የታበሱ፣ ያልታበሱ እንባዎች Featured

03 Sep 2015

የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአገራችን ዴሞክራሲ እንዲያብብና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ ብሎም የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ኃላፊነትን ተቀብሎ የሚሰራና እየሰራ ያለ ተቋም ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁን እዚህም እዚያም ከሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የመብት ጥሰቶች አኳያ ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት በሚገባ እየተወጣ ነው? ተቋሙ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የስንቶችንስ እንባ አበሰ? ስንል የተቋሙን ዋና እንባ ጠባቂ ወይዘሮ ፎዚያ አሚንን ጠይቀናል፡፡የዜጎችን መብት ጥሰው ምላሽ ስጡ ሲባሉ ለተቋሙ ተገቢውን ምላሽ የማይሰጡና ትብብር የማያደርጉ የመንግስት አካላት ተጠያቂነታቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ አውግተውናል፡፡ በርካታ ነጥቦችንም አንስተን ተወያይተናልና ያንብቡት፡፡

ዘመን፡- /ሮ ፎዚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ በመሆንዎ እናመሰግናለን፡፡

/ሮ ፎዚያ፡- እኔም በመምጣታችሁ ደስ ብሎኛል አመሰግናለሁ።

ዘመን፡- የፌዴራል የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የብዙዎችን እንባ ማበስ ዋናው ተልዕኮ ነው፡፡ እስኪ እስካሁን የስንት ተበዳዮችን እንባ አበሰ? ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በደል የሚደርስባቸውን ግለሰቦችስ እንባ በሚገባ አብሷል?

/ሮ ፎዚያ፡- እንግዲህ እንባ በተለያየ መልክ ነው የሚፈሰው። በመከፋት ብቻም ሳይሆን በመደሰትም የሚፈስበት ሁኔታ ይኖራል። ዞሮ ዞሮ ግን ከተቋሙ ዓላማ ብንነሳ ጥሩ ይሆናል። በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 መሠረት የተቋቋመ ተቋም ነው። በተለይ በዋናነት በአዋጅ 211/92 ላይ ለእንባ ጠባቂ ተቋም በርካታ ስልጣንና ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል፡፡ ለተቋሙ ከተሰጡት ሥልጣን፣ ኃላፊነትና ተግባራት መካከል አንደኛው ዜጐች በተለያየ ምክንያት ተጐድተው፣ በደል ደርሶባቸውና ቅሬታ አድሮባቸው እንዳይቀሩ ቅሬታቸውን በማየትና በመመርመር በደሎች ደርሰውም ከሆነ እንዲታረሙና እንዲስተካከሉ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ሕጐችና አሠራሮች አፈፃፀማቸውን በተመለከተ እንደ ምክር ቤቱ ሆኖ አስፈፃሚውን አካል እንዲቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ሌላው በሁለተኛው አዋጅ ማለትም በአዋጅ 590/2000 ደግሞ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅን በተመለከተ ዜጎች መረጃ የማግኘት፣ የመጠየቅና የማስተላለፍ መብታቸውን ያረጋገጠውን ይህን አዋጅ እንዲያስተገብር ሥልጣን ተሰጥቶታል። እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ላይ ነው አትኩረን የምንሠራው። እንግዲህ ከእነዚህ መካከል ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ አቤቱታዎችን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ከቀበሌ፣ ከወረዳ፣ ከከተሞች፣ ከክልሎችና ከፌዴራል ተቋማት በርካታ አቤቱታዎችን ሲያይና ሲመረምር ነው የቆየው። በሂደቱ አንዳንዶቹ የመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑና ለነዚህም ምላሽ የሚሰጥበት በሌላ መልኩ በተቋሙ ሥልጣንና ኃላፊነት ሥር የማይወድቁትን ደግሞ እየመከረ የሚመልስበት ግን ደግሞ በተቋሙ ሥልጣንና ኃላፊነት ሥር የሚውድቁ የአስተዳደር በደል ተፈጽሞባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን ከተጠሪ ተቋማት ጋር ወይም አቤቱታ ከቀረበበት ወይም በደል አድርሶብኛል ከሚባለው ተቋም ጋር በመተባበር በደሎቹ እንዲታረሙ በርካታ ሥራዎችን ስንሠራ ነው የቆየነው። እና ከዚህ አንፃር ተቋሙ በርካታ በደሎችን አርሟል። በርካታ እንባዎችንም አብሷል ማለት ይቻላል።

