደሉም። አሜሪካኖች ፕሮፌሽናል ሌፍት የሚሏቸው አሉ። በቋሚነት መንግሥትን በማውገዝ በቋሚነት ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማውግዘ ብቻ የተሰማሩ። ስለዚህ ብር ይዋጣላቸዋል። ሥራቸውን እንዲሰሩ ማለት ነው። እነዚህ ደግሞ ፕሮፌሽናል ጯሂዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ቀለብ ሊሰፈርላቸው ይገባል። እና አመቺ አጋጣሚዎች ይፈልጋሉ። በዚያ ሰሞን የእግር ኳስ ጨዋታ ነበር። ሰው ሰብሰብ ብሎ ስለነበር እንደው የተዳከሙ አባላቶቻቸው ሳይቀር ዲፕረስድ ሆኑ። ቀጠሮ ሲቀጥሯቸው በዚህ ሳምንት ልንደርስ ነው ሲሏቸው ለታኀሣሥ 12 ልንደርስ ነው ሲሏቸው በዚያ ምክንያት የተበሳጩባቸው ወዳጆች ነበሯቸው። ይሄን ዜና አውጥተው ትንሽ ብር ማሰባሰብ ፈለጉ፡፡

ይሄን ዜና አውጥተው ትንሽ ተንፍሰ ማድረግ አለባቸው፡፡ በነገራችን ላይ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶላቸዋል፡፡ አንድ ቦታ 37 ሺ አንደኛው ሰማንያ ሺ ዶላር እንደዚህ ይሰባሰባል፡፡ አሁን አስመራ የገቡት እንደሚሉት ትግላቸው የመሪዎቹን ቅርብ ክትትል የሚጠይቅበት ምዕራፍ ላይ ስለደረሰ ነው፡፡ ከኛ አቅጣጫ አይታይም ይሄ ወሳኝ ምዕራፍ፡፡ ከዲሲ አቅጣጫ እንዴት እንደሚታይ አይገባኝም፣ ከፊላዴልፊያ እንዲሁም ከአስመራ፡፡ ከኛ አቅጣጭ ግን ይሄ ወሳኝ ምዕራፍ አይታይም፡፡ ግን ፍላጎት አላቸው እንዳልኩሽ፡፡ አጋጣሚዎችን ከመጠቀም ውደ ኋላ አይሉም፡፡ አገር ውስጥ ያሉ ወኪሎች ልከው፣ የትርምስ ሥራ ከመስራት ወደኋላ አይሉም፡፡ ጸረ ህዝብ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የሽብር እንቅስቃሴ ነው ስለዚህ እንደማንኛውም የሽብር እንቅስቃሴ የጸጥታ ኃይሎችና የሕዝብ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር የሚያውለው እንቅስቃሴ ነው የሚሆነው፡፡ ከዛ በዘለለ ይሄ የትጥቅ ትግል እንዳልሽው ፌስ ቡክ ላይ ነው በብዛት የሚካሄደው፡፡ ምርኮኞቹም ያሉት እዛ ነው፡፡ ቁስለኞቹም ሟቾቹም ያሉት ሶሻል ሚዲያ ላይ ነው፡፡ እንግዲህ በሶሻል ሚዲያ ላይ ባለ ቁስለኛ እና ሞት የሚገኝ ድል ካለ ኋላ የምናየው ነው የሚሆነው፡፡

ዘመን፦ ሌላ የሚጨምሩት ሀሳብ ካለ ?

አቶ ጌታቸው፦ ብዙ ሰው ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ በሚመለከት ያለው ግንዛቤ አሜሪካንን ጨምሮ ከትላልቅ ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ በጣም ቁንጽል ነው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘጠና ዘጠኝ በመቶው ኑሮውን ለማሸነፍ የሚጥር ባለው አቅም ቤተሰቡን ሀገሩን ለማገዝ የሚሞክር ነው፡፡ እሱ ግን አይጮህም፡፡ ስለዚህ ስለሱ ብዙ አንሰማም ስለሱ ብዙ አናወራም፡፡ የምንፈጥራቸው መድረኮች ይሄኛውን ጎን ለማጉላት በሚያስችለን መልኩ መጠቀም ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ ከኃያላን ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ከአሜሪካ ከቻይና ከእንግሊዝ ጋር ያለን ግንኙነት ከምንም በላይ ሀገራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር የሚመጥን ኩራት ያለው መንግሥት ነው፡፡ ደጅ አይጠናም፡፡ ትእዛዝ አይቀበልም፡፡ መርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ከማንም ሀገር ጋር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ከአሜሪካም ይሁን ከቻይና፣ ከራሺያ፣ ከእንግሊዝ ጋር ያለን ግንኙነት ሀገራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ይሄንን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለ ለዘመናት ራሱን ከጠላት ተከላክሎ የኖረ ራሱን ለዘመናት ያስተዳደረ ህዝብ በየኤምባሲው ደጅ በሚጠኑ፤ መንግሥት ቀይሩልን በሚሉ፤ እርዳታ ይቁም ብለው በሚጮሁ ጥቂት ፎካሪዎች ሰላሙና መረጋጋቱ ሊረበሽ አይገባም ብቻ ሳይሆን በእንደዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ላይ በተመሰረቱ ሰዎች ሊመራ አይችልም፡፡ ስለዚህ የተሻለ ዲሰርቭ ስለሚያደርግ አሁን ያለው መንግሥት ይህንን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ በሚገባ የሚገነዘብ ከምንም ነገር በላይ ሀገራዊ ጥቅምን ቅድሚያ ሰጥቶ የሚንቀሳቀስ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በሚመለከት በሰዎች ይሁንታ በሰዎች መልካም ግምገማ ወይም መጥፎ ግምገማ ላይ ተመስርቶ ወደ ኋላና ወደ ፊት አይልም፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላምና ጥቅም ለማረጋገጥ ብዙህነቷን የሚያስተናግድ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ድህነትን ተዋግቶ ብልጽግናን ማስፈን የሚያስችል የህዝብ ተሳትፎን ያረጋገጠ ሥራ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለን ጸጥታ አሁን ያለን መረጋጋት አሁን ያለን ሰላምና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መነሻውን ማረጋገጥ የጀመርነው የህዝቡን ሰፊ ተሳታፊነት ዕውን ማድረግ ያስቻለ ዴሞክራሲያው ስርዓት ግንባታ በቁርጠኝነት በመጀመራችን የተገኘ ውጤት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይሄንን ነው ማለት የምፈልገው፡፡

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137307
TodayToday118
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week18
This_MonthThis_Month3389
All_DaysAll_Days137307

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።