ዘመን፡- በቁጥር ላይ መነጋገር እንችላለን? ይሄን ያህል አቤቱታዎች ቀርበው ለእነዚህ ያህሉ ምላሽ ተሰጥቷል ወይም እንባቸውን አብሶ ሸኝቷል ማለት ይቻላል?

/ሮ ፎዚያ፡- ይቻላል። ይሄ ዳታ በየዓመቱ አለ፡፡ በየአምስት ዓመቱም አለ። ባለፈው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከያዝነው ዕቅድ ወደ 22,000 አቤቱታዎችን ተቀብለን እናስተናግዳለን ብለን ከእነዚህ ውስጥ ወደ 17,000 ወይም 18,000 አቤት ባዮች አቤቱታ መርምሮ በትክክል የደረሱ በደሎች እንዲታረሙ ተደርጓል። ተቋሙ የሚሰጣቸውን የመፍትሔ ሃሳቦች ተቀብሎ ላለመፈጸምና ላለማረም ደግሞ የሚያንገራግሩ አስፈጻሚ አካላት አሉ። እነዚህ በየክልሉና በየከተማው አጋጥመውናል። እና በጥቅሉ ተቋሙ እንባን ለማበስ የሄደባቸው ሁኔታዎች የሚበረታቱ ናቸው ማለት ይቻላል።

ዘመን፡- እርስዎም እንዳሉት እኛም ከተለያዩ ሚዲያዎች እንደሰማነው የመብት ጥሰቶችንና በደሎችን ለማረም የሚያንገራግሩ አስፈፃሚ አካላት አሉ። ለምሳሌ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የአርሲ ዞን፣ የአዲስ አበባ መሬት ልማት አስተዳደር ወዘተ- እነዚህ አስፈፃሚ አካላት ለዚህ ትልቅ የዴሞክራሲ ተቋም ተገቢውን ምላሽ የማይሰጡት ለምንድን ነው? ጉልበተኝነት ነው?

/ሮ ፎዚያ፡- እንግዲህ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ እነሱ ናቸው የሚያውቁት። እኛ የምናውቀው ምላሽ ያለመስጠታቸውን ነው። በደል ፈጽመዋል፡፡ እዚህ ላይ እርግጠኛ ነን። የመብት ጥሰት አለ።

ዘመን፡- የመብት ጥሰቱ በግለሰቦች ላይ ነው?

/ሮ ፎዚያ፡- አዎ! የአዋሳውም በግለሰቦች ላይ ነው። የአሰላውም ከጡረታ መብት ጋር የተያያዘ ነው። ዜጐቹ ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን ነው የጠየቁት። ያቀረቡት አቤቱታዎች በተቋማችን ሲመረመሩ ተገቢና ተጨባጭነት ያላቸው የመብት ጥሰቶች ናቸው። በደሎቹ እንዲታረሙ ለአስፈፃሚ አካላቱ የጊዜ ገደብ ሰጥተን ነበር፡፡ ሆኖም ለማረም ፈቃደኞች አልነበሩም። እናም ተቋሙ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ጉዳዩን ለምክር ቤቱ ልዩ ሪፖርት አድርጓል። በሂደቱ ምክር ቤቱም ገብቶበት የታረሙ በደሎች አሉ። ለምሳሌ ሐረር ላይ በደል ደርሶ ልዩ ሪፖርት አቅርበን ነበር። እነዚያን ልዩ ሪፖርቶች ምክር ቤቱ ተቀብሎና መርምሮ የታረሙ በደሎች ነበሩ። ሀዋሳ ላይም በኋላ ለማረም ፈቃደኝነትን የማሳየት ነገር ነበር። እኛ ግን የታረሙትን ትተን ያልታረሙት ነው ለምክር ቤቱ የምናሳውቀው።

ዘመን፡- የእንባ ጠባቂ ተቋም እንዲህ ያሉ በደሎችን ለማረም ፈቃደኛ ያልሆኑ እንቢተኛ ተቋማት ሲያጋጥሙት ለምክር ቤቱ ሪፖርት ከማድረግ ባሻገር ሌላ የሚወስደው እርምጃና ሥልጣን የለውም?

/ሮ ፎዚያ፡- ተቋሙ በሚያቀርባቸው የመፍትሄ ሃሳቦች መሰረት ጉዳዮች በድርድር እንዲያልቁ በማደራደር ነው አብዛኛውን ሥራ የሚሠራው። ምክንያቱም አንደኛ ይሄ ወጪ ቆጣቢ ነው። ሁለተኛ አስፈፃሚው አካል ወይም በደሉን ያደረሰው አካል በሌላ የበላይ አካል አርም ከመባሉ በፊት በደሉን አይቶ እዚያው እንዲያርም ጭምር ዕድሉን እንሰጠዋለን። የሚሰጠው ጊዜም አጭር ነው። እንደ ፍርድ ቤት ምስክር፣ የመከላከያ ምስክር፣ ቀጠሮ ወዘተ ተብሎ አይደለም ረጅም ሂደት የሚኬደው፡፡ አንድ ተበዳይ በደል ደርሶብኛል ብሎ ማስረጃውን አያይዞ ያቀርባል። ተቋሙ ሄዶ ይመረምራል፡፡ ከዚያ ችግሩ ካለ ችግር ያደረሰው ተቋም ችግሩን እንዲያርም ይነገረዋል፡፡ ከዚያ አዎ አጥፍቻለሁ፣ በድያለሁ ይላል፡፡ እዚያው ችግሩ ይታረማል። ይሄ ጊዜንና ወጪን ከመቆጠብ አንፃርና በቀላሉ ለኅብረተሰቡና ለዜጋው ተደራሽ ከመሆን አኳያ ተመራጭ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ በዚህ መንገድ ነው የሚያልቁት። አሁን ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ እየተጠናከረ ሲመጣና የእኛም የማስፈፀም አቅማችን እየጨመረ ሲመጣ እንዲሁም በአገልግሎት፣ በንግድና በትምህርት የተሻሉ ሰዎች ወደ አስፈፃሚው አካል እየመጡ ባሉበት ሂደት ሰዎች ሕጐችን፣ ሕገመንግሥቱንና መመሪያዎችን እያዩና እየተገበሩ ነው። አልፎ አልፎ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወይም በቸልተኝነት የመብት ጥሰቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በደሎች ፈፅማችኋል ሲባሉ ቶሎ ተቀብለው የሚያርሙ አስፈፃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በዚህ ዓይነት በርካታ ነገሮች ናቸው እየታረሙ ያሉት። እና ይሄ ተቋሙ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የሚቀር ሳይሆን መንግሥትም መልካም አስተዳደርንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እውን ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣት ጋር ይያያዛል።

ነገር ግን በተለያየ ምክንያት አስፈፃሚውጋ ስህተቶችን ላለመቀበልና ላለመሸነፍ እንዲሁም አጥፍተሀል መባልን ያለመፈለግና ተጠያቂነትን የመሸሽ ነገር አለ። ይሄ እኔ የምሰጠው ውሳኔ ሁሌም ትክክል ነው ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭም ይመስለኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት መንፈስ ያላቸው ግለሰቦችም አሉ። እነኚህ ግን በጣም ጥቂት ግለሰቦች ወይም ተቋማት ናቸው። እንዲህ ዓይነት ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ የቻልነውን ያህል ጥረት አድርገን ችግሩ እንዲፈታ እናግባባለን፤ እንገፋለን። በዚህ መልኩ ሄደን ስህተቱን የሚያርም አለ። አንዳንዱ ደግሞ የራሱን ያችኑ የያዛትን አልለቅም ብሎ የራሱን ምክንያት እየደረደረ እስከ መጨረሻው የሚገፋም አለ። እንግዲህ ችግር የሚፈጠረው ይህ አካል እስከ መጨረሻው ስህተቱን ለማረም ዝግጁ ካልሆነ ምንድን ነው የሚደረገው? ነው። ሁሉም ሰው ተጠያቂነት አለበት። ሕገ መንግሥታችን የመንግሥት ሥራ ሁሉ በግልፀኝነትና በተጠያቂነት መንፈስ መፈፀም አለበት ይላል። ስለዚህ ሁሉም አካል ይሄንን የሕገ መንግሥት ፅንሰ ሃሳብ ተቀብሎ መሥራትና መፈፀም ግዴታው ነው። እኛ እንዲህ ዓይነት የእምቢተኝነት ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ በሁለት መንገድ እናያለን፡፡ አንዱ ሲጠየቅ መልስ አልሰጥም ለሚለው በተቋማችን የማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ስህተቱን እንዲያርም ተጠይቆ መልስ አለመስጠት በወንጀል የሚያስቀጣ ነው። ጉዳዩ ቀጥታ ለአቃቤ ሕግ ተልኮ ግለሰቦቹ ወይም ተቋማቱ በወንጀል የሚጠየቁበትና የሚከሰሱበትን ሂደት እንከተላለን። ሌላው መልስ ሰጥቶ የመጨረሻው መፍትሔ ሃሳቡ ላይ ደግሞ ለመፈፀም የሚያንገራግር አካል ካለ እኛ ለምክር ቤቱ አለመፈፀሙን ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ በዚያ በኩል ይጠየቃሉ። ሌላው ደግሞ በሚዲያ የማጋለጥ ጉዳይም አለ፡፡ ኅብረተሰቡ ውሳኔውን አልፈፅምለትም ያለን በዳይ አመራር፣ ተቋም ወይም አስፈፃሚ በሚዲያ በማጋለጥ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ዋጋ እንዲያጣ የሚደረግበት ሁኔታ አለ።

ዘመን፡- ስለዚህ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ እናንተ በመንግሥት ተቆርሶ የተሰጣችሁን ሥልጣንና ኃላፊነት በመተግበሩ በኩል በየትኛው እርከንና ደረጃ ላይ ራሳችሁን ታስቀምጣላችሁ?

/ሮ ፎዚያ፡- እንግዲህ ተቋሙ የአሥር ዓመት ዕድሜ ነው ያለው፡፡ የመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ተቋሙን በማደራጀት ላይ ነው የጨረስነው። ተቋሙ በዚህ በፌዴራል ደረጃ በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ነበር የነበረው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 80 ሚሊዮን ይጠጋል። ከዚህ አንፃር ሲታይ ተቋሙ በእያንዳንዱ ቀበሌ፣ ማኅበረሰብና ቤተሰብ ውስጥ ገብቶ በደሎችንና ችግሮችን አርሟል ማለት አይቻልም። በዚህ ደረጃ ተቋሙ ተደራሽ አልነበረም። አሁን ተቋሙ ቢያንስ ስድስት ክልሎች ላይ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን ከፍቷል። እስከ ወረዳ ያሉ የቅሬታ ሰሚ ተቋማት አሉ፡፡ ከእነዚህ ጋር ደግሞ ቅንጅታዊ አሠራርን በመፍጠር በደሎች ወይም አቤቱታዎች እዚያው እንዲታረሙ የሚደረግበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሄድንበት ሁኔታ በርካታ ነው። ከዚህ አንፃር ኅብረተሰቡ ጋ ለመድረስ የምናደርገው ጥረት የተሻለ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጦች አሉ። ኅብረሰቡን ለመድረስና እንባውን ለማበስ የምንሠራቸውን ሥራዎች በጥራት ለመሥራት የተሻለ ጉዞ ተጉዘናል ማለት ይቻላል። የተደራሽነቱ ጥያቄ ግን እንዳለ ነው። ተቋሙም አዲስ እንደመሆኑ የልምድ ማነስም አለ። ከአገራችን ባህል ጋርም ተያይዞ በደሎችን ለማረም የምንሄድባቸው ሂደቶች በራሳቸው አዲስ ከመሆናቸው አንፃር ችግሮች ይገጥሙናል።

ዘመን፡- በደልና የመብት ጥሰት የደረሰባቸው ግለሰቦች የተቋማችሁን አሠራር ላያውቁ ይችላሉና እንዴት ነው ወደ እናንተ መጥተው አቤት የሚሉት? እንዲህ ያሉ ተበዳዮች ጋ የምትደርሱበት መንገድ አለ?

/ሮ ፎዚያ፡- በሚዲያዎች ማስታወቂያዎችን እናስነግራለን። ስፖቶችንና መልዕክቶችን እናስተላልፋለን፡፡ ነፃ የስልክ መስመርም አለን። የአዲስ አበባና የክልል ሚዲያዎችንም እንጠቀማለን፡፡ አሁን እየተለመደ መጣ እንጂ አንድ ሰው በደል ቢደርስበት እንዲህ ያለ ተቋም ላይ አቤቱታዬን አቀርባለሁ የሚል ግንዛቤ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ የለም። እዚህ ላይ ግንዛቤ ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በብዛት በተለያዩ የክልል ቋንቋዎች የተለያዩ የክልል ሚዲያዎች ላይ ማስታወቂያና ስፖቶችን እናስነግራለን። ግንዛቤውም በዚሁ መልክ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ አለ።

ዘመን፡- የመረጃ ተደራሽነት ላይም ተቋማችሁ ኃላፊነትና ስልጣን አለው። እኔ እንደ ጋዜጠኛ አንዳንድ ተቋማት መረጃ መስጠት የማይፈልጉ አጋጥመውኛል። መጠየቅን የማይፈልጉ፣ ተገቢ የሆነ መረጃ ስጡን ስንል የሚያንገላቱ አሉ። መረጃ መስጠት ላይ ችግሮች አሉ። ስለዚህ ተቋማት መረጃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ ከማድረግ አኳያ እናንተ ተገቢውን ስራና ሚና ተጫውታችኋል ማለት ይቻላል?

/ሮ ፎዚያ፡- አዋጁን ማስተግበር ከጀመርን ሶስት ዓመት ይሆናል። እንደሚታወቀው በዚህ ረገድ የሚሰሩት ስራዎች ሰፊ ናቸው፡፡ ይሄ እንግዲህ ከክፋት ጋር ብቻም ሳይሆን ባህላችንም ጭምር ስለሆነ ነው። ይሄ ድብቅና ሚስጢራዊ በሆነው ባህላችን ምክንያት ሚስጢር ያልሆነውንም ሚስጢር ነው ብሎ የመደበቅ ሁኔታ ይታያል። ፓርላማ ያፀደቀውንና በአደባባይ ታትሞ የወጣውን መመሪያና ህግ አንድ ተቋም ጋር ሄደህ ይሄን መመሪያና ህግ ስጡኝ ብትል አይ ይሄ ሚስጢር ነው የሚል እሳቤና ባህል ያለበት ማህበረሰብና ሥርዓት ውስጥ ነው የቆየነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር በዚህ ሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። በአብዛኛው ከባህል ጋርም የተሳሰረ ነገር አለው። መረጃ የመጠየቅና የማግኘት መብት የዜጎች ህገ መንግስታዊ መብት ነው። በእኛ ህግ ደግሞ የመረጃ ነፃነት አዋጁ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ማንም ሰው ነው የሚለው፤ የውጭ ዜጋም ቢሆን ከማንኛውም የመንግስት አካል መረጃ የማግኘትና መረጃ የማስተላለፍ መብት አለው፡፡ በአዋጁ በህግ ክልከላ ከተጣለባቸው መረጃዎች ማለትም ከሀገር ደህንነት ጋር የተያያዙ፣ የግለሰብና የድርጅት፣ የንግድ ወዘተ ሚስጢር ጋር የሚያያዙ አሉ በአዋጁ፤ ከእነዚህ ውጪ ያሉ መረጃዎችን በሙሉ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሰዓት ከየትኛውም የመንግስት ተቋም የማግኘትና የማስተላለፍ መብቱ ተረጋግጦለታል። ከዚህ አንፃር ሲታይ ጋዜጠኛም ሆነ ሌላ ዜጋ ማንኛውም የመንግስት አካል ጋ ሄዶ መረጃ ቢጠይቅ ለምን ፈለክ? ተብሎ መጠየቅ የለበትም። ህጉ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ የምትፈልገውን መረጃ ስትጠይቅ ተቋሙ ለምን ትፈልጋለህ? ብሎ ማለት መብት የለውም፡፡ ተቋሙ ማረጋገጥ ያለበት የተጠየቀው መረጃ የመረጃ ክልከላ የተጣለበት ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ብቻ ነው። ስለዚህ ከዚህ አንፃር ስናይ ጋዜጠኛ መረጃ ጠይቆ የማያገኝበት ሁኔታ ይስተዋላል። እንዲያውም የመንግስት አስፈፃሚ መረጃ ሳይጠየቅ መስጠት አለበት ነው የሚለው አዋጁ። ሳይጠየቅ እትሞ የማውጣት ግዴታ አለበት። ከዚህ አኳያ ከአመለካከት፣ ከባህል ወዘተ ጋር የሚያያዙ ነገሮች አሉ። ስለዚህ ይሄ ስራ ተጀመረ እንጂ ገና ነው።

ዘመን፡- እንደሚታወቀው እርስዎ የአፍሪካ እንባ ጠባቂዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ነዎት። ይሄ ደግሞ ለሀገራችን በተለይም አሁን እየገነባነው ላለው ገጽታችን ትልቅ ትርጉም አለውና እዚህ ላይ ሃሳብ ካለዎት ቢጨምሩ?

/ሮ ፎዚያ፡- ይሄ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ትልቅ ስራም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራዎች በጣም ሰፊ ናቸው። የመረጃ ነፃነትን ማስከበሩም እንደዚያው። ስራው እነዚህ በጣም ትልልቅ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያካተተ ስራ ነው። ስለዚህ ከዚህ አንፃር ባለፉት አስር ዓመታት ተቋሙ የሄደበት ሂደት አለ። በእርግጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ፡፡ ተቋማዊ የመፈጸም አቅሙ እንዲሁ፡፡ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር የምንሰራቸው በርካታ ስራዎች አሉ። በውስጥ ያሉብንንም ችግሮች እየቀረፍንና የተቋሙን አቅም እያጎለበትን ህብረተሰቡ ከተቋሙ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት በፍጥነትና በጥራት እንዲያገኝ ለማድረግ የተጀማመሩ ስራዎች አሉ፡፡ እነዚህን ስራዎች አጠናክሮ በመቀጠል ተቋሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ብቻም ሳይሆን የዜጎችን ህገ መንግስታዊና ሰብዓዊ መብቶች ከማስከበር አንፃር ትልቅ ኃላፊነት ነው የተጣለበት። ይሄ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ እውነት ለመናገር ከባድ ነው። በውስጡ ብዙ ነገሮች አሉት። እነዚህን ኃላፊነቶች ለመወጣት የቻልነውን ያህል ጥረት እናደርጋለን የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።

የአፍሪካ እንባ ጠባቂዎች ማህበርን በተመለከተ ማህበሩ ባለፈው ዓመት በሀገራችን 4ኛውን ጉባኤውን አካሂዶ ኢትዮጵያ ማህበሩን ለአራት ዓመታት እንድትመራ ኃላፊነት ተሰጥቷታል። ይሄም በጣም ከባድ ስራ ነው። እና እዚህ ላይ ያለንን አቅም አጠናክረንና የአፍሪካ ሀገሮችንም ልምድ ወስደን በአህጉሪቱ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብቶች በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲከበሩ ለማድረግ እንሰራለን። በዚህ ረገድ ልምዶችን የተሻለ አፈፃፀም ካላቸው የአፍሪካ ሀገሮች እያመጣን ተግባራዊ እንዲሆን ካደረግን ለአገርም ለተቋሙም ትልቅ ጥቅም ነው።

 

አዘጋጅ ሰሎሞን በቀለ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137304
TodayToday115
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week15
This_MonthThis_Month3386
All_DaysAll_Days137304

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